ቦይንግ የአደጋውን የምርመራ ውጤት ተቀበለ

ዴኒስ ሚሌንበርግ የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ Image copyright ቦይንግ
አጭር የምስል መግለጫ ዴኒስ ሚሌንበርግ የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ የቦይንግ ከፍተኛ ኃላፊዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫ ያወጡት ሁለቱ ከፍተኛ የቦይንግ ኃላፊዎች ዴኒስ ሚሌንበርግ የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበር፣ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የቦይንግ የመንገደኞች አውሮፕላን ፕሬዝደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ኬቪን ማካሊስተር ናቸው።

ዴኒስ ሚሌንበርግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች ምክንያት ለጠፋው የሰው ህይወት አዝነናል ብለዋል። የኩባንያው ሊቀመንበር '' . . . የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንዳሳየው እንደ ከዚህ ቀደሙ [ላየን ኤየር] ኤምካስ የተሰኘው ሶፍትዌር በተሳሳተ መረጃ 'አክቲቬትድ' (ሥራውን ጀምሯል) ሆኖ ነበር'' ብለዋል።

''አብራሪዎቹ ትክክለኛው መመሪያ ተከትለዋል''

''አደጋን ሊያስከትል የሚችል ሁኔታን የመቅረፍ ሥራ የእኛ ነው። አውሮፕላኑ የእኛ ስሪት ነው። እንዴት እንደሚስተካከልም የምናውቀው እኛው ነን። . . . ለኤምካስ ሶፍትዌር ማስተካከያ ከተደረገለት በኋላ 737 ማክስ አውሮፕላን ወደ በረራ ሲመለስ በበረራ ደህንነታቸው አስተማማኝ ከሆኑ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ ይሆናል'' ሲሉም ተደምጠዋል በቪዲዮ በተደገፈው መግለጫቸው።

የቦይንግ የመንገደኞች አውሮፕላን ፕሬዝደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ኬቪን ማካሊስተር በበኩላቸው ''የኢትዮጵያ የአደጋ መርማሪ ቡድን ላልተቋረጠው ትጋታቸው እናመሰግናቸዋለን። የበረራ ደህንነትን ለማረጋገጥ የአደጋው መንስዔ ምን እንደሆነ መረዳት ቁልፍ ጉዳይ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን በአጽንኦት ተመልክተን የአውሮፕላናችንን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን እንወስዳለን'' ብለዋል።

አደጋው የደረሰበት ቦይንግ 737 የገጠመው ምን ነበር ?

ኬቪን ማካሊስተር ጨምረውም ''በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ የበረራ መረጃ መቅጃው የያዘው መረጃ እንዳሳየው አውሮፕላኑ የተሳሳተ ማዕዘን ጠቋሚ (አንግለ ኦፍ አታክ ሴንሰር) ግብዓት ስለነበረው የደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ (ኤምካስ) ሥራውን እንዲያከናውን አድረጎታል" ሲል መግለጫው ኢቲ 302 ከኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይ አደጋ እንደገጠመው ገልጿል።

ቦይንግ ጨምሮም በተሳሳተ መረጃ ኤምካስ (ማኑቬሪንግ ክራክተሪስቲክስ ኦጉመንቴሽን ሲስተም) አክቲቬት እንዳይሆን የተሻሻለ ሶፍትዌር እያዘጋጀ እንደሆነ፣ ለአብራሪዎች ስልጠና እና 737 ማክስን በተመለከተ የሥልጠና ፕሮግራሞችን እየቀረጸ እንደሆነ ገልጿል።

የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ መውጣቱን ተከትሎ ቢቢሲ ካነጋገራቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ሳራ ቢረዳ "ሁኔታው ለኢትዮጵያውያን በጣም አሳዛኝ ነው። አሁን ስህተቱ የአየር መንገዱ እንዳልሆነ ተረድተናል። ይህ ዜና አስደሳች ነው ማለት ባልችልም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስም እና ዝና አስጠብቆ የሚያቆይ ነው። ችግሩ የሶፍትዌሩ መሆኑን እና አብራሪዎቹም አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር እንደሞከሩ አውቀናል" ብላለች።

አደጋው ስፍራ በየቀኑ እየሄዱ የሚያለቅሱት እናት ማን ናቸው?

ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እስራኤል ተፈራ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ለቢቢሲ ሰጥቷል። ''አብራሪዎቹ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ጀግኖች ናቸው። ችግሩ የአውሮፕላኑ ነው። አደጋው በጣም ቢያሳዝነኝም አሁን ባለው መረጃ ግን አብራሪዎቹ ጀግኖች ናቸው። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊደነቅ ይገባዋል። በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ መጽናናትን እመኛለሁ።''

የአደጋው መንስኤ ከአውሮፕላኑ የደህንነት መጠበቂያ ሥርዓት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መታወቁና የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ቦይንግም የምርመራውን ውጤት መቀበሉ ለኢትዮጵያ አየር መንገድም ትልቅ እፎይታ እንደሆነ የአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ