ሕዝብ ስለመሪው ምን እንደሚያስብ እንዴት እንወቅ?

የተሰበሰበ ሕዝብና ግራፍ

በኢትዮጵያ የሕዝብ አስተያየት የሚሰፈርበት ዘመናዊ ቁና የለም። በመሆኑም ድምዳሜ ላይ የምንደርሰው በነሲብ ነው። ወይም ደግሞ ከአንዳንድ ኩነቶች በመነሳት…።

ለምሳሌ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በሚቀነቀን ጯኺ አጀንዳና ምላሹ…፤ ለምሳሌ ከተሳካ የመሪ ቃለ ምልልስ ወይም የመድረክ ላይ ንግግር። አንዳንድ ያልሰመሩ የመሪ ንግግሮች ፖለቲካዊ ጡዘት ያከራሉ፤ አንዳንድ የሰመሩ የመሪ ቃለ ምልልሶች ፖለቲካዊ ትኩሳትን ያበርዳሉ።

በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ዞሮ ዞሮ የመሪ ቅቡልነት በምን እንደሚመተር የሚያውቅ የለም። "ሕዝቡ'ኮ እያለን ያለው…" ብለው ዲስኩር የሚጀምሩ ፖለቲከኞች ግን እልፍ ናቸው…ፓርቲ ይቁጠራቸው። ሕዝቡን በምን ሰምተውት ይሆን?

ቀደም ባለው ጊዜ አውቶቡስና ውይይት ታክሲ ሳይቀር፣ የዕድርና ልቅሶ ድንኳኖችን ጨምሮ ሕዝብ ስለ መሪው እንዴት እያሰበ ነው ለሚለው ረቂቅ ጥያቄ ባህላዊ መስፈሪያዎች ነበሩ። በአያቶች ዘመን ደግሞ "እረኛ ምናለ?" ይባል ነበር፡፡ አሁንስ? የመሪዎቻችንን ተወዳጅነት የምንለካበት አገራዊ ማስመሪያ አለን? ስሙ ማን ይባላል?

"የበይነመረቧ ኢትዮጵያ"

ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራው አገር ከፌስቡክ እንደምትሰፋ እንዳንረዳ የጋረደን ምንድነው? አንዱ ምክንያት ሁነኛ የሕዝብ የልብ ትርታን መስፈሪያ (Opinion Poll) ማጣታችን ይሆን?

አቻ አገራዊ ቃል ያልተበጀለት "ፖሊንግ" ለምዕራቡ የቢሊዮን ዶላር ቢዝነስ ነው። የፖሊንግ ጥናት ማጠንጠኛ ሁልጊዜም አንድ ነገር ነው፤ "ሕዝብ ስለ አንድ ጉዳይ እንዴት ያስባል?" የሚል ምላሽ ማግኘት።

ይህ ዳሰሳዊ ጥናት ታዲያ ውጤቱ በዋዛ አይታይም። የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ያስቀይራል፣ ምርጫን ያጎናል፣ ምጣኔ ሀብትን ያዛንፋል፣ በጀት ያስቀይራል፣ ቁልፍ ወታደራዊና ወንዛዊ ጂኦ ፖለቲካን ያተረማምሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወታደሮቹ ድርጊት ተበሳጭተው እንደነበር ተናገሩ

በተቀረው ዓለም "ፖሊንግ" የመሪዎቻቸውን ቅቡልነት ብቻም ሳይሆን የመራጩን ሕዝበ-ልበ-ትርታ የሚለኩበት ስቴትስኮፓቸው ነው።

እኛ ያ የለንም። ሐሳብ ጠፍጥፈው ጋግረው ለገበያ በሚያቀርቡ ጥቂት የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ "ጄኔራሎች" ናቸው። በነርሱ ስፌት ልክ አገሪቱን እናያታለን። ስለዚህ ትጠብብናለች፤ ትፈርስብናለች። ከዚያ ተነስተን የእልቂት ነጋሪት የተጎሰመ ያህል እንሸበራለን።

አቶ ኢፌራ ጎሳ ምናልባትም ለዚህ "ፖሊንግ" ለሚባለው የዳሰሳ ጥናት ቅርብ ከሆኑ ኢትዮጵያዊን መካከል አንዱ ሳይሆኑ አይቀሩም። ለምን ቢባል ለ26 ዓመታት ማኅበራዊ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የሚታወቀውን ዋስ ኢንተርናሽናል ኩባንያን በምርምር ዳይሬክተርነት መርተዋል።

"ኢትዮጵያን መሬት ካልወረድን አናገኛትም" ሲሉ ይደመድማሉ። ለዚህ ድምዳሜ ያበቃቸው ታዲያ በጎ በጎውን ማየት ስለሚሹ ሳይሆን ደረቅ አሐዝ ነው።

"ንቁ የኢንተርኔት ተጠቃሚው እኮ ከሕዝቡ ሁለት በመቶም አይሞላም" ይላሉ። እንዴት ሆኖ?

"በተጨባጭ ስናወራ ቴሌ 50 ሚሊዮን ስልክ ተጠቃሚ አለ ብሎ ነበር። አሁን ወደ 30 ሚሊዮን አውርዶታል። ከዚያ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚ 20 በመቶው ነው። እኛ በተለያየ መንገድ ባደረግነው ጥናት ግን 10 ከመቶም አይሆንም። ከ10 ከመቶው ውስጥ በየጊዜው ኢንተርኔት የሚበረብር ንቁ (አክቲቭ) ተጠቃሚ 'የ10 ፐርሰንቱ 10 ፐርሰንት' ነው። በዚህ ስሌት ከሄድን እጅግ ትንሹ ቁጥር ላይ እንደርሳለን" ይላሉ አቶ ኢፌራ።

የፌስቡኳ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ማግኘት እንዴት ከባድ እንደሆነ ሲያስረዱም፣ "እኛ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በየገጠሩ ሄደን፣ በር አንኳኩተን 'ደህና አደራችሁ?' ብለን ቃለ መጠይቅ ስንሰራ ኢንተርኔት ላይ ያለችውን አስፈሪዋን ኢትዮጵያን አይደለም የምናገኘው።"

የዶክተር ዐብይ አሕመድ 'ፑሽ አፕ'

ሰው ፌስቡክ አካውንቱን ሳይሆን ጎረቤቱን ቢመለከት ይበልጥ ኢትዮጵያዊያንን ያውቃል።

ያም ሆኖ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፖለቲካዊ ትኩሳት የሚለካ ቴርሞሜትር እስከዛሬም የለንም። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቅቡልና ልንሰፍረው ይቸግረናል። ለምን ግን "ፖሊንግ" እስከዛሬ ሳይኖረን ቀረ?

Image copyright Getty Images

"ፖሊንግ ማካሄድ ወንጀል ነበር"

የዐቢይን አንድ ዓመት የሥልጣን ልደት አስመልክቶ አንዳንዶች "ፖሊንግ" የሚመስል ነገር አሰናድተው መጠይቅ ለማስሞላት ግላዊ ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል።

ሌሎች ደግሞ የጠቅላዩን የከፍታና የዝቅታ ነጥቦች በሰንጠረዥ አስፍረው ማኅበራዊ ሰሌዳዎች ላይ ሲለጥፉ ነበር። ይህ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ። አንድ አስፈላጊ ነገር ግን ሁሉም ሰው የረሳው ተቋም። የሕዝብ ልብ ትርታን የሚመትር የማኅበራዊ ጥናት ተቋም።

ዋስ ኢንተርናሽናል ለትልልቅ ዓለማቀፍ የጥናት ድርጅቶች ጭምር መረጃ የሚለቅም አገር በቀል ኩባንያ ነው። ከእውቁ ጋሎፕ ፖሊንግ ጋር በሽርክና ሠርቷል። ዋስ መሬት ላይ ወርዶ ዘርፈ ብዙ ጥናቶችን በማካሄድ የሁለት አስርታት ልምድ አለው።

በዚህ ሁሉ ዘመን ታዲያ የአቶ መለስንም ሆነ የአቶ ኃይለማርያምን ሕዝባዊ ቅቡልነትን ሰፍሮ አያውቅም። ለምን?

የዋስ ባለድርሻና ተመራማሪ አቶ ኢፌራ "ፖሊንግ (የሕዝብ ስሜት ዳሰሳ ጥናት) በኢትዮጵያ ክልክል ሆኖ ቆይቷል" ይላሉ። በመሆኑም ለረዥም ዓመታት ፖሊንግ በኢትጵያ እንደ ወንጀል ነበር የሚታየው።

የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

"እንኳንስ የአገር መሪን መስፈር (rate ማድረግ) ይቅርና ስለ ጤና ሽፋን ወይም ስለመልካም አስተዳደር የዳሰሳ ጥናት ለማድረግም የመንግሥት ፍቃድ ይጠየቃል።"

አቶ ኢፌራ ጨምረው እንደነገሩን የጥናት ኩባንያቸው ዋስ ኢንተርናሽናል ለእውቁ "ጋሎፕ ኢንተርናሽናል" በውክልና ማኅበረሰባዊ ጥናቶችን ሲያደርግ የመጠይቅ ወረቀቱ መዘርዝር ሳይቀር ሳንሱር ይደረግበት ነበር። ፖለቲካ ዘመም ጥያቄዎች ተለቅመው "እነዚህን ጥያቄዎች አውጡ እንባል ነበር" ይላሉ።

ፖሊንግ ምን ይፈይድልናል?

አንድ ፓርቲ ለሕዝብ ቃል ገብቶ ነው ምረጡኝ የሚለው። ምረጡኝ ለማለትም መራጩ ምን እንደሚፈልግ ማወቅን ይጠይቃል። ሕዝቡ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ባሻገር ምን እንደሚፈልግ እንዴት ማወቅ ይቻላል?

አንድ ፓርቲ ከተመረጠም በኋላ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑን ሳያውቀው ዓመታትን ሊያስቆጥር ይችላል። ጆሮ ለራሱ ባዳ አይደል? ይህን ለማስረዳት እንደ ኢህአዴግ ጥሩ ምሳሌ የለም።

በ97 ምርጫ ኢህአዴግ ምን ሰይጣን አሳስቶት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ እንደወሰነ ባይታወቅም አንዳንድ በድኅረ ምርጫው የተጻፉ መጣጥፎች ግን ፓርቲው ራሱን በሕዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተመራጩ ፓርቲ አድርጎ የማየት ዝንባሌ እንደነበረው የሚጠቁሙ ናቸው።

በምርጫው የደረሰበት ስብራት ዛሬም ደረስ ያልጠገገው ለዚያ ይሆናል። "ፖሊንግ" ቢኖር ምናልባትም ያ የዚያን ጊዜ እምነቱ አሸዋ ላይ የተገነባ እንደነበር የማወቅ ዕድል ይኖረው ነበር።

የመደመር ጉዞ ወደ አሜሪካ

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ 108 የደረሱት ፓርቲዎች ሕዝባቸው ምን እንደሚያስብ የሚያውቁበት መንገድ አለ ተብሎ አይገመትም። ስላንተ አንተ ከምታውቀው በላይ እናውቅልሀለን የሚሉበት እርግጠኝነት ግን አሳሳቢም አስፈሪም አደገኛም ነው።

"ያንተን ጉዳይ ላስፈጽም ነው ሥልጣን ላይ የወጣሁት የሚል መንግሥት፣ ጥያቄህን ለመመለስ ነው የምፎካከረው የሚል ፓርቲ የሕዝቡን የልብ ትርታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይለት ዳሰሳ ጥናት (ፖሊንግ) ሳያካሄድ እንዴት አውቅልሀለሁ ለማለት ይቻለዋል?" ሲሉ ተገርመው ይጠይቃሉ አቶ ኢፌራ።

የመጀመሪያዋ "ፖሊንግ"

26 ዓመት ዳሰሳ ጥናት ሲያደርግ የቆየው ዋስ፣ በዓመት በአማካይ ሰማንያ የጥናት ፕሮጀክቶችን የሚያካሄደው ዋስ፣ በዓመት ለመቶ 20 ሺህ ሰዎች መሬት ወርዶ መጠይቅ የሚያስሞላው ዋስ በዚህ ሁሉ የዕድሜ ዘመኑ "ፖሊንግ" የሠራው አንድ ጊዜ ነው። እርሱም የዐቢይን ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ባለፈው ግንቦት።

ፖሊንጉ እንዲሠራ ያዘዙት ራሳቸው ዐብይ አሕመድ ወይም መንግስታቸው ይሆኑ?

አቶ ኢፌራ ድርጅታቸው ነገሩን በራስ ተነሻነት እንዳደረገው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"በአጋጣሚ የሚዲያ ዳሰሳ ጥናት በ12 ከተሞች እያደረግን ነበር" በዚያውም ለምን በነዚሁ ለቃለ መጠይቅ በተመረጡ ናሙናዎች ላይ የዐቢይን የቅቡልነት ከፍና ዝቅ አንመትርም ብለው ተነሱ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በ100 የሥራ ቀናት የት የት ሄዱ? ምን ምን ሠሩ?

ሀሳባችን የነበረው አንድም ስለ ፖሊንግ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር፤ "በዚያ ላይ ለሌላ የሚዲያ ጥናት በተሰናዳ ሪሶርስ ስለነበር መጠይቁን ያደረግነው ብዙም ወጪ አላስወጣንም።"

ነገር ግን ያስነሳው አቧራ እግረ መንገድ የተሰራ ፖሊንግ አላስመሰለውም።

ብዙ ሰዎች ማናቹ እናንተ? ምን ቤት ናችሁ? ሲሉ የተቿቸው ነበሩ። "በዚያው መጠንም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ የእኛን ጥናት እንደ መነሻ ሲጠቀሙበት ነበር።"

በዚህ ዋልታን በረገጠና በሚፋጅ ፖለቲካ ውስጥ ፖሊንግ መስራት ፈታኝ አይሆንም ግን?

አቶ ኢፌራ እንደሚሉት አንድ የተማረ ሰው አንድን ሪሰርች ውጤቱን አይደለም የሚጠይቀው፤ ቀድሞ በምን መንገድ ተሰራ ብሎ ነው የሚጠይቀው። ገለልተኝነት፣ የናሙና መረጣ፣ የመዘርዝር ጥያቄዎች ቅንብር፣ ግልጽነትና ይዘት፣ ወደ ውጤት የተኬደበት ቀመር ለፖሊንግ መታመን ወሳኝ ግብአቶች ናቸው።

ፖሊንግ መቶ በመቶ ስለ አንድ ሕዝብ ፍላጎት እቅጩን ላያውቅ ይችላል። ሆኖም ሳዊንሳዊነቱን ጠብቆ ከተተገበረ ለእውነታው የቀረበ ነው። በፖሊንግ የተሰሩ የምርጫ ትንበያዎች ከአየር ሁኔታ ትንበያ ባልተናነሰ ሐቀኛ የሚሆኑትም ለዚያ ነው።

ሆኖም ይሄ ሕዝብ ቅኔ ነው። ንጉሡን "ሌባ" እያለ በቮልስዋገን የሸኘ፤ አቶ መለስን "አባይን የደፈረ" ከሚለው "ባንዲራን የደፈረ" እስከሚለው ዜጋ ድረስ ከል ለብሶ፣ አንቆለጳጵሶ የቀበረ፣ ያከበረ፤ ዓለም የመሰከረላቸውን አምባገነን "መንጌ ቆራጡ" እያለ የሚናፍቅ ሕዝብ ነው።

እንዲህ ሰምና ወርቅ ለሆነ ሕዝብ ‹‹ፖሊንግ›› ምን ያህል የልብ አውቃ እንደሚሆን ማንም አፉን ሞልቶ መናገር አይችል ይሆናል? ቢሆንም. . . !

ተያያዥ ርዕሶች