የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመደመር እሳቤ ከአንድ ዓመት በኋላ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ Image copyright Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት አንደኛ ዓመት ከመከበሩ ቀደም ብሎ በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሲዘዋወር የነበረና አፈትልኮ ወጣ የተባለው ቪዲዮ እንደሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትም 'መደመር' የሚለው ቃል ከአንደበታቸው የማይይለይ እንደነበር ያሳያል።

ብዙዎቹ "ለመተቸትም ለመደገፍም ጽንሰ ሃሳቡ ግልጽ ተደርጎ ተተንትኖ አልወጣም" የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን መንበረ ስልጣኑ ከተቆጣጠሩ ጊዜ ጀምሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ቃል ደጋግመው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

በስልጣን ላይ አንድ ዓመታቸውን የደፈኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ከአንዳንድ ወገኖች አድናቆትን ከሌሎች ደግሞ ነቀፌታን እያስተናገዱ ይገኛሉ። የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆነው በርካታ እርምጃዎች የወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቆየው የግንባሩ አመራር የተለየ የሚመስል አቋም ሲያራምዱ ይስተዋላሉ።

በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ከቆየው የኢህአዴግ አስተዳደር ከሚለዩባቸው መካከል የሚጠቀሙባቸው ቃላቶችና አገላለጾች አንዱ ነው። ዶ/ር አብይ ግን ከእነዚህ በብዙዎቹ 'የተሰለቹ' ከሚባሉ ቃላት ርቀው 'መደመር' የሚለው ቃል ዘወትር ከንግግራቸው መካከል የማይጠፋ ሆኗል።

ለመሆኑ ይሄ ጽንሰ ሃሳብ በውል ሙሉ ትርጉም አግኝቷል ማለት ይቻላልን? የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችስ እንዴት ይረዱታል?

መደመር. . . መደመር. . .

አቶ አንዱአለም አራጌ በርከት ላሉ ዓመታት በእስር ቆይተው ባለፈው ዓመት መፈታታቸው የሚታወስ ነው። በቅርቡ በዜግነት ፖለቲካ የተሰባሰቡ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብሳቢ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመር ሲሉ 'በምንድነው' የሚገለጸው የሚለውን ግልጽ ማድረግ እንደነበረባቸው ይናገራል።

"እንደተቃዋሚ የምንደመረው በምንድነው? የማንደመረውስ በምንድን ነው? የሚለው ግልጽ አይደለም" በማለት ሙሉ ለሙሉ ሊደመሩ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

"አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሰባሰብ እና ኢትዮጵያን ከጭቆና ዘመን ነጻ የማውጣት እንቅስቃሴ ካለ እንደምንተባበር ይታወቃል።"

ብዙዎችን ከእስር መፍታት፣ በውጭ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ወደ አገር ቤት ገብተው እንዲታገሉ መፍቀድና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝቅ ብሎ ከዜጎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆንና ለመሳሰሉት እርምጃችዎቻቸው ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡታል። ከእነዚህ ውጪ ግን ይላሉ " እሳቸው መደመር መደመር ቢሉም መሬት ላይ የሚታው ነገር ግን ሌላ ነው" ይላሉ።

"ሰው በማንነቱ እና በሚናገርበት ቋንቋ ተፈርጆ የሚገደልበት፣ የሚገለልበትና የሚፈናቀልበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። ህዝቡ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ በትክክል የተረዳው አይመስለኝም። እንደፍላጎታቸው መጠን መሬት ላይ ወርዷል ብየ አልወስድም" ሲሉ ይናገራሉ።

"እንደ ህመም ማስታገሻ"

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት የአገሪቱ ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የነበረበት ዘመን ነው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የነበሩ ሲሆን ኢህአዴግም እንደ ድርጅት የመፍረስ አደጋ አጥልቶበት ነበር።

የሕግ ባለሙያዋ ህሊና ብርሃኑ ጠቅላይ ሚንሰትሩ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ይህንን የመደመር ሃሳብ ይዘው መምጣታቸው ሁኔታዎችን ለመቀዝቀዝና ነገሮችን ለማብረድ ረድቷል የሚል እምነት አላት። "ለግዜው የመደመር ሃሳብ አስፈላጊ ነበር" የምትለው ህሊና ሃሳቡ "ለግዜው እንደ ህመም ማስታገሻ" ትገነዘበዋለች።

''በወቅቱ በጣም ብዙ ችግሮቻችን ጫፍ ደርሰው የነበረበት በመሆኑ፤ እንደ አገር ወዴት እየሄድን ነው የሚለው ጉዳይ በጣም አጠያያቂ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር" ትላለች።

የጠቅላይ ሚንስትሩን የአንድ ዓመት የስልጣን ዘመን እንዴት ይመዝኑታል?

"ጉዳዩ የፖለቲካ ውስብስብነት የሌለበት፣ ለማንኛውም ማህበረሰብ በቀላሉ በሚገባ መልኩ እንደ ማስታገሻ ወስደነዋል።" ይሁን እንጂ ጽንሰ ሃሳቡ ከማስታገሻነት አልፎ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ሊያሻግረን አልቻለም የሚል አቋም አላት። "ከጊዜያዊ ማስታገሻነት ግልጽ ወደሆነ በየቀኑ ሊገባን ወደሚችለው መልስ መምጣት ነበረበት። ወደ መሬት ሊወርድ ይገነባ ነበር።"

ህሊና ሃሳቡ ግልጽነት ይጎለዋል ትላለች። "ማንም መጥቶ መደመር ማለት ይሄነው እያለ ለራሱ በሚጠቅም መልኩ ጠምዝዞ እንዳይጠቀምበት ግልጽ ሆኖ መቀመጥ ነበረበት'' ትላለች።

መደመር-ለኤርትራውያን ?

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ሃሳብ በውጭ ግንኙነት እንቅስቃስያቸው ዙርያም ተደጋግሞ ይነሳል። እስከ የዳቮሱ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተውታል።

የተለያዩ ጥያቄዎች የሚነሱበትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬቶች እንደ አንዱ የሚወሰደው የኢትዮ ኤርትራ ዕርቅ ላይም ይኸው ሃሳብ በተደጋጋሚ ተነስቷል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስም "ይሄ ህዝብ ሁለት ህዝብ ነው ብሎ የሚያምን ታሪክን ያልተረዳ ብቻ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ጽንሰ ሃሳቡ በግልጽ ካለመቀመጡ የተነሳ በኤርትራውያን ዘንድም ጥርጣሬን እንደፈጠረ አንዳንዶች ይናገራሉ። የተቃውሞ ደብዳቤም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የጻፉ ኤርትራዊያንም አልጠፉም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲስ ምዕራፍ

በስዊድን ነዋሪ የሆነው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ካሊድ አብዱ "መደመር ለእኛ ለኤርትራዊያን ትልቅ ስጋት ነው" ብሏል ለቢቢሲ። "መደመር የሚለው ሃሳብ ኢሳያስ ኤርትራን አሳልፎ እየሰጣት ነው። ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ሊያደርጋት ነው" የሚል ስሜት እንደፈጠረ ይናገራል።

"የኤርትራ ህዝብ ስለ መደመር ያሰማው ድምጽ የለም። አንድ ግለሰብ ብቻ እየወሰነ ነው።የኤርትራ ህዝብ የሚቀበለው ጉዳይ ግን አይደለም" ይላል።

መደመር-ትናንትና ዛሬ

መደመር የሚለው ሃሳብ ሲጀመር ችግር ያለው እንዳልሆነ ፋሲል ተስፋዬ ይናገራል። በወቅቱ የገባቸውም ያልገባቸውም እንደተደመሩበት ይገልጻል። ለእሱ መደመር "አንድ መሆን" ነው።

ይሁን እንጂ በማህበራዊ ሚድያ ላይ ከአንድ ዓመት በኋላ የተለየ አቋም ሲያንጸባርቁ ከታዩት መካከል አንዱ ነው። የዛሬ ዓመት ለውጡ ሲጀመር የነበረው ስሜት 'ዛሬ በውስጤ የለም' ይላል።

'መደመር' የሚለው ቃልም ከጨመረው ይልቅ ያጎደለው ጎልቶ እንደሚታየው ይናገራል።

ጽንሰ ሃሳቡ- የተወሰነ ወገን ጠቅሞ ከሆነ እንጂ ሁሉም ህብረተሰብ ሲጓጓና ሲጠብቅ የነበረው ሁኔታ ያሰገኘ ነው የሚል እምነት እንደሌለው ያምናል።

"ከዚያ ይልቅ ጥርጣሬ፣ የእርስ በርስ አለመተማመንና ወደር የሌለው ስግብግብነት ነግሷል" የሚል ግምገማ ነው ያለው።

"ሰዉ ነገን በስጋት እንዲመለከት አድርጎታል" ይላል።

"ችግሩ ግን መደመሩ ላይ አይደለም፤ እሳቤውም አይደለም። ወይም ደግሞ ህዝቡ በዚያ መንፈስ መቀላቀሉ አይደለም። ይህንን አስተሳሰብ ወደፊት አምጥተው ህዝቡ በዚህ ዙርያ እንዲሰበሰብ ያደረጉ ኃይሎች፤ በትክክል እንድንጠቀምበት አልቀረጹልንም። አስተሳሰቡን ተግባራዊ አድርገው እየመሩንም አይደለም" በማለት ይነቅፋል።

አዲስ ሃሳብ ነውን?

አቶ አንዱአለም አራጌ ቀደሞ ሲል በአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል ሆነው ሲታገሉ ነበር። እሳቸው እንደሚሉት መደመር የሚለው ጽንሰ ሃሰብ ድርጅታቸው ስለአንድነትና አብሮነት ሲያቀነቅንና በአቋም ደረጃም የኢትዮጵያ አንድነትን የማስቀደም አዝማሚያ እንደነበረው ይናገራሉ።

ለብዙ ዘመናት የአንድነት የዜግነት ፖለቲካ ማራመዳቸውን ጠቅሰው መደመር የሚለው ለእነሱ አዲስ ሃሳብ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ።

በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መምህራንን ሰብስበው ሲያነጋግሩ "መደመር ምን ማለት ነው?" የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ "እሱ የምሁራን ሥራ ነው፤ እናንተ ተመራመሩበት" ማለታቸውን ያስታውሳሉ። "ሃሳቡን የመተርጎምና የማርቀቅ ተግባር የጉዳዩ አምጪ ሥራ ነው" ይላሉ።

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

የሥነ አዕምሮ ሃኪምና በአነቃቂ ንግግራቸው የሚታወቁ ዶክተር ምህረት ደበበ "መደመር አዲስ ሃሳብ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አዲስ አቅጣጫ (ፓራዳይም) ነው" በማለት ይገልጹታል።

በኢትዮጵያ ባለፈው 50 ዓመት በመከፋፈልና በዘር እይታ በዙ ልዩነት ተፈጥሮ የእርስ በርስ ጦርነት መካሄዱ አስታውሰው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተግባር ላይ ከዋለ አዲስ የአመለካከት ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነ ይናገራሉ። "በተፈጥሮም ውስጥ አብሮ ያለ ነገር ነው አዲስ ልንለው አንችልም" ይላሉ።

የተደመረና ያልተደመረ

አቶ ናሁሰናይ መደመርና አለመደመር ጠላትና ወዳጅ ለመለያ፤ ተደመረ ያልተደመረ እየተባለ ለማጥቃት ጥቅም ላይ ውሏል ይላሉ።

"ምን ማለት እንደሆነ አይታወቅም። ተደመርክ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚሉት ማጨብጨብ ነው፤ አለመደመር ማለት ደግሞ ተጠራጠርክ ወይም ተቃዋሚ ሆንክ ማለት ነው" በማለት በተግባር ሲገመገም ይህ ነው የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አይደለም ይላሉ።

ዶክተር ምህረት ግን ከዚህ የተለየ ሃሳብ አለቸው። በተለይ በማህበራዊ ሚድያ ቃሉ ላልተገባ ጥቅም እየዋለ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎትም ይህ አንዳልሆነ ይናገራሉ።

"በተለያዩ አካባቢዎች ማህበረሰቡን ተደመረ አልተደመረ እያለ መለየትና ሰው ላይ ጥላሸት በመቀባት ጽንሰ ሃሳቡን ያልተረዳ አለ" የሚሉት ዶክተር ምህረት ሃሳቡ በቀና መንገድ ወደ ህብረተሰቡ እንዲገባ መሰራት አለበትም ይላሉ።

"መደመር፤ ላለመደመርም ነጻነት የማይሰጥ ከሆነ ከራሱ ከቃሉ ጋርም ይቃረናል" በማለት ሃሳቡ ነጻነትን የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ዐብይ አህመድ፡ ያለፉት 100 ቀናት በቁጥር

ለመሆኑመደመር ምንድን ነው?

ከሃሳቡ ጋር የቆየ ቁርኝት እንዳለቸው የሚናገሩት ዶክተር ምህረት ደበበ፤ ሰዎች ተግባብተው አንዱ የሌለውን ነገር ከሌላው እንዲያገኝ፤ እያንዳንዱ አንድ ነገር ለብቻ ከሚሰራ በጋራ ቢሰራ ስኬታማ እንደሚሆን የሚያመላክት አስተሳሰብ እንደሆነና ቀላል የሂሳብ ቀመር ሳይሆን ረቂቅ ግንኙነት እንዳለበት ይናገራሉ።

መደመርን በተመለከተ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተግባር ለመፈተሽ አጭር ጊዜ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ምህረት፤ ይሄ ጽንሰ ሃሳብ በምሁራን ተተችቶና ጥናት ተደርጎበት በግልጽ የተፈተሸ ነገር እንዳልሆነ አመልክተው ይሁን እንጂ ለክርክር ክፍት መሆን እንዳለበት ያምናሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ