ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ጋር በተያያዘ ተከሰሰ

ከሟቾች ቤተሰቦች መካከል Image copyright Getty Images

በኢትዮጵያው አየር መንገድ አደጋ ህይወቱን ያጣ አንድ ግለሰብ ቤተሰቦች በአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ቦይንግ ላይ በአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ።

ከሁለት ሳምንት በፊት በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት 157 መንገደኞች በሙሉ በአዳጋው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ቦይንግ "ችግሩ ተፈቷል" እያለ ነው

"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

በአደጋው ህይወቱ ያለፈው ሩዋንዳዊ ግለሰብ ጃክሰን ሙሶኒ ዘመዶች በክሳቸው ላይ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በአውቶማቲክ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ላይ የዲዛይን ችግር አለበት ሲሉ አመልክተዋል።

ከአምስት ወራት በፊት ከተከሰከሰው ተመሳሳይ የኢንዶኔዢያ አውሮፕላን በኋላ በኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ አደጋው ሲደገም ቦይንግ 737 ማክስ የተባለው አይነት ስሪት ያላቸው አውሮፕላኖች በሙሉ ከበረራ ታግደዋል።

"አደጋውን ስሰማ ክው ነበር ያልኩት..." አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በቀረበበት ክስ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ረቡዕ እለት ቦይንግ ከአደጋዎቹ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው በአውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ላይ ያለው ችግር መፍትሄ እንደተበጀለት አስታውቋል።

የአደጋው መርማሪዎች ምክንያቱ ምን እንደሆነ ገና በምርመራ ላይ ናቸው።

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ የሚመረምሩ ባለሙያዎች የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ከአደጋው በፊት እንዲሰራ ተደርጎ እንደነበር በመጀመሪያ ደረጃ ውጤታቸው እንደደረሱበት ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

ስለ አደጋው እስካሁን የምናውቀው

ጋዜጣው ስማቸው ያልተገለጹ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ውጤቱ ትናንት ሐሙስ ለአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር በተሰጠ ማብራሪያ ወቅት መቅረቡ ተነግሯል።

የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ አውሮፕላኑ እንዳይቆም ለመከላከል የሚረዳ ነው።

ይህንን በተመለከተ ቦይንግ ምላሽ ካለው ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ስለአደጋው የሚደረገው ምርመራ ከመጠናቀቁ በፊት ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይሰጥ ገልጿል።

ጨምሮም ስለጉዳዩ ያሉ ጥያቄዎች በሙሉ መቅረብ ያለባቸው ምርመራውን እያደረጉ ላሉ ባለስልጣናት እንደሆነም ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ያወጣውን ዘገባ እንደተመለከተውና በቅርቡ ምላሸ እንደሚሰጥ ተናግሯል።