ዞማ ቤተ መዘክር ለአዲስ አበባ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስፍራ

መስከረምና ባልደረቦቿ በአትክልት ስፍራ ውስጥ Image copyright Meskerem Asegid

ዞማ ቤተ መዘክር የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ገደማ የተጠነሰሰው በመስከረም አሰግድ አዕምሮ ውስጥ ነበር። አሁን ዞማ የብዙዎች መዋያ፣ ነፍስ ማደሻ፣ ባህል እና ጥበብን መጠበቂያ እና ማስተዋወቂያ የሆነውም በእርሷና በባልደረባዋ ኤሊያስ ስሜ ጥረት ነው።

በዞማ ግቢ እግር ሲረግጥ ከመጀምሪያው እርምጃ አንስቶ ቦታው በዓይነቱ ለየት ያለ መሆኑን አለማስተዋል ይከብዳል።

እምቦጭ የጣና ቂርቆስ መነኮሳትን ከገዳሙ እያስለቀቀ ነው

ቤተ መዘክሩ የተገነባው በጭቃ መሆኑ ለየት ያደርገዋል። ጭድን ከጭቃ በመቀላቀል የእንጨት ማገሮቹ ላይ እየተወረወረ ግንብ በሚሰራበት ዘዴ መሆኑን የምታስረዳው መስከረም፤ ይህን የግንባታ ዘዴ በሃገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ለጉብኝት በሄደችባቸው ጊዜያት ማየቷን ትናገራለች።

ከታሪካዊ ግንባታዎቹ በተጨማሪ የሰው መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ጥበብ እጅግ ያስገርሟታል። በጉብኝቷ ወቅት ባለቤቶቹን ስታናግራቸው ከቅድመ አያት እስከ ቅም ቅም አያት ድረስ ወደ ኋላ የተገነቡ በመሆናቸው አብዛኛዎቹ ቤቶቹ እንዴትም ሆነ መቼ እንደተገነቡ አያስታውሱም ትላለች።

Image copyright Abel Tilahun
አጭር የምስል መግለጫ ኤልያስና መስከረም

ከሁሉም በላይ እንድትገረም ያደረጋት የባህላዊ ግንባታ ዘይቤዎቹ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሆነ ትውልድ ላይ መቅረታቸው ነው።

"የቤቶቹ ውበት ብቻ ሳይሆን ይህን ያህል ጊዜ የተለያየ የአየር ፀባይ ተቋቁመው መቆየታቸው በጣም ያስደንቀኝ ነበር። ለዚህም ነው የግንባታውን ዓይነት ለማወቅ እጓጓ የነበረው" የምትለው መስከረም፤ በማከልም ይህ የሃገር ቅርስ እየጠፋ ወይም እየተረሳ መምጣቱ ያሳሰባት እንደነበር ታስረዳለች።

መስከረም እነኚህን የጥንት የግንባታ ጥበቦች ከዘመናዊ የግንባታ ዘዴዎች ጋር በማዋሃድ እንዲቆዩ ማድረግ እንደሚቻል ያላትን እምነት ሳታመነታ አካፍላናለች።

ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

"በጣም ይቆጨኝ ነበርና የቤቶቹን የግንባታ ዘዴ ለሕዝብ የምናስተዋውቅበት አንደኛው መንገድ የእራሴን ቤት በዚያ መንገድ መሥራት አልነበረም … ምክንያቱም ከጓደኞቼ ውጪ ማንም ላያየው ስለሚችል" የምትለው መስከርም የግንባታ ዘይቤዎቹ በቅርስ መልኩ እንዲቆዩና ለመጪ ትውልዶች ማሳያ ብቻ ሳይሆን መማሪያም እንዲሆኑ በማሰብ ከሁለት አሥርት ዓመታት ጥረት በኋላ በዞማ ቤተ መዘክር መልክ ለሕዝብ መቅረብ መቻላቸውን አጫውታናለች።

Image copyright Anatoli Bulti

የዞማ አፀ

ከጭቃ የተገነቡትን ግድግዳዎች ተከትሎ በአንድ ጊዜ ለዓይን መለየት እስኪያቅቱ ድረስ የዛፍና የአበቦች ዓይነቶች በብዛት ይታያሉ።

የአባቷ እርሻ ላይ ያደገችው መስከረም፤ አስተዳደጓን መለስ ብላ ስታስታውስ ከእንሰሳትና ከተለያዩ ተክሎች ጋር እንደነበር ትናገራለች። የሥራ ባልደረባዋ ኤሊያስን በተመለከተም "እርሱም ቢሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ለዕፅዋት ልዩ ቦታ ነበረው። እስካሁን በሄደበት ሁሉ ባለው ቦታ ላይ ትንሽም ነገር ቢሆን ይተክላል" ትላለች።

ሁለቱም ለዕፅዋት ካላቸው ፍቅር ባሻገር ዞማን በተለያዩ ዕፀዋት መሸፈንና ለዕይታ የሚማርኩ ብቻ ሳይሆኑ ታይተው የማይታውቁ ለብዙ የጤና እክሎች ጠቃሚ ሊሆኑ ለሚችሉ ተክሎች ቦታ እንዲሰጡ የገፋፋቸው ሌላ ምክንያት እንዳለ ትናገራለች።

ካናዳን በጥበብ ሥራው ያስዋበው ኢትዮጵያዊ

"ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቅመማ ቅመሞች፣ ዛፎች፣ ተክሎችና ለመድሃኒትነት የሚጠቅሙ ብዙ እፆች እየጠፉ ነው" ስለዚህም በዋነኝነት የዞማ የተክል ስፍራ ለመጽሐፍትና ለሥዕል ብቻ ሳይሆን የእፅዋትም ቤተ መዘክር እንዲሆን ታስቦ መቋቋሙን አጫውታናለች።

ከሃገሪቱ በመጥፋት ላይ ያሉ ዛፎችና ተክሎችን መጎብኘት የሚቻልበት ስፍራ በመሆን የኢትዮጵያን የዕፅዋት ሃብት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፊያ መንገድ ነውም ትላለች።

ግቢው ውስጥ ያሉት ዕፀዋት በተተከሉበት ወቅት እነሱን ከመጠበቅ በላይ በጥበብ እንዴት አሳምሮ መትከል ይቻላል? የሚለው ላይ በማተኮር ለዓይን ማራኪ በሚሆን መልኩ የተተከሉ ናቸው።

ይህን በማድረጋቸውም ብዙ አዕዋፋትና ቢራቢሮዎች በዓይነት በዓይነት ዞማን ማረፊያቸው፤ እንደውም ቤታቸው እንዳደረጉት በደስታ ትናገራለች።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

ምንም እንኳን ዞማ ያረፈበት ግቢ ሰፊ ቢሆንም ወንዝ ዳር መገኘቱ አትክልቶቹ በሙሉ በቂ ውሃ እንዲያገኙ እንደረዳቸው ነግራናለች። የወንዝ ተዳፋት ላይ የሚገኘው የዞማ ግቢ የሰፈሩን ቆሻሻ በሙሉ ይዞ ወደ በግቢው ወዳለው የፍሳሽ መውረጃ መቀላቀሉ ትንሽ አስቸግሯቸው እንደነበር ታስታውሳለች።

ለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ወደ ዞማ ግቢ የሚገባውን ውሃ በማጣራትና በማፅዳት ወደ ወንዙ ሲቀላቀል "ለመጠጣት እራሱ የሚሆን ውሃ ማቅረብ ነው። ቢያንስ ከእኛ ግቢ የሚወጣው ውሃ ንፁህ ከሆነ ለጎረቤቶቻችንና ለሌሎቹ ምሳሌ በመሆን ሁሉንም ሰው ማበረታታት ይችላል" ትላለች።

Image copyright Benedetta Castrioto

መዋለ ሕፃናት የሆነው ቤተ መዘክር

በዕፀዋት ካጌተው አፀደ ወረድ ሲባል ወደ ወንዙ ሲጠጉ ደግሞ አነስ ያለ እርሻ፣ የዶሮ ማርቢያ፣ የፍየልና የላሞች ማደሪያም ይታያል። በቤተ መዘክሩ እነዚህ የግብርና ግብአቶች ለምን እንዳስፈለጉ መስከረም ስትናገር "ዋናው ለልጆቹ ተብሎ ነው" በማለት ታስረዳለች።

በቤተ መዘክሩ ውስጥ በከፈቱት መዋለ ሕፃናት ለሚማሩት ተማሪዎች የሆነበትም ምክንያት ልጆቹ ዶሮም ሆነ እንቁላል መገኛቸው ከመደብር እንዳልሆነ እንዲያውቁ መሆኑን ትናገራለች።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

"ዶሮዎቹን መጥተው ይንከባከባሉ፣ ጫጩት ሲወለድ ያያሉ፣ ጫጩት ይንከባከባሉ፣ እንቁላል ይለቅማሉ እንደውም ስም አውጥተውላቸው እያንዳንዳቸውን ይለይዋቸዋል። ይህ ደግሞ ዶሮና እንቁላል ከየት እንደሚመጡ ከማወቃቸውም በተጨማሪ ለዶሮዎቹ ፍቅር እንዲያዳብሩ ያደርጋል" ትላለች።

ልክ እንደ ዶሮዎቹ ላሞችና ፍየሎች በዞማ ግቢ ውስጥ ስላሉ ከተለያዩ እንስሳት ጋር ጥሩ ግንኙነት ከመፍጠሩም ባሻገር ተጨባጭና ተፈጥሯዊ መማሪያ እንደሚሆንላቸው ገልጻለች።

የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ትውስታዎች በኢትዮጵያውያን ዓይን

በተጨማሪም "ልጆቹ ምግብ ማብሰልም ጭምር ይማራሉ" የምትለው መስከረም፤ ህጻናቱ እግረ መንገዳቸውን ደግሞ ሂሳብ በሚታዩ ነገሮች እንዲማሩ በማሰብ ለምሳሌ "ድንች ተሰጥቷቸው ለሁለት ቢከፈል ስንት ይሆናል ሲባሉ በእራሳቸው እየቆጠሩ ሂሳብ ተማሩ ማለት ነው" ትላለች።

ዞማ ቤተ መዘክር፣ የሥነ ሥዕል ዓውደ ርዕይ ማሳያ፣ የተንቀሳቃሽ ምስል ማሳያ፣ መጽሕፍት ማንበቢያ፣ ሱቅ፣ ምግብ ቤት፣ የአፀደ ስፍራ፣ አፀደ ሕፃናት እና እርሻም ጭምር ነው።