ዐቢይ እና የኢትዮጵያ ለውጥ፡ በመስቀለኛ መንገድ ላይ?

መስቀለኛ መንገድ Image copyright Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጥተው በተለያዩ ፈተናዎች የተተበተበውን የሀገሪቱን ፖለቲካ ለማስተካከል የሚያስችሉ ቁልፍ የሚባሉ እርምጃዎችን ቢወስዱም ከአንድ ዓመት በኋላ አሁንም ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ናት የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ላለፈው አንድ ዓመት በለውጥ መንገድ ስትጓዝ ቆይታለች። ይህ የለውጥ ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ቢሆንም የጉዞው በተደጋጋሚ መንገራገጭ በርካታ ጥያቄዎችን እያስነሳ፣ ስጋት እያጫረና ፍርሃትንም እያነገሰ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠንከርና መረር ያለ ንግግር ማድረጋቸውም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው የሚሉ አሉ።

የድኅረ ዐብይ ሚዲያ በምሁራኑ ዕይታ

ከእነዚህ ነገሮች በመነሳት ለውጡን በሚመለከት ፅንፍ ለፅንፍ የሆኑ አስተያየቶች እየተንፀባረቁ ሲሆን የለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይንም መተቸትና ማብጠልጠልም ተጀምሯል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የለውጥ እርምጃ ከአንድ ዓመት በኋላ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ የአገሪቱ የፖለቲካ ሽግግር ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፖለቲካ ተንታኞች የየራሳቸውን ምልከታ ያስቀምጣሉ።

"አዲስ አበባ እንደ እየሩሳሌም"

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ጎን ለጎን እየሄዱ እንደሆነ፤ ይህ ደግሞ ለውጡን መስቀለኛ መንገድ ላይ እንዳቆመው ያስረዳሉ። "ስለዚህ ከሁለቱም ነገሮች ጋር ወደፊት እየገፋን ነው" ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሃገሪቱ ውስጥ ላሉ በርካታና ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ የሆንኑ ዘንድ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።

ከእነዚህም መካከል እንደ ምርጫ ቦርድ ማሻሻያ፣ የፀረ ሽብርና የሲቪል ማህበራትን የተመለከቱ ሕጎችን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ፕሮፌሰር መረራ ተስፋ ሰጪዎች ከሚሏቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያነጋገሩ መሆናቸውም ሌላው የሚጠቅሱት ነገር ነው።

በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

በዚህ ሂደት ውስጥ የለውጡ እንከን ወይም ተስፋ አስቆራጭ ከሚሏቸው ውስጥ የመጀመሪያው የኢህአዴግ አቋም ላይ የሚያነጣጥር ነው። "ገዥው ፓርቲ ራሱ ለውጡን ለማንበብም ሆነ ወደ ፊት ለመግፋት አንድ ላይ ነው ወይ? የተወሰነው ለውጡን ሲገፋ የተወሰኑት ወደ ኋላ የሚጎትቱ ይመስላል።"

አክለውም ሽግግሩን መስቀለኛ መንገድ ላይ እንዲሆን ያደረጉ ከሚሏቸው ያልተመለሱ የታሪክ ፈተናዎችን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጣሉ።

ያላለፍናቸው የታሪክ ፈተናዎች ከሚሏቸው የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ ሲሆን "አዲስ አበባም እየሩሳሌም እንዳትሆን አንዳንድ ቦታዎች ስጋቶች እየተፈጠሩ ነው" ይላሉ።

የለውጡ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ አልባ መሆንም ለእሳቸው ሌላው ከባድ ችግር ነው።

እየተደረጉ ባሉ ነገሮች ማለትም ምን አይነት ኢትዮጵያ? ምን አይነት ለውጥ? በምን ደረጃ ወዴት? የሚሉ ነገሮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ተደርሶ የተቀመጠ ፍኖተ ካርታ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አላቸው፤ ፕሮፌሰር መረራ።

ዶ/ር ዐብይ በግላቸው ለውጥ ያመጣሉ?

ከገዢው ፓርቲ በተጨማሪም በፖለቲካው መድረክ ላይ ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ በሆኑ አጀንዳዎች አብሮ ለመስራት አለመሞከርም ሌላው የለውጡ እንከን እንደሆኑ ያምናሉ።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተገኝተው 'ለውጡ እዚህ አልደረሰም' የሚል ነገር ከህዝቡ መስማታቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ "በዚህ መንገድ ከቀጠልን ህዝቡ በለውጡ ተስፋ እንዳይቆርጥ እሰጋለሁ" ይላሉ።

በተጨባጭ በህዝቡ ፖለቲካዊም ሆነ ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ መሬት ላይ የሚታይ ነገር ከሌለ ለውጥ ለውጥ የሚባለው ነገር የልሂቃን ጨዋታ ሆኖ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው።

ፕሮፌሰር መረራ ጨምረውም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እተከሰቱ ለሰዎች መፈናቀልና መጎዳት ምክንያት እየሆኑ ለሚታዩት ግጭቶች መፍትሄ መፈለግም በጣም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ይጠቁናሉ።

ኦዴፓና አዴፓ እየተገፋፉ ነው?

በኬል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር አወል አሎ ስለለውጥ ሲወራ እንደ አገር የነበርንበት ሁኔታ ምንድን ነው? ከየት ወደ የት ነው የምንሻገረው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል ይላሉ።

የአገሪቷ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ተቃርኖዎች ምንድን ናቸው? ትልልቆቹ የፖለቲካ ጥያቄዎችስ? እነዚህ ጥያቄዎች አብዛኛው የፖለቲካ ኃይል እንደሚፈልገው ይፈቱ ቢባል በምን መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል? የሚለው ነገር ለዶ/ር አወል ወሳኝ መነሻ ነው።

ለየት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ደብዳቤ ለየመኖች

ከዚህ ነጥብ በመነሳት ምንም እንኳ ፈታኝና የሚያሰጉ ነገሮችን እየተመለከቱ ቢሆንም አሁን ያለው ሽግግር መጥፎ ደረጃ ላይ ነው ብለው አያስቡም።

እሳቸው እንደሚሉት እየታዩ ያሉ ነገሮች ይገጥማሉ ተብሎ መታሰብ ነበረበት። "ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ መከፋፈሎች፣ ከሚስማሙበት ይልቅ የማይስማሙበት ነገር የሚበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሉበት፤ በጥቅሉ ብዙ ቀይ መስመሮች ያሉበት" ይላሉ።

ስለዚህም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አሁን የለውጥ ሂደቱን ያጋጠሙ ችግሮች እንዳይፈጠሩ፤ ከተፈጠሩም በጊዜ ለመፍታት መስራት ነበረበት ብለው ያምናሉ ዶ/ር አወል። መንግሥት ያን አድርጎ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለው ከመስመር የወጡ ነገሮችን፤ ሥርዓት አልበኝነትን ማስቀረት ይቻል ነበር ብለው ያስባሉ።

ነገር ግን በለውጡ ሂደት ውስጥ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም "ተስፋ ልንቆርጥ የምንችልበት ቦታ ላይ በጭራሽ አልደረስንም" በማለት ነገሮችን ወደ መስመር ለማስገባት አሁንም እንዳልረፈደ ይገልፃሉ።

የተወሳሰበ ታሪክ ባለው እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የፖለቲካ ሽግግር ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ቢሆንም መንግሥት ሊሰራቸው ሲገባ ያልሰራቸው የቤት ሥራዎች መኖራቸው ዶ/ር አወልን ጨምሮ ለብዙዎች አከራካሪ ጉዳይ አይደለም።

ለህይወታቸውና ለንብረታቸው ዋስትና ላጡ ሰዎች የዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ጉዳይ ሁለተኛ ስለሚሆን መንግሥት በአሁኑ ወቅት ለህግ የበላይነት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያሳስባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወታደሮቹ ድርጊት ተበሳጭተው እንደነበር ተናገሩ

በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ብሔረተኝነትን በሚያራምዱ ኃይሎች መካከል እየተካሄዱ ያሉ ክርክሮችና መበሻሸቆች አገሪቱን ወደ ትልቅ አደጋ ሊመራ ይችላል የሚል ስጋትም አላቸው።

የብሔርን መሰረት ያደረጉ ብሔረተኞች የድሮውን ሥርዓት እኛ ላይ ለመጫን እየተንቀሳቀሰ ነው፤ የኢትዮጵያ ብሔረተኞች ደግሞ ስለኢትዮጵያ ጥሩ ጥሩ ነገር ቢናገሩም በተግባር ግን የብሔረተኞቹን አላማ ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እየወቀሱ ያሉበት ሁኔታን በማሳያነት ይጠቅሳሉ ዶ/ር አወል።

የእነዚህ ሁለት ኃይሎች ክርክር ከገዥው ፓርቲ ዘንድ ጭምር ደርሶ መከፋፈልን እየፈጠረ ነውም ይላሉ። በተለይም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጎራቸው ውስጥ ያሉ ብሔረተኛዎችን የመከተል ግልፅ አዝማሚያ ታይቷል ይላሉ።

እነዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስበትን የሚቆጣጠሩ ፓርቲዎች በየበኩላቸው ባሉ ብሔርተኛ ቡድኖች ተፅእኖ ስር ከወደቁ ለአገሪቱ ከባድ አደጋ እንደሚሆን ጨምረው ያስረግጣሉ።

"ፓርቲዎቹ መግባባት ሳይችሉ ቀርተው የሚፈጠረው ንትርክ ገዥውን ፓርቲ እንደ ፓርቲ እንዳይቀጥል የሚያደርግ ከሆነ ይህች ሃገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትወድቃለች ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምታሉ።

ትልቅ ተፅዕኖ የነበረው ህወሓት ወደ ዳር መውጣት ራሱን የቻለ ችግር በሆነበት ሁኔታ በኦዴፓና በአዴፓ መካከል ያለው ሁኔታ ለገዥው ፓርቲ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ።

ፖለቲካ ሁሌም ሰጥቶ መቀበል ስለሆነ እንደ ወጣት በስሜትና በኃይል ከመሄድ ይልቅ ማመቻመችን ምርጫቸውን ማድረግ እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

ነጥብ ማስቆጠር

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ አብርሃ ሃይለዝጊ ወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታ የፖለቲካ ኃይሎች ባለመደማመጥ እየተወነጃጀሉ ነጥብ ለማስቆጠር ብቻ የሚሮጡበት በመሆኑ አገሪቷ ትልቅ አደጋ ላይ ነች የሚል ስጋት አላቸው።

ስለዚህም የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ቆም ብለው አገሪቷ እንዴት ትዳን? ብሎ በማሰብ ሃላፊነት በተሞላ መንፈስ መወያየት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ይላሉ።

"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

እንደ ዶ/ር አወል ሁሉ ከመቼውም በላይ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ለ'አንተም ተው አንቺም ተይ' ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።

ጽንፍ የወጡትን የፖለቲካ አመለካከቶችና ፍላጎቶችን ለማቀራረብና ፍጥጫን ለማስቀረት ደግሞ ሳይዘገይ ከስሜታዊነት የራቁ ሃቀኛና ግልጽ ውይይቶች የሚደረጉባቸው የፖለቲካ መድረኮች ያስፈልጋሉ ይላሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በ100 የሥራ ቀናት የት የት ሄዱ? ምን ምን ሠሩ?

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ