340 ሔክታር የሚሸፍነው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በእሳቱ ጉዳት ደርሶበታል

የተቃጠለው የፓርኩ ክፍል Image copyright AMMA

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሳንቃ በር፣ እሜት ይጎጎ እና ግጭ የተባሉት የፓርኩ ክፍሎች ከመጋቢት 19/2011 ዓ.ም አመሻሽ ጀምሮ እየተቃጠለ ይገኛል። ዛሬም እሳቱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር አለመዋሉንና አሁንም ጭስ እንደሚታይ የብሔራዊ ፓርኩ ዋና ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ኃላፊው በተለያዩ መገናኛ ብዙህንና በማህበራዊ ሚዲያዎች በአካባቢው በረዶ በመዝነቡ እሳቱ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱን በተመለከተ የተሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኃላፊው አክለውም እሳቱ ከተነሳበት የፓርኩ ክፍል በተቃራኒ ባለ ቦታ ትንሽ ካፊያና ደመና በመታየቱ እርሱ ወደ ቃጠሎው ቦታ ይመጣ ይሆናል በሚል ተስፋ የተሰራጨ መረጃ ሳይሆን እንደማይቀር ገልፀዋል።

አደጋ የተጋረጠበት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት

"እሳቱ እንደ አየር ፀባዩ እየተለዋወጠ ደመና ሲሆን የመቀዝቀዝ ፀሐይ ሲሆን ደግሞ ታፍኖ የቆየው እንደገና የመነሳት ሁኔታዎች ይታያሉ" ብለዋል አቶ አበባው።

በዚህም ምክንያት ስጋት መኖሩን ገልፀው ሰዎች የማይደርሱባቸው ቦታዎች አሁንም እሳት እንደሚታይ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከተለያዩ አካባቢዎች ግለሰቦችና የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው በማምራት እሳቱን በውሃና በቅጠል እንዲሁም በአፈር ለማጥፋት ቢሞክሩም በፓርኩ የመልከዓ ምድር አቀማማጥ የተነሳ መድረስ የማይቻልባቸው ቦታዎች ላይ ደርሰው ለማጥፋት አለመቻሉን አስረድተዋል።

እሳቱን ለማጥፋት ራቅ ካሉ ቦታዎች የሚመጡ ሰዎችም ቦታው ተራራማ በመሆኑ በድካምና በውሃ ጥም ተንገላተው ስለሚደርሱ በሚፈለገው መጠን የማጥፋት ሥራውን ለማከናወን አስቸጋሪ ሆኗል።

ጣና ሐይቅ የተጋረጡበት ፈተናዎች

በየዓመቱ እንዲህ ዓይነት የእሳት አደጋዎች እንደሚያጋጥም የሚናገሩት ኃላፊው የዘንድሮው ግን ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለና ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል። እስካሁን 340 ሔክታር የሚሸፍነው የፓርኩ ክፍል ውድመት እንደደረሰበት ለማወቅም ተችሏል።

ኃላፊው እንደገለፁት ቃጠሎው የደረሰባቸው ቦታዎች የምኒልክ ድኩላና ሌሎች ድኩላዎች እንዲሁም የቀይ ቀበሮና የተለያዩ የዱር እንስሳቶች የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ይሁን እንጂ ተሳቢ እንስሳት ካልሆኑ በስተቀር በእሳቱ ምክንያት በዱር እንስሳት ላይ ያጋጠመ ጉዳት እንደሌለ ገልፀውልናል።

Image copyright AMMA

በብሔራዊ ፓርኩ የሊማሊሞ ሎጂ ሥራ አስኪያጅና አስጎብኝ ሽፈራው አስራት በበኩሉ በአካባቢው ዝናብ አለመዝነቡን ጠቅሶ እዚያ አካባቢ ያለው ማሕበረሰብ በንቃት እየተከታተለና እየጠበቀ እንደሆነ ይናገራል።

"ዛሬ ያለው ሁኔታ የሚያሰጋ ቢሆንም እሳቱ ጠፋ ሲሉት እየተነሳ ስለሆነ፤ ለዕይታ ግልፅ ያልሆኑ ቦታዎች በመኖራቸው ጠፍቷል ብሎ መደምደም አይቻልም" የሚለው አቶ ሽፈራው ከ15 ቀናት በፊት የእርሱ መዝናኛ ቦታ የሚገኝበት የፓርኩ ክፍል ላይ እሳት ተነስቶ እንደነበር ያስታውሳል።

መዝናኛ ቦታው አሁን ቃጠሎ ካጋጠመው የፓርኩ ክፍል በ200 ሜትር ርቀት ላይ በመገኘቱ "በፓርኩ የሚገኙ እንስሳቶች ሲራወጡ ማየት በራሱ ያማል" ይላል።

የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ሊመለስ ነው

ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የዓለም ቅርስ እንጂ የአንድ አካባቢ ብቻ ሐብት አይደለም የሚለው ሽፈራው "አባቴ የፓርክ ሰራተኛ በመሆኑ ፓርኩን ከ25 ዓመታት በላይ አውቀዋለሁ፤ ፓርኩ ከተፅዕኖ ነፃ ሆኖ አያውቅም" ሲል ያክላል።

ለዚህም የህዝብ ብዛት መጨመር፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋት፣ የመንገድ ግንባታና ሌሎች ምክንያቶችን ይጠቅሳል።

እርሱ እንደሚለው ከዚህ ቀደም በዓለም የቅርስ መዝገብ ለአደጋ ከተጋለጡ ቦታዎች አንዱ ሆኗል ተብሎ ተመዝግቦ ነበር። ከዚያም በተደረገ ጥረት ከዝርዝር ሊወጣ እንደቻለ ያስታውሳል።

እንዲህ ዓይነት የእሳት አደጋዎችን የመቆጣጠር ኃላፊነት የማን ነው?

በቅርቡ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ አሁን በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰቱ የእሳት አደጋዎችን የማጥፋቱ ኃላፊነት ለሕዝብና ለፀጥታ ኃይሎች የተተወ ነው ያስብላል። ታዲያ በፌደራል ደረጃ እንዲህ አይነት አደጋዎችን የሚቆጣጠረው ማነው?

"በአንዳንድ የክልል ከተሞች የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤት ያለ ቢሆንም አቅማቸው ያን ያህል ጠንካራ አይደለም" ያሉን የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ናቸው።

አቶ ንጋቱ ጊዜው ትንሽ የራቀ ቢሆንም ከ15 ዓመታት በፊት በሻኪሶ ጥብቅ ደን እንዲሁም ፉኝዶ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን የእሳት አደጋ ያስታውሳሉ።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

"በወቅቱ የተፈጠረው የእሳት አደጋ ለ15 ቀናት የዘለቀ ነበር፤ በመሆኑም በአገር ውስጥ ባለው አቅም መቆጣጠር ስላልተቻለ ከደቡብ አፍሪካ እርዳታ ተጠይቆ በሔሊኮፕተር የታገዛ የማጥፋት ሥራ ተከናውኗል" ይላሉ።

አሁንም ግን በአገር ውስጥ እንዲህ ዓይነት የቱሪዝም ፓርኮችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ሌሎች ግዙፍ ህንፃዎችን ሊያጋጥማቸው ከሚችል የእሳት አደጋ ለመታደግ የሚያስችል አቅም እንደሌለ አበክረው ይናገራሉ -አቶ ንጋቱ።

"በቅርቡ የተገነባውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለ 54 ፎቅ ህንፃ ነው፤ ነገርግን ባለስልጣኑ 72 ሜትር የሚደርስ የህንፃ ቃጠሎ መቆጣጠር የሚችል መሳሪያ ነው ያለው። ይህም መሳሪያ ሊደርስ ሚችለው እስከ 23ኛው ፎቅ ድረስ ብቻ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ምንም እንኳን መስሪያ ቤታቸው ለአዲስ አበባ የተቋቋመ ቢሆንም ባሉት ችግሮች ሳቢያ ሌሎች አካባቢዎችም እየሄዱ አገልግሎት ለመስጠት መገደዳቸውን ይናገራሉ። "ብቸኛው የስልጠና ማዕከልና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው የእኛ ባለስልጣን ነው" ይላሉ።

የአዲስ አበባ ያህል ያደጉ የክልል ከተሞች ቢኖሩም የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ለመቆጣጠር አቅም እንደሌላቸውም ጨምረው ተናግረዋል።

ጨምረውም የመከላከል ሥራው ትኩረት የሚሰጠውና ቀዳሚ ቢሆንም በክልል ከተሞች ያለውን አቅም ማጠናከርና አገር አቀፍ አንድ ጠንካራ መስሪያ ቤት መቋቋም እንደሚያስፈልግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ