ለመጀመሪያ ጊዜ ከኤች አይቪ በሽተኛ ኩላሊት ተለገሰ

ኒና ማርቲኔዝ [መሀል] ኩላሊቷን በመለከሷ ደስተኛ ናት Image copyright AFP/GETTY
አጭር የምስል መግለጫ ኒና ማርቲኔዝ [መሀል]

በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ኤች አይቪ ኤድስ በሽተኛ ወደ ሌላ የኩላሊት ልገሳ ተደረገ።

ቀዶ ጥገናው የተደረገው በአሜሪካ ሜሪላንድ ጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ሲሆን ሁለቱም ታካሚዎች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

"በዓለማችን ኤች አይቪ ያለበት ሰው ኩላሊቱን ሲለግስ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው" በማለት ዶ/ር ዶሪ ሴጄቭ ትናገራለች።

ከዚህ በፊት በሚለግሰው ሰው ላይ ኤች አይቪ ከፍተኛ የኩላሊት በሽታ የመፍጠር ዕድል አለው ተብሎ ይታሰብ ነበር።

ነገር ግን አዲስ የመጡት መድኃኒቶች በኩላሊት ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ ተረጋግጧል።

ጆን ሆፕኪንስ የምትሠራው ዶ/ር ክርስቲን ዱራንድ ቀዶ ጥገናው "ኅብረተሰው ኤች አይቪን የሚያይበትን መንገድ ይፈትናል፤ ከዚም አልፎ መድኃኒቶች እንዲሻሻሉ ያደርጋል" ብለዋል።

ታካሚዎቹ "በዚህ ልዩ ዕድል በጣም ደስተኛ ናቸው፤ አሁን የረጅም ጊዜ ውጤቱን ነው የምንጠባበቀው" በማለት ዶ/ር ዱራንድ ጨምረዋል።

ቀዶ ጥገናው የተካሄደው ሰኞ ሲሆን ኩላሊት የለገሰችው የ35 ዓመቷ ኒና ማረቲኔዝ "በጣም ደህና ነኝ" በማለት ለጋዜጠኞች ተናግራለች።

ኩላሊቷን ለመለገስ ያነሳሳት የ"ግሬይስ አናቶሚ" ተከታታይ ፊልም አንድ ክፍል እንደሆነ ተናግራ በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን ቀዶ ጥገና ማድረጓ እንዳስደሰታትም ተናግራለች።

"ዶክተሮቹ እኔን እየጠበቁ እንደነበር አውቃለው፤ ይህን የማድረግ ፍላጎት ያለው ማንም ሰው ቢሆን እንደሚቻል አሳይቻለው፤ ስለዚህ ቀጣዩን ሰው ለማየት ጓጉቻለው" ትላለች ኒና።

ኩላሊት የተቀበለው ሰው እራሱን ለመግለፅ ያልፈለገ ቢሆንም ጤናው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሆነ ዶ/ር ዱራንድ ተናግረዋል።

በዓለማችን ወደ 37 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከኤች አይቪ ጋር ይኖራሉ።

ሳይንቲስቱ መንትዮች ኤች አይ ቪ እንዳይዛቸው ዘረ መላቸውን አስተካከለ

ስለኤች አይ ቪ /ኤድስ የሚነገሩ 8 የተሳሳቱ አመለካከቶች