ከጨው ማብዛት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ

ምግብ የምትበላ ሴት Image copyright Getty Images

በምንመገበው ምግብ ምክንያት ብቻ በዓለማችን የ11 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት በየዓመቱ እንደሚቀጠፍ አንድ ጥናት ጠቁሟል። በጥናቱ መሰረትም ከሲጋራ በበለጠ ከአምስት ሰዎች አንዱ ከምግብ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወቱ ያልፋል።

በየዕለቱ የምንመገበው ምግብ፤ ዳቦም ሆነ ወጥ፣ የተቀነባበረ ሥጋም ሆነ ጣፋጭ ምግብ፤ በውስጡ የሚገኘው የጨው መጠን በምድር ላይ የምንኖርበትን ጊዜ የማሳጠርና የማስረዘም ከፍተኛ አቅም አለው።

የምግብ ምርጫዎ ስለማንነትዎ ይናገራል?

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ከልክ ካለፈ ውፍረት ጋር አይያያዝም፤ ልባችንን እያስጨነቁ ስላሉና ለካንሰር እያጋለጡን ካሉ የተሳሳተ የአመጋገብ ሥርዓት ጋር ነው የሚያያዘው።

ከምግብ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ከሚሞቱት 11 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 10 ሚሊዮን የሚሆኑት በልብ ነክ በሽታዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። ይህ ደግሞ ጨው ምን ያክል የምግብ ሥርዓታችን ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ማሳያ ነው።

ብዙ ጨው የደም ግፊትን ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ተከትሎት ደግሞ የልብ በሽታ ይመጣል።

Image copyright Getty Images

ጨው ከዚህ በተጨማሪ የደም ስሮች ላይ ጫና በማሳደር ልባችን በድንገት ሥራ እንዲያቆም ሊያደርግ አልያም ወሳኝ የአካል ክፍሎቻችን በትክክል ሥራቸውን እንዳይሰሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ጥራጥሬዎች፣ ፍራፍሬና አትክልቶች ደግሞ የጨው ተቃራኒ ተግባር ነው ያላላቸው። ልብና ልብ ነክ በሽታዎችን ለመከላከል እጅግ ወሳኝ ናቸው።

በዓለም አቀፉ ጥናት መሰረት በአብዛኞቻችን የምግብ ሥርዓት ውስጥ የሚጎድሉት ጤናማ የምግብ አይነቶች የለውዝ ዘሮችና ከአፈር ውስጥ ተቆፍረው የሚወጡት ናቸው።

እውን እንጀራ ሱስ ያስይዛል?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰዎች ከገበታቸው ላይ ለማስቀረት የሚሞክሯቸው የምግብ አይነቶች ጣፋጭ የሆኑትንና ቅባት ነክ የሆኑትን ነበር። ነገር ግን እነዚህ የምግብ አይነቶች ከሚኖራቸው ጉዳት በበለጠ ጨው ብዙ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ ነው።

የጤናማ አመጋገብ አቀንቃኞችና ታዋቂ ሰዎች ስለ ጣፋጭና ቅባት ነክ ምግቦች ጉዳት በብዛት ከማውራት ይልቅ ስለ ጤናማ የምግብ አይነቶችና አወሳሰዳቸው ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩ ጥሩ ነው ይላል የጥናት ውጤቱ።

ልጆችዎ ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ማድረጊያ መላዎች

በታዳጊ ሃገራትም ሆነ ባደጉት ሃገራት የሚገኙ ዜጎች ስለአመጋገባቸው የማይጨነቁ ከሆነ በ50ዎቹ እድሜያቸው በልብ በሽታ ስለመሞት አልያም በ40ዎቹ አካባቢ በካንሰር መሞት ይፈልጉ አይፈልጉ እንደሆነ ሊጠይቁ ይገባል ይላል ጥናቱ።

በሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ የሚገኙ ሃገራት በተለይ ደግሞ እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔንና እስራኤል ያሉ ሃገራት ጤናማ ካልሆነ ካልሆነ አመጋገብ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሞት ዝቅተኛ ነው።

በደቡብ ምሥራቅና በማዕከላዊ እሲያ የሚገኙት ሃገራት ደግሞ በተቃራኒው ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ጋር ተያይዞ ብዙ ዜጎቻቸው ህይወታቸው ያልፋል።