"ሐዘኑ አንደበቴን ሰብሮታል፤ አእምሮዬን አቃውሶታል" የካፒቴን ያሬድ አባት ዶ/ር ጌታቸው ተሰማ

ዶ/ር ጌታቸው ተሰማ የኢቲ 302 ዋና አብራሪ የነበረው ያሬድ ጌታቸው አባት

ዶ/ር ጌታቸው ተሰማ የሰማኒያ አመት አዛውንት ናቸው። የቢቢሲ ባልደረቦች ያገኟቸው ወቅት ከደረሰባቸው ሐዘን መፅናናት አቅቷቸው ፊታቸው ላይ በሚያሳብቅ ሁኔታ ስሜታቸው ተሰብሮ ነበር። እንዴት ነው አባት በረቱ? ተብለው ሲጠየቁም "ምርኩዜን ነው ያጣሁት" አሉ።

እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ጠዋት ላይ 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው አውሮፕላን ቢሾፍቱ አቅራቢያ ነበር የተከሰከሰው። ዜናውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትዊተር ገፃቸው ላይ ነው።

ሁኔታውም ብዙ ኢትዮጵያውያን ከማስደንገጥ በላይ ብዙዎችም አንብተዋል። ለመሆኑ አውሮፕላኑን በዋና አብራሪነት ሲያበር የነበረው ካፒቴን ያሬድ አባት ዶክተር ጌታቸው ተሰማ የሰሙበትን ቅፅበት እንዴት ያስታውሱታል?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ባለቤቴ ደወለችልኝ። ያሬድ እመጣለሁ ብሎ ደውሎልኝ ነበር፣ እስካሁን ግን አልደረሰም። የሰማኸው ነገር አለወይ አለችኝ። የሰማሁት ነገር የለም ብያት ወደ አየር መንገዱ ደወልኩ። መጀመሪያ ላይ ሊነግሩኝ አልፈለጉም። በኋላ ግን ሊደበቅ የሚችል ነገር ስላልሆነ የደረሰውን አደጋ ነገሩኝ። ለባለቤቴም ነገርኳት። እና ጠዋት ወደ አራት ሰዓት ግድም ነው የሰማሁት አደጋውን እንደሰማሁ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። አፋፍሰው ሆስፒታል ወሰዱኝ። ስነቃ በሆስፒታል አልጋ ላይ ኦክስጂን ተሰክቶልኝ ነው የነቃሁት።

ከአደጋው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኛችሁት መቼ ነበር?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ከሶስት ቀን በፊት ይሆናል። ብዙ ጊዜ ሲመለስ ነው የሚደውልልኝ። አንዳንድ ጊዜም ጠዋት ሲሄድ ይደውልልኛል። አንድ ወይም ሁለት ቀን ካለው ደግሞ አዳማ ያለው ቤቴ መጥቶ ይጎበኘኛል። ታዛዥ እና ቅን ልጅ ነበር። ሌሎችም ልጆች አሉኝ። ያሬድን የሚተካ ግን አንድም የለም። አንዳንድ ጊዜ አዲስ አበባ ሄጄ ያመሸሁ እንደሆን እርሱ ቤት አድራለሁ። ማለዳ ስነሳ የሚንከባከበኝ እርሱ ነበር። ብዙ ልጆች ቢኖሩኝም ብዙዎቹ ውጪ ስለሆኑ በሀሳብ፣ በመግባባት ቀረብ ያለኝ እርሱ ነው። ሐዘኑ አንደበቴን ሰብሮታል። አእምሮዬን አቃውሶታል። የሆነ ሆኖ ሞቱ በሀገር ደረጃ ስለሆነ ኩራትም ክብርም ይሰማኛል። ዛሬ ጊዜ ሞት ሰበቡ ብዙ ነው።

ያሬድ ለመሆኑ ምን አይነት ልጅ ነበር?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ስፖርት ወዳድ ነበር። በተለይ በዋና በርከት ያሉ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበረው ስሜትና ፍላጎት በአጠቃላይ ስፖርት ነበር። እያደገ ሲሄድ ከመሰናዶ በኋላ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ይናገር ጀመር። እኔም እናቱም በሕክምና ዘርፍ ውስጥ ስላለን፤ ቢያንስ ያሉኝን መፅኃፍት የሚያነብልን ስለምፈልግ፤ ወደ እኔ ወይም ወደ እናትህ ሙያ ብትመጣ ደስ ይለኛል ብለው እርሱ ግን የምትችሉ ከሆነ ፓይለትነት ብታስተምሩኝ ፍላጎቴ እርሱ ነው የሚል ሀሳብ አቀረበ። እንግዲህ ስሜት ካለህ አንከለክልህም በማለት ፍላጎቱን ተቀበልን።

አውሮፕላኑ 'ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር'

የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰማቸው?

መጀመሪያ ፍላጎታችን ደቡብ አፍሪካ ሄዶ እንዲማር ነበር። በኋላ ላይ ግን፤ ለኔም ወደ ሀገሬ መመላለሻ ምክንያት እንዲሆነኝ በማሰብም፤ ኢትዮጵያ ሄዶ እንዲማር የሚል ሀሳብ ለባለቤቴ አቀረብኩላት። የአየር መንገዱ ትምህርት ቤት የታወቀ እና በርካታ ኢትዮጵያውያንንና አፍሪካውያንን ያፈራ ስለሆነ እዚያ ሄዶ እንዲማር ፍላጎቴ ነበር።

ሌላው ልጆቼ በሙሉ የሚኖሩት ውጪ ሀገር ነው። አንድ ልጅ እንኳን በአስራት ደረጃ ወደ ሀገር ይመለስ በማለት ከቤተሰቡ ጋር ከተወያየን በኋላ ስለተስማማን አዲስ አበባ ሄዶ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ተማረ።

ስንት ልጆች አለዎት?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ስድስት

ያሬድ ስንተኛ ልጅዎ ነው?

ዶ/ር ጌታቸውአምስት

Image copyright Hassan Katende/Facebook

አብራሪ ለመሆን ለምን ፍላጎት እንዳደረበት አጫውቶዎት ያውቃል?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ልጆቼ ሁሉ የሚሉት እንዳንተ ሐኪም እንሆናለን ነበር። ሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ሀሳባቸውን እየቀየሩ መጡ። እርሱም ሁለተኛ ደረጃ ላይ እያለ ነው ሀሳቡን የቀየረው። ይመስለኛል በትምህርት ቤታቸው የቀድሞ ተማሪዎች ፓይለት ሆነው እየመጡ ንግግር ያደርጋሉ። እርሱም መሰናዶ እየተማረ እያለ ፍላጎት አደረበት። እኛም አልከለከልነውም።

አደጋው ስፍራ በየቀኑ እየሄዱ የሚያለቅሱት እናት ማን ናቸው?

ስለሚያበረው አውሮላን ዘመናዊነት አጫውቶዎ ያውቃል?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ብዙ አውሮፕላኖችን በረዳትነት ጭምር አብሯል። ድሪም ላይነር እና ሌሎች ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ጨምሮ። የተለያየ ሀገራትም በሯል። በስራው ደስተኛ ነበር። ፍላጎትም ጭምር ነበረው። መብረር ብቻ ሳይሆን በስራው የተሻለ ለመሆን ጥረት ያደርግ ነበር። በእረፍት ጊዜው ያነብ ነበር። ወደ አሜሪካም በራሱ በመሄድ የንግድ አውሮፕላን ማብረር የሚያስችለው ስልጠና ሁለት ጊዜ ወስዷል። ምስክር ወረቀትም አግኝቷል። በእድሜው ምንም እንኳ ትልቅ ሰው ባይሆንም በስራው ከፍ ያለ ግምትና አስተሳሰብ የነበረው ልጅ ነበር።

እንደነገሩኝ በርካታ ስልጠና ወስዷል። አደጋው ከደረሰ በኋላ የአብራሪዎቹ ጥፋት ይሆን የሚል ትንሽ ጥርጣሬ አላደረብዎትም?

ዶ/ር ጌታቸው፡ አላደረብኝም። ምክንያቱም እነደነገረን አብዛኞቹ አውሮፕላኖች ዘመናዊ ናቸው። አንድ ጊዜ ግን ምን ብሎኛል..'በዚህ አውሮፕላን ስንሄድ ስንሰራ አንዳንድ ጊዜ ችግር ይታያል' ሲል በትንሹ ነግሮኛል። ግን የትኛው እንደሆነ አላውቅም። ብዙ ቅሬታ አያቀርብም። በወር ውስጥ በርካታ ሰዓታትም ይሰራ ነበር።

በአደጋው ቦይንግን ይወቅሳሉ?

ዶ/ር ጌታቸው፡ አዎ፤ በጣም፤ ምክንያቱም ስለምን በኢንዶኔዢያ ከደረሰው አደጋ በኋላ ይህ አውሮፕላን እንዳይበር አላደረጉም። ስለምን እንዲበር ፈቀዱ? ምክንያታቸው ከሌላ አምራቾች ጋር ያላቸው ውድድር ሊሆን ይችላል። ብዙ መሸጥ ፈልገውም ይሆናል። በአንዳንድ ያደጉ ሀገራት ክቡር የሰው ልጅ ዋጋ የለውም። በአውሮፕላኑ ላይ ተገቢው መሳሪያ ባለመገጠሙ ልጄን አጥቻለሁ። ለዚህ ደግሞ መሪር ሀዘን ተሰምቶኛል። ነገር ግን በስራው ላይ እያለ ነው የተሰዋው። ያ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስታውሰው ይሆናል። ለዚህ ነው ሀገር ሁሉ ጀግና ሲለው የምትሰማው። የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

እቅዱን አጫውቶዎት ያውቃል?

ዶ/ር ጌታቸው፡ አዎ

ምን አለዎት?

ዶ/ር ጌታቸው፡ እጮኛ ነበረችው። እርሷም ካፒቴን ናት። በሚቀጥለው አመት ትዳር ለመመስረት እቅድ ነበራቸው። እኔም አዲስ አበባ ቤት ስላለን ያንን ቤት መኖሪያ እንደሚያደርጉ ቃል ገብቼለት ነበር።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላለቶቹ አውሮፕላኑ እንዳከሰከስ የተቻላቸውን ማድረጋቸውን ጠቅሷል። እርስዎ እንደአባት ህንን ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ኩራት ነው ያደረብኝ። መስሪያ ቤቱም የፖለቲካ ግፊት ሳያድርበት ትክክለኛውን ነገር በማድረጋቸው አመሰግናቸዋለሁ። ከዚህ በፊት ሊባኖስ ላይ የደረሰው ተልከስክሶ ነው የቀረው። በአሁኑ ሰዓት ግን የደረሰው ሁኔታ በገለልተኞች ተጠንቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአለም በማቅረባቸው ትልቅ ምስጋና አቀርባለሁ።

አየር መንገዱም እንኮራባቸዋለን በማለቱ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሌላውም አለም ምሳሌ ነው ብዬ አስባለሁ። የተሰጠው ምስክርነት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት በአየር መንገዱ ወደፊት ፓይለት ለመሆን ፍላጎት ላለው ወጣት ሁሉ ትልቅ ምሳሌ ነው ብዬ ነው የማምነው።

የቦይንግ አምራች የሆነው ኩባንያ በአደጋው ማዘኑን ገልፆ ይቅርታ ጠይቋል። ከቦይንግ የተሰማው ይቅርታ በቂ ነው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ከዚህ በፊት ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶችን ስከታተል ነበር። በጋዜጦች የሚሰጡትንም ጨምሮ። ያበረሩበትን ሰአት ጨምሮ አስቀያሚ አስተያየቶች ይሰጡ ነበር። ይህ ከባድ ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው። ያሬድ ከ8 ሺህ ሰአቶች በላይ በሯል። ረዳት አብራሪውም እንደዛው። ሁለቱም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል። ቦይንግ ግን በርካታ የፈጠራ ታሪኮችን ይነግረን ነበር። ራሳቸውን መከላከል እንደፈለጉ ይገባኛል። እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ትንንሾቹን መደቆስ ይፈልጋሉ። አሁን እውነቱ ወጥቷል። እነርሱም ይቅርታ ጠይቀዋል። ነገር ግን በጣም የዘገየና እዚህ ግባ የማይባል ነው።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በካሳ ክፍ በኩል ያናገራችሁ አለ?

ዶ/ር ጌታቸው፡ እስካሁን ድረስ የተደረጉትን ያስረዱኛል። ነገሩ ተጀምሯል ወደፊት እየተጣራ ሲሄድ ያለውን ነገር እናሳውቅሀለን ብለውኛል።

በአሜሪካ ቦንግን የከሰሱ አሉ። ኬንያውንም ቦንግንና ኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚከሱ ተሰምቷል። እርስዎ ህ ሀሳብ አለዎት?

ዶ/ር ጌታቸው፡ ሬሳ ባለበት አሞራ ይበዛል ነው የአሜሪካኖቹ ነገር። አሜሪካውያን ጠበቆች እዚህ ናይሮቢ ድረስም መጥተዋል። ኢትዮጵያም ሄደዋል። ለእኔም በማግስቱ ነው የደወሉልኝ። በጣም ነው ቅር ያለኝ። አርባው እስኪወጣ፣ የእኛም እንባችን እስኪደርቅ ድረስ መታገስ ማንን ገደለ? ግን አሜሪካኖቹ የእኛ ስሜትና አስተሳሰብ የላቸውም። እኔ አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያኖቹ የምለው ሰብሰብ ብሎ በአንድነት መነጋገር ጥቅም ይኖረዋል ነው የምለው። አንደኛ ተሰሚነት ይኖረዋል። የጠበቆቹም ኮሚሽንም ይቀንሳል። ስለዚህ መሰባሰቡ ክፋት አለው አልልም።

እስካሁን ግ ክስ ለመመስረት አላሰቡም?

ዶ/ር ጌታቸው፡ አላሰብኩበትም። ካናዳ ጠበቃ የሆነ ልጅ አለኝ። አሜሪካም ፈቃድ አለው። እርሱም እየደወለ አንዳንድ ነገሮችን ይጠይቀኛል። እስካሁን ነገሩን እናስብበት የሚል ነገር ላይ ነኝ።

ኢትዮጵያ መንግት በቋሚነት ማሰቢያ ቢያቆምላቸው የሚል ሀሳብ ተሰምቶዎት ያውቃል?

ዶ/ር ጌታቸው፡ እነዚህ ፓይለቶች ሳይሆንላቸው ቀረ እንጂ አውሮፕላኑን ለማትረፍ የተቻላቸውን ሁሉ ሙከራ አድርገዋል። መቼም ለሀገር በጦርነት ዘመን ብቻ ሳይሆን በሰላሙ ጊዜም መስዋዕት ይቀርባል። ስለዚህ ይህ መስዋዕት ለመጪው ትውልድ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስታወሻ እንዲሆን የረገፉበት ቦታ አንድ ሀውልት ወይንም መቃብር ስፍራ ቢሰራ እና መጪው ትውልድ ያለፈው ትውልድ ምን እንዳበረከተ እንዲያውቀው ቢደረግ ደስተኛ ነኝ። ይህንን ነው የምለው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ