ሴተኛ አዳሪነት ባህል የሆነበት ማህበረሰብ

ቤተሰቦች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ሴተና አዳሪነት ይገፋፋሉ

አብዛኛው የህንድ ማህበረሰብ ከሴት ይልቅ ወንድ ልጅ እንዲወለድለት ነው የሚፈልገው። ሂና ስትወለድ ግን ቤተሰቦቿ በተለየ መልኩ ነበር የተደሰቱት። ደስታቸው የመነጨውም ባልተለመደ መልኩ ወደፊት ምን እንደሚያሰሯት በማሰብ ነበር።

ራቅ ባለ የህንድ አካባቢ 'ባቻራ' ከተባለው ማህበረሰብ የተገኘችው ሂና ህይወቷን የምትመራው በወሲብ ንግድ ነው።

ለብዙ መቶ ዓመታት የዚህ ማህበረሰብ አባላት መጀመሪያ የሚወለዱ ሴት ልጆቻቸውን ከ10 እስከ 12 ዓመት ሲሞላቸው ለገንዘብ ገላቸውን እንዲሸጡ ይገፏፏቸዋል።

የሴቶችና ወንዶች የኢኮኖሚ እኩልነት እንዴት ይስፈን?

የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ እድሜዋ ሲገፋ ቀጥላ የምትመጣው ሌላኛዋ የቤተሰቡ ሴት ልጅ እሷን ተክታ ወደ እዚህ ሥራ ትሰማራለች፤ ይህ ደግሞ ሁሉም ተቀብሎት የሚተገብረው የማህበረሰቡ ልምድ ነው።

ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ በኖረው በዚህ ባህል የሚገኘውን ገንዘብ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሚጠቀሙት ወንዶቹ ወይም የቤተሰቡ አባወራ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሴቶቹ ሥራቸውን በትክክል መስራታቸውን የሚቆጣጠሩት አባቶች አልያም ወንድሞቻቸው ናቸው።

ሌላው ቢቀር የዚህ ማህበረሰብ ሴቶች ሲዳሩ ቤተሰቦቻቸው ለጥሎሽ ረብጣ ገንዘብ ይጠይቃሉ። ምክንያቱ ደግሞ ወደ ወንዱ ቤተሰብ ከሄደች በኋላ ብዙ ገንዘብ እንደምታስገኝላቸው ስለሚታሰብ ነው።

''ምንም አማራጭ የለኝም''

ሂና ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ እድሜ ልኳን ለዚህ ተግባር ስትዘጋጅና ስትለማመድ ነው ያደገችው።

''ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ሳለሁ ወደዚህ ሥራ ተገድጄ ገባሁ። ትምህርቴን ማቋረጥ ነበረበኝ፤ ምክንያቱም የእናቴንና የአያቴን ፈለግ መከተል ግዴታዬ ነበር'' ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ብቻቸውን ወደ መዝናኛ ስፍራ የሚሄዱ ሴቶች ፈተና

በእያንዳንዱ ቀን ከገጠር ሃብታሞች እስከ የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌሮች ድረስ ደንበኞቿን ታስተናግዳለች።

''ልክ 18 ዓመት ሲሞላኝ የምሰራው ሥራ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማኝ ጀመር። በጣም እናደድ ነበር፤ ግን ምን አማራጭ አለኝ?''

''እኔ ይህንን ሰርቼ ገንዘብ ካላገኘሁ ቤተሰቤ በምን ይኖራል? ቤተሰቤ ይራባል።''

የባቻራ ማህበረሰብ አባላት ከሌሎቹ የህንድ ማህበረሰቦች ጋር ሲነጻጸሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ገንዘብ ነክ ጥያቄዎቻቸውን የሚመልሱት ሴቶቹ ላይ በመተማመን ነው።

በአካባቢው የሚንቀሳቀስ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የሚሰራው አካሽ ቾሃን እንደሚለው በዚህ ሥራ ከሚሰማሩት ሴቶች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ናቸው።

ታዳጊ ህጻናቱ በአካባቢው በሚገኝ የጠፍር አልጋ ላይ ለብቻቸው ወይም ተሰብስበው በመቀመጥ ደንበኞቻቸውን ይጠባበቃሉ። በቅርበት ደግሞ አነስተኛ ሱቆች ይኖራሉ። ብዙ ጊዜ አንድ የቤተሰብ አባል በሱቋ ውስጥ ከደንበኞች ጋር ስለክፍያው መጠን ድርድር ያደርጋል።

በድርድሩ መሰረትም አንድ ደንበኛ በአማካይ ከ40 እስከ 80 ብር ድረስ ይከፍላል። ነገር ግን ከዚህ በፊት ከወንድ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያልፈጸመች ከሆነች ክፍያው እስከ 2000 ብር ድረስ ከፍ ሊል ይችላል።

የህንድ ብሔራዊ ጋዜጣ ባወጣው መረጃ መሰረት ከ5500 የማህበረሰቡ አባላት ላይ የደም ናሙና ተወስዶ 15 በመቶ የሚሆኑት በደማቸው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

"ከመቶ ምናምን ፓርቲ ሴት የምናገኘው አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ሊሆን ይችላል" ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

አብዛኞቹ ሴቶች ከሥራው ጋር በተያያዘ ያልተፈለገ እርግዝና ያጋጥማቸዋል የምትለው ሂና እራሷ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሴት ልጅ እንደተገላገለች ትናገራለች።

''ብዙ ሴቶች ወዲያው ያረግዛሉ። ይሄ ሲታወቅ ብዙ ገንዘብ አግኝተው ልጃቸውን እራሳቸው እንዲንከባከቡ በሚል ምክንያት ከሌላ ጊዜው ተጨማሪ ደንበኛ እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ።''

አጭር የምስል መግለጫ ሂና

የወሲብ ንግድ ውስጥ የሚሰተፉ ሴቶች ደግሞ እዚያው ማህበረሰባቸው ውስጥ አባል የሆነ ወንድ ማግባት አይችሉም።

ሂና በጊዜ ብዛት ከአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ባገኘችው እርዳታ በመታገዝ ይህንን ልማድ ተፋልማ አሸንፋ መውጣት ችላለች። ነገር ግን አሁንም ብዙ ታዳጊ ሴቶች በዚሁ ልማድ ታስረው እንዳሉ ትናገራለች።

''በዚህ እርኩስ ልምድ ውስጥ ያለፈ ሰው ብቻ ነው መከራው ሊገባው የሚችለው። ሴቶቹ ምን እንደሚሰማቸው እኔ አውቃለው፤ ስለዚህ ይህንን ልምድ ለማስቀረት እሰራለሁ።''

የባቻራ ማህበረሰብ እስከ 33 ሺህ የሚደርሱ አባላት ያሉት ሲሆን 65 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው። የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ትንንሽ ሴት ህጻናት ታፍነው ወደዚህ አካባቢ ስለሚወሰዱ ነው።

አካሽ እንደሚለው ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ 50 የሚደርሱ ህጻናትን ከዚህ ንግድ ማዳን ችለዋል።

''ሌላው ቢቀር ለዚሁ ተግባር ታፍና ተወስዳ የነበረች የሁለት ዓመት ህጻን ወደ አሳዳጊ ቤተሰቦች እንድትላክ አድርገናል።''

ሴት ተመራቂዎች ለምን ሥራ አያገኙም?

የህንድ መንግሥትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚሰሯቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ምክንያት ይህ ተግባር እየቀነሰ የመጣ ይመስላል። ወጣት ሴቶች በወሲብ ንግድ መሳተፍ አንፈልግም እያሉ ቤተሰባቸውን መሞገት ጀምረዋል።

አንዳንዶቹም ከአካባቢው ራቅ ብለው በመሄድ ሌላ ሥራ ማፈላለግ ጀምረዋል። ትምህርታቸው ላይ ማተኮር የጀመሩም አሉ።

ሂና እሷን ከዚህ ህይወት ካወጣት የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን ለውጥ ለማምጣት እየሰራች ነው።

''ሌሎች ታዳጊ ሴቶች ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉና ከወሲብ ንግድ መውጣት እንደሚቻል ለማሳየት የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለው'' ብላለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ