በሰሜን ሸዋ በተከሰተ ግጭት ህይወት ጠፍቷል ንብረት ወድሟል

የኢትዮጵያ ካርታ

ቅዳሜና እሁድ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመ ግጭት ሰዎች መሞታቸውንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።

በባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ተከስቶ ውጥረት ቅዳሜ እለት ተቀሰቅሶ እሁድም በቀጠለው ግጭት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት መጥፋቱንና በርካቶች መቁሰላቸውን የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

አወዛጋቢው ግጭት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር

ከንቲባው ጨምረውም በግጭቱ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸውንና የዘረፋ ድርጊትም ተከስቶ እንደነበር ተናግረው ክስተቱ ከክልሉ ልዩ ኃይል አቅም በላይ በመሆኑ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እንዲገባ መደረጉንም አመልክተዋል።

ግጭቱ ከአጣዬ ባሻገር በካራቆሬ፣ በማጀቴና በዙሪያቸው ባሉ አካባቢዎች መከሰቱን የተናገሩት ነዋሪዎች በቡድን የተደራጁ ታጣቂዎች በድርጊቱ ተሳታፊ እነደሆኑም ተናግረዋል።

በጥቃቱ በሰው ህይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር "በቤተ እምነቶች፣ በግለሰብ መኖሪያና በንግድ ተቋማት ላይ" ጥቃት መፈጸሙን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአፋር ክልል በተፈጸመ ጥቃት የሰው ህይወት መጥፋቱ ተሰማ

የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ምክትል ኅላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ እንደተናገሩት ከእሁድ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢዎቹ በመግባታቸው ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን ተናግረዋል።

ኅላፊው የፀጥታ ጨምረውም በተደራጀ ሁኔታ በመታጠቅ የሕዝብን ሰላም እያደፈረሰ ያለውን ቡድን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በየአካባቢው በሚገኙ የጤና ተቋማት ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸውንም ወደሌሎች አካባቢዎች እንደተወሰዱ ተገልጿል።

የዐቢይ ለውጥ፡ በመስቀለኛ መንገድ ላይ?

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እሁድ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ባጋጠሙ ግጭቶች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የግጭቱን ምክንያት እና ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችን በተመለከተ በማጣራት ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ አመራሮች ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር እየሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች