በሕዝብ ቆጠራው መራዘም የትግራይ ክልል ቅሬታና የኮሚሽኑ ምላሽ

የኢትዮጵያ ህዝቦች Image copyright Getty Images

የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በሃገሪቱ መፈናቀልና ግጭቶች መኖራቸው እንዲሁም ቆጣሪዎችን በመልመል ረገድ በሚጠበቀው ደረጃ በቂ ዝግጅት አልተደረገም በሚሉና ሌሎች ምክንያቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም የውሳኔ ሃሳብ ከሳምንት በፊት ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

ይህንኑ ተከትሎ በዚህ ሳምንት የትግራይ ክልል መንግሥት የሕዝብና ቤት ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገቢ አይደለም ሲል ምክንያቶቹን በመጥቀስ መግለጫ ሰጥቷል።

የትግራይ ክልል መንግሥት ካነሳቸው ምክንያቶች አንዱ "ጉዳዩ በምክክር ላይ ያለ እንጂ ውሳኔ የተላለፈበት አለመሆኑ ነው" ሲሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አብራሃም ተከስተ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምስት ነጥቦች ስለቀጣዩ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ

''መጋቢት ዘጠኝ ላይ ነው አስአኳይ ስብሰባ የተጠራው። በመሃል በነበሩት ጊዜያት አዲስ የተከሰተ ነገር የለም። አብዛኞቹ ክልሎችም በተቀሩት ጊዜያት የቆጠራ ዝግጅቱን አጠናቀው ቆጠራ ማካሄድ እንደሚቻል ነው ሃሳብ ያቀረቡት፤ ስለዚህ የግልጽነት ችግር አለ'' ብለዋል።

"የሕዝብ ቆጠራውን ወደሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ የውሳኔው ሃሳብ የተላለፈው በቆጠራ ኮሚሽኑ እንጂ በሕዝብ ተወካዮችና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች ውሳኔ አላገኘም" የሚሉት የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ አቶ ቢራቱ ይገዙ፤ "ኮሚሽኑ ለብቻው ያስተላለፈው ውሳኔ አይደለም" በማለት ይከራከራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የክልሎች ተወካዮች የሆኑ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች ባሉበት ውይይት ስለተደረገ፤ ከተገለጹት ምክንያቶች ውጪ ሌላ ሰበብ የለም።

ኢትዮጵያዊያን ቶሎ አያረጁም?

በአንድ ቦታ የተሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የሕዝብና ቤት ቆጠራው እንዲራዘም የውሳኔ ሃሳብ የቀረበው ከሳምንት በፊት እንደመሆኑ፤ በተደጋጋሚ መረዘሙ ተአማኒነትን አያሳጣም ወይ ለሚለው ጥያቄ አቶ ቢራቱ መልስ ሲሰጡ ''በችግር ውስጥ ተሁኖ ሲሰራ ነበር፤ ትክክለኛ ቆጠራ ተካሂዷል ወይ የሚል ጥያቄ ሊቀርብበት የሚችለው፤ ነገር ግን ችግሮች ከተቀረፉ በኋላ ቆጠራን ማካሄድ ተአማኒነቱን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም'' ብለዋል።

አቶ ቢራቱ ይህንን ይበሉ እንጂ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ "ቆጠራው መራዘሙ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያሉ ድንጋጌዎችንም የጣሰ ነው" ብለዋል።

''በየአስር ዓመቱ ቆጠራው እንዲካሄድ ነው ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገው። ስለዚህ መንግሥት ሥራውን ስላልሰራ ቆጠራው ይተላለፍ ብሎ መወሰን የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ እንዲከበር ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየው።'' ሲሉም ያክላሉ ዶ/ር አብርሃ ተከስተ።

አቶ ቢራቱ በበኩላቸው "የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ አልጣስንም፤ እየሰራን ያለነው ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ነው" በማለት ያስረዳሉ።

''ሕገ መንግሥታችን የህዝብና ቤት ቆጠራው በየአስር ዓመቱ ይካሄዳል ይላል፤ ይሄ በግልጽ የተቀመጠ ነው። ነገር ግን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶና ከህግ አንጻር ገምግሞ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ይሆናል'' በማለት የአሰራር ሂደቱን ያብራራሉ።

Image copyright Anadolu Agency

ለቆጠራው ቅድመ ዝግጅት ክልሉ ወጪ በማውጣቱ የማራዘም ውሳኔው ተገቢ ላለመሆኑ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አብርሃም ያነሱት ሌላኛው ምክንያት ነው።

"ለቅድመ ዝግጅቱ ብዙ ወጪ ስለተደረገበትና መተላለፉ ደግሞ ኪሳራ ስላስከተለ በቀጣይ ቆጠራው ሲካሄድ ክልሉ ላልተፈለገ ወጪ ይዳረጋል" በማለት ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል። ከዚህ አንጻር ኃላፊነት የሚወስድ አካልና ተጠያቂነትም መኖር አለበት ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ጌዲዮ በዐቢይ ጉብኝት ማግስት

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ቢራቱ ምላሽ ሲሰጡ ምንም እንኳን አንዳንድ የልማት ድርጅቶ የቆጠራውን ወጪ የሚሸፍኑ ቢሆንም እስካሁን በነበሩትም ሆነ አሁን ወጪውን የሚሸፍነው የፌደራል መንግሥት ስለሆነ የክልሎች ወጪ እምብዛም ነው ይላሉ።

''60 በመቶ በመንግሥት ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በልማት አጋሮች የሚሸፈን ነው ብለን ነበር የተነሳነው፤ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ወጪውን እየሸፈነ ያለው የፌደራል መንግሥት ነው። ከዚህ ውጪ ክልሎች ምናልባት ወደታች ማህበረሰቡ ጋር ወርደው የማስረዳትና የመቀስቀስ ሥራ ስለሚሰሩ ወጪ ሊያወጡ ይችላሉ ግን ብዙ አይደለም'' ይላሉ የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ቢራቱ።

ሰማይ ላይ ወልዳ አሥመራ የምትታረሰው ኢትዮጵያዊት

ከዓመት በፊት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተወሰኑ ክልሎች በነበረ የፀጥታ ችግር መራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁንና የፀጥታ ችግሮቹ ተቀርፈው በዚህ ዓመት እንደሚካሄድ ተጠብቆ የነበረና ሰፊ ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ቢሆንም የሕዝብና ቤት ቆጠራው በድጋሚ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።