አምስት ጉዳዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ

ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የማስተዳደር መንበርን ከተረከቡ አንድ ዓመትን ሊደፍኑ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በስልጣን ቆይታቸው ሁለተኛ የሆነውን ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ሰጥተዋል።

ባለፉት ወራት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አነጋጋሪ ጉዳዮች በተከሰቱባቸው አጋጣሚዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልሆነም በተለያዩ ስብሰባዎች ባገኙት አጋጣሚ በሕብረተሰቡ ለሚነሱ የተወሰኑ ጥያቄዎችና ጉዳዮች ውስን መልስና ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል።

በዚህም ምክንያት ከተለያዩ ወገኖች ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። ስለዚህም ይመስላል ለሁለተኛ ጊዜ በጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ሰዓታት የወሰደ መብራሪያ የሰጡት። በመግለጫው ላይ የትኞቹ ቁልፍ ጉዳዮች ተነሱ?

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሲጀምሩ አዲስ አበባ የእኛ ናት የሚል ክርክር በስፋት ይነሳል ነገር ግን አዲስ አበባ የሁላችን ናት፤ በመሠረቱ አዲስ አበባ የማን ናት የሚል ጥያቄ በእኛ ደረጃ አንስቶ መወያየት አሳፋሪ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የማን ናት? የማን አይደለችም? እያሉ የሚከራከሩ ሰዎች ከጭንቅላታቸው ጀርባ ምን አስቀምጠው ነው የሚነጋገሩት የሚለውን በራሳቸው አውድ መመልከት ያስፈልጋል፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምን ታስቦ ነው የማናት የሚባለው? አዲስ አበባ የእኔ ናት ስል የአንተ አይደለችም ማለት ከሆነ ስቼያለሁ። የእኔ ሆና የአንተ እንዳልሆነች የምናገር ከሆነ ስህተት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁላችንም ናት።

ዐብይ አሕመድ ለኖቤል ሽልማት ታጭተዋል?

የፌደራል ሥርዓቱ ሲዋቀር አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለምትገኝ የኦሮሚያ አካል የማድረግ ፍላጎት ነበረ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቻርተርድ ፌደራል ከተማ መሆን አለባት ነገር ግን በዙሪያዋ ካለው አካባቢ ጋር ባላት ግንኙነት የተነሳ ክልሉ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለበት የሚል በሕገ መንግሥቱ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁን ባለበት አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ እንዳይሄድ በአልባሌ ጉዳይ ጊዜ እንድናባክን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ይህንን ሐሳብ የሚያንሸራሽሩት። ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይህ አጀንዳ ሊሆን አይችልም።

አዲስ አበባ የእኛ ናት ስንል መነሻችን ምንድነው? የዛሬ 20 ዓመት በአዲስ አበባ የአሁኑን ያህል ሰው አልነበረም፤ አዲስ አበባ ከፍቶትም ሆነ ተደስቶ የመጣውን ኢትዮጵያዊና የውጭ አገር ዜጎች አቅፋና ተሸክማ ኖራለች።

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላት ልዩ ጥቅም ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ፣ እንዴት ይተግበር የሚለው ላይ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደሮች በጋራ መምከር አለባቸው።

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው የልዩ ጥቅም መብት ግን ሊረጋገጥ ይገባል፤ የሚለውን ሀሳብ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ሊደግፈው የሚገባ ነው።

የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

ለኦሮሚያ ክልልም በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶች ሲባሉ አላግባብ ከአዲስ አበባ እድገትና መስፋፋት ጋር ከኢንዱሰትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚወጡ በካይ ፍሳሾች የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞንን የሚጎዱ መሆን የለባቸውም እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችም ተጠቃሚ መሆን ይገባቸዋል በሚል እንጂ አንድ ኦሮሞ አዲስ አበባ ላይ ከሌሎች በተለየ መልኩ መብት አለው ማለት አይደለም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል በሚያቀርበው ግብዓት ልክ ይጠቀም የሚል ሀሳብ ሊነሳ ይገባል። 170 ሺህ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚከናወኑ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መፈናቀላቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ዜጎች መርዳት ያስፈልጋል።

መንግሥት ተዳክሟል

የፌደራል መንግሥት ተዳክሟል ለማለት መለኪያው መሆን ያለበት ሀገር ስትወረር መመከት ሲያቅተው ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በብቃት መስራት አልችል ሲል ነው።

አሁን ግን በዚህ መልኩ የሚገለፅ አንዳችም ተግዳሮት አልገጠመንም በክልሎች የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ጣልቃ የማንገባው ክልሎች በራሳቸው መፍታት አለባቸው ብለን ስለምናምን ነው፤ ይህ ደግሞ ተገቢ ነው።

ኢህአዴግ

ኢህአዴግ የቀድሞ ጥምረቱ አለ፤ ብዙዎች የተለያየን የሚመስላቸው የልዩነት ሀሳቦች ሲኖሩ አራቱ ፓርቲዎች በውስጣዊ ውይይት ብቻ ይገድቡት የነበረው ሂደት ቀርቶ ፓርቲዎቹ የልዩነት አቋማቸውን በአደባባይ መግለፃቸው ነው ጥምረቱ የሌለ የሚያስመስለው።

የዶክተር ዐብይ አሕመድ 'ፑሽ አፕ'

በኦዲፒና በአዴፓ እንዲሁም በኦዲፒ በራሱ ውስጥ አንድነት እንጂ ምንም አይነት የተለየ ነገር የለም። ነገር ግን በመካከላቸው የልዩነት ሀሳቦች ይኖራሉ እነሱንም በመነጋገር እየፈታን ነው

በገዢው ፓርቲ አባላት መካከል የተጀመረው መቀራረብ ተጠናክሮ ይበልጥ ወደ አንድ ለመወሃድ የጀመርነው ሂደትም ይቀጥላል።

ኢኮኖሚ

ከለውጡ በኋላ በኢኮኖሚው ላይ በሚፈለገው መጠን ውጤቶች ያልታዩት ችግር ውስጥ ሆኖ ስለተቀበልን ነው። እሱን የማስተካከል ሥራ እየሰራን ቆይተናል። በዚህም በርካታ ሀገራት ድጋፍ ስላደረጉ ውጤት ማግኘት ተችሏል። አሁን ላይ ኢኮኖሚው ከታመመበት ሁኔታ ወጥቶ ጤናማ ሆኗል።

ግ የበላይነትን ከማስከበር

ከዚህ በፊት መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስዳቸው ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ከሰብዓዊ መብት አንፃር ጥያቄ የሚያስነሱ ነበሩ፤ መንግሥት ይህን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አንፃር ተገቢ ያልነበሩ እርምጃዎችን ሲወስድ ህግ አስከበረ ሲባል እንደነበረና አሁን ግን ያ ዓይነት አሰራር ትክክል እንዳልሆነ በመረዳት በለውጡ ውስጥ ማሻሻያዎች እየተደረጉ በመሆኑ ሕግን በተከተለ መልኩ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው።

በርካታ የፖለቲካ ሁነቶች የነበሩበት፣ በርካቶች ተስፋ የሰነቁበት፣ ሌሎች ደግሞ በፖለቲካ ሁኔታው ግራ መጋባት ውስጥ የገቡበት ነበር።

በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ከዚህ ባለፈ በርከት ያሉ የዲፕሎማሲ ስኬቶች የተገኙበት ነበር። ይህም ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ከሌሎች በርካታ ሀገራት ጋር የተከናወነውን የዲፕሎማሲ ሥራ በማንሳት ለውጡን ከገንዘብ ጀምሮ በሀሳብና በባለሙያዎች የደገፉበት እንደነበር ገልፀዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ይህንን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ለማስቀጠል የሚያስችሉ እና ወደ ከፍታ የሚያሸጋገሩ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ፅንፍ የያዙ የፖለቲካ ሀሳቦችን የሚያቀራርቡ መድረኮችን በመፍጠር የሃሳብ ልዩነትን የሚያስታርቅ እድልን ማመቻቸት አለባቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ