ቦይንግ "ችግሩ ተፈቷል" እያለ ነው

በኢትዮጵያው የአውሮፕላን አደጋ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ሲገልጹ

አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ችግሩን ፈትቼዋለሁ እያለ ነው። እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉት የቦይንግ 737 ማክስ ስሪቶች ጋር በተያያዘ ኩባንያው ላለፉት ወራት የሚይዝ የሚጨብጠው ጠፍቶት ሰንብቷል።

በተለይም የኢንዶኒዢያው ላየን አየር መንገድ አውሮፕላን በተከሰከሰ በአምስተኛ ወሩ የኢትዯጵያ አየር መንገዱ አደጋ ሲደገም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አየር መንገዶች የ737 ማክስ ስሪቶችን ላለማብረር ወስነው ነበር። ይህም በቦይንግ ላይ የቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራን ማድረሱ ሲነገር ቆይቷል።

ዋናው የችግሩ ምንጭ እንደሆነ የሚጠረጠረውን "ኤምካስ" የተሰኘውን የመቆጣጠሪያ ሲስተም ቀይሬያለሁ ብሏል ቦይንግ።

ያም ሆኖ እንዳይበሩ የተደረጉት የብዙ አገራት የማክስ ስሪቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ይመለሳሉ የሚል ግምት የለም።

ይህም የሆነው ቢያንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተከሰከሰበትን ምክንያት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ስለሚጠበቅ ነው።

ኤምካስ የተባለውን ሲስተም አድሻለሁ የሚለው ቦይንግ አሁን አውሮፕላኖቹ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ቢገቡ ማስጠንቀቂያ የሚልክ ዘዴን ቀይሻለሁ ይላል። ይህ ዘዴ ቀደም ሲል እንደ አማራጭ የነበረ እንጂ አስገዳጅና መደበኛ ሲስተም ሆኖ ከቦይንግ የቀረበበት ሁኔታ ጨርሶ እንዳልነበረ የአቪየሽን ባለሞያዎች ይናገራሉ።

ይህ አሁን ተሻሽሎ ይገጠማል የሚባለው የቅድመ ጥንቃቄ ሰጪ ሲስተም በኢንዶኒዢያውም ኾነ በኢትዯጵያው አየር መንገድ ላይ ያልነበረ ነው። ይህ ሲስተም መገጠሙ አውሮፕላኑ የሚቃረኑ ምልክቶችን ሲሰጥ ለፓይለቶቹ ጥቆማን ይሰጣል ተብሏል።

ቦይንግ ለደንበኞቹ ይህን ሲስተም የምገጥምላችሁ በነጻ ነው፤ አንዳችም ክፍያ አልጠይቃችሁም ብሏቸዋል።

ተሻሻለ የተባለው ሶፍትዌር ምንድነው?

ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) ለሚለው ምህጻረ ቃል ነው። ይህ ሲስተም አውሮፕላኑን የሞተሩ ክብደትና የተቀመጠበትን ቦታ ምክንያት አድርጎ እንዳይቆምና እንዳያጋድል ያደርገዋል። ይህም አውሮፕላኑ ሽቅብ በሚወጣ ጊዜ የሚያሳየውን ዝማሜ ተከትሎ ሚዛኑን እንዲያስጠብቀው ለማድረግ የተሠራ ነበር።

ነገር ግን የኢንዶኒዢያው ላየን አውሮፕላን ምርመራ ውጤት እንዳመላከተው ይህ ሴንሰር አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ነው።

ይህም ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው። የተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘምና እንዲምዘገዘግ አድርጎታል።

አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስበርሱ የሚጣረስ ምልእክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘውን መቆጣጠሪያ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ባልቦላ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው።

ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሊከሰስ ይችላል?

የአሜሪካ የአቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ከአምስት ወራት በፊት በተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አውሮፕላንና በኢትዯጵያው አደጋ ምስስሎሽ እንዳለ አምኗል።

ባለፈው ረቡዕ በአሜሪካ የሴኔት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ለጥያቄ የቀረቡት የአሜሪካ የአቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ተጠባባቂ ኃላፊ ዳንኤል ኤልወል መሥሪያ ቤታቸው በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ለአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ አሳልፎ የሰጠበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሸንጎ አቅርቧቸዋል።

ቦይንግ ያመረታቸው ማክስ ዘመነኛ አውሮፕላኖች እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ የምሕንድስና ሕጸጽ እያለባቸው እንዴት በተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ የይለፍ ፍቃድ አገኙ የሚለው ዓለምን እያነጋገረ ቆይቷል።

አንዳንድ የምርመራ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ባለበት የበጀትና የባለሞያ እጥረት ምክንያት የአምራቹን ቦይንግ መሐንዲሶች ራሳቸው አውሮፕላኑን ፈትሸው እንዲያረጋግጡለት በከፊል ኃላፊነቱን አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር።

ሴናተር ሪቻርድ ብሉሜንተል ይህንን ዝርክርክ አሠራር "ቀበሮ የአውራዶሮ ማደሪያ ቆጥ እንዲጠብቅ" ከማድረግ የማይተናነስ ሲሉ የሰላ ትቸት ሰንዝረውበታል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያው አደጋ ከደረሰ በኋላ በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች እርምጃ ሲወስዱ የአሜሪካ የአቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ግን የማክስ አውሮፕላኖችን እንዳይበሩ ውሳኔ ለማስተላለፍ ዘገምተኛ ሆኗል በሚል ከሴናተሮች ተጨማሪ ወቀሳ ቀርቦበታል።

የባለሥልጣኑ ተጠባባቂ ኃላፊ ግን ለሴናተሮች ትቸት እጅ አልሰጡም።

"በኤምካስ ሶፍትዌር ላይ እምነት አለኝ። አብራሪዎችም ቢሆን አውሮፕላኑ ድንገት በአፍንጫው ሲደፋ ያንን ለመቀልበስ የሚያስችል በቂ ስልጠና ወስደዋል" ሲሉ ፍርጥም ብለው ለሸንጎው ምላሽ ሰጥተዋል።

"እንዲያ የሚሉ ከሆነ ታዲያ የኢንዶኒዢያው አውሮፕላን በአንድ ደቂቃዎች ውስጥ 21 ጊዜ በአፍንጫው ሲደፋ ፓይለቱ ለምን ዝም አለ?" ሲባሉ " በጉዳዩ ዙርያ ለጊዜው በቂ ምላሽ የለኝም። መረጃ ይዤ እመለሳለሁ" ብለዋል።

በቀጣይነት ምን ይጠበቃል?

ቦይንግ አድሼዋለሁ፣ በነጻ ትወስዱታላችሁ ያለውን ሶፍትዌር በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ለአሜሪካ ፌዴራል የአቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ያስረክባል።

ነገር ግን አዲሱ ሶፍትዌር ተቀባይነት እንዲያገኝ አውሮፕላኑ ሲስተሙ ላይ ተጭኖ፣ ስለ አፈጻጸሙ ፍተሻና ግብረ መልስ ከተገኘ በኋላ ፓይለቶች እንዲሰለጥኑበት ይደረጋል። ይህን ሁሉ ሂደት ካለፈ በኋላ ነው አውሮፕላኖቹ እንዲበሩ "የይብረሩ ሰርተፍኬት" ሊያገኙ የሚችሉት።

አሁን ምርመራ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ የብሔራዊ ተራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ፣ የፈረንሳይ የአቪየሼን ምርመራ ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በዚህ ሳምንት መጨረሻ የመጀመርያ ዙር የምርመራ ውጤታቸውን ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።