የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰማቸው?

የአየር መንገዱ ሰራተኞች ሲያለቅሱ Image copyright Getty Images

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢት 302 መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ጠዋት 2፡38 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ በጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተከስክሷል። በአደጋው የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ግለሰቦች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አደጋው በመላው ዓለም ድንጋጤን የፈጠረና ያሳዘነ ነበር። ታዲያ በረራ የዘወትር ሥራቸው ለሆነው የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰምቷቸው ነበር?

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የበረራ አስተናጋጅ ስለአደጋው የሰማችው ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር ተሰብስበው እየተጫወቱ እንደነበር ታስታውሳለች። ከዚያም ድንገት ስልኳ አቃጨለ "ተርፈሻል?" ለማለት ከጓደኛዋ የተደወለ ስልክ ነበር። የሰማችውም ያኔ ነው። " በፍፁም ላምን አልቻልኩም ነበር " ትላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሀዘን መግለጫ ሲያወጡ የሚወራው ሁሉ እርግጠኛ መሆኑን እንዳረጋገጠች ትናገራለች።

"እናቱ ስታየኝ 'ልጄ ያሬድ ይመጣል' እያለች ታለቅስ ነበር"- በናይሮቢ የካፒቴኑ ጸጉር አስተካካይ

ከዚያም በየተራ ሰው መደወል ጀመረ... ያኔ " እኔም ልሆን እችል ነበር ... ብዙ ጊዜ በማክስ አውሮፕላን እበራለሁ፤ በ20 ሰዓት ልዩነት ስለምንመደብም ልመደብ እችል ነበር" ስትል በሃዘኔታ አጋጣሚውን ታስታውሰዋለች።

"አደጋው ሁላችንንም ያስለቀሰ ነበር፤ እሞታለሁ ብለንም ስለማንወጣ በጣም ነበር ያዘንኩት፤ ለተሰጠን ሥራ 'እንደ ወታደር' እሽ ብለን ነው የምንሄደው" ስትል ታክላለች።

ያው የሥራ ጉዳይ ነውና ይህች የበረራ አስተናጋጅ አደጋው በተፈጠረ ዕለት ማታ ወደ ታይላንድ፣ ባንኮክ በረራ ነበራት። ይሁን እንጂ ቤተሰቦቿ እንዳትሄድ አጥብቀው ተማፅነዋት እንደነበር ታስታውሳለች። "እናቴም፣ አያቴም፣ ሁሉም ዛሬ ከቤት አትወጭም! እንደዚህ ሆኖ ይወጣል? ሰው ሞቱን ነው ወይ የሚፈልገው?" ሲሉ ከልክለዋት ነበር።

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

በጊዜው እርሷም ፍርሃትና ጭንቀት ገብቷት እንደነበር አልደበቀችም "ከበረራ በፊት ውይይት ስናደርግ ሕይወታቸው ያለፉት አስተናጋጆች ትዝ ይሉን ነበር፤ ድባቡ ያስጠላ ነበር፤ ከባድ ነበር ...እንቅልፍ ሁሉ ነስቶኝ ነበር" ትላለች።

"አደጋው ያጋጠመው አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስለነበር፤ እኛም ልክ አውሮፕላኑ ገና ሲነሳ ሁሉም እያለቀሰ ነበር፤ አገልግሎት መስጠት ተስኖን ነበር" ስትል ታስታውሰዋለች።

"ከበፊት ጀምሮ ከቤት ስወጣ ለእግዚያብሔር አደራ ሰጥቼ ነበር የምወጣው፤ አሁንም ይህንኑ ማድረግ የዘወትር ተግባሬ ነው" ትላለች።

ይህች የህግ ምሩቅ የሆነችው አስተናጋጅ ቤተሰቦች በአደጋው ምክንያት በስጋት መኖራቸው አልቀረም "አባቴ በተመረቅኩበት ትምህርት እንድሰራ ማስታወቂያዎችን እያየ 'ሞክሪ!... እስከመቼ ተሳቀን እንኖራለን' " ሲሉ ይወተውቷት ነበር። እርሷ ግን ሥራዋን አብዝታ ስለምትወደው የእነርሱን ውትዎታ ከቁብም አልቆጠረችው።

ሌላኛዋ ያነጋገርናት የበረራ አስተናጋጅ ለምለም ያደሳም የተለየ ሃሳብ የላትም። የአደጋው ዕለት በርካታ የስልክ ጥሪዎችን አስተናግዳለች። አንዳንዶቹ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው እያሉ ሲያበረታቷት ቤተሰብ ግን "ሥራውን ተይው" እስከማለት ደርሰው ነበር።

ይሁን እንጂ በማንኛውም ሥራ ላይ ሊያጋጥም የሚችል በመሆኑና ለሥራው ፍቅር ስላላት ለንግግራቸው ጆሮዋን አልሰጠችም።

"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

ከአደጋው ማግስት በረራ የነበራት ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ነበር። ቤተሰቦቿ ሲሸኟትም የውስጧን በውስጧ አድርጋ "አይዟችሁ ምንም አልሆንም፤ አታስቡ" የሚል መፅናኛ ቃል እንደሰጠቻቸው ታስታውሳለች።

"መጀመሪያ ስገባ በጣም ፈርቼ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት አደጋ ይፈጠራል ብለን አስበን ስለማናውቅ በጣም ተጨንቄ ነበር" የምትለው ለምለም ከዚያ በኋላ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት እንድትሰጥ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች።

"ብዙ ዓይነት አደጋዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ ከወትሮው በተለየ በትኩረትና በንቃት መከተታል ጀምሬያለሁ" ስትልም አክላለች።

የበረራ አስተናጋጇ ለምለም "ኢትዮጵያ አየር መንገድን ከመግባቴም በፊት እወደዋለሁ፤ አሁንም ከዚህ የተለየ ስሜት የለኝም፤ ሥራዬን እወደዋለሁ፤ እንዲህ ዓይነት አደጋ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሊያጋጥም ስለሚችል ሥራዬን ወድጄው፤ በአግባቡም እየሰራሁ ነው" ስትል ለቢቢሲ ስሜቷን አጋርታለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ