ከ28 ዓመታት በኋላ ለዕይታ የበቃው ኢትዮጵያዊ ተውኔት

የነቃሽ ቲያትር ተዋንያን Image copyright Alazar Samuel

የተውኔቱ ጭብጥ በሕክምና ተቋማት ላይ የሚታዩ ሙያዊ ደባዎች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ሙያቸውን ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉትን የሚተችና የሚያስተምር ታሪክ ነው። በአስክሬን ሽያጭ፣ በመድሃኒት አቅርቦት፣ ከአስክሬን ላይ ስለሚደረጉ ዘረፋዎች ገልጦ ያሳያል- ነቃሽ።

"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7?

ነቃሽ በዮሐንስ ብርሐኑ ተደርሶ ለዕይታ የበቃው ከዛሬ 28 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የባህልና ቲያትር አዳራሽ ነበር። ይህ ተውኔት ከዓመታት በኋላ በተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ በአርቲስት ተፈራ ወርቁ አዘጋጅነት ዳግም ለዕይታ በቅቷል።

በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ የማነ ታዬ ተውኔቱን የተመለከቱት በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ላይ እያሉ በአንድ ጓደኛቸው ጋባዥነት ነበር። "በወቅቱ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበረው" የሚሉት አቶ የማነ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ የነበረውን ረጅም ሰልፍ ተቋቁመው እንዳዩት ያስታውሳሉ።

ከተውኔቱ በተለይ አልአዛር ሳሙኤል የተጫወተው እኩይ ገፀ ባህሪ (ሊቀረድ) ከአዕምሯቸው አልጠፋም። "ከአስክሬን ላይ የወርቅ ጥርሶችን የሚሰርቅ ገፀባህሪ ነበር እና በዚያ ዘመንና እድሜ እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል ብዬ ስለማላምን በአግራሞት በአዕምሮዬ ተቀርፆ ቀርቷል" ይላሉ።

አሁንም ተውኔቱ በድጋሚ በመቅረቡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በድጋሜ ለማየት እንደጓጉ ነግረውናል።

ዓመታትን ያስቆጠሩ ተውኔቶች ተመልሰው ለተመልካች ዕይታ ሲበቁ እንዲሁም ተመልካች ኖረውም አልኖረውም ለዓመታት ከመድረክ ሳይወርዱ የሚቆዩበት አጋጣሚ ይስተዋላል።

ለዚህም የተውኔት ጸሐፊዎች ብዕር ነጥፏል፣ ገንዘብ ወዳድ ስለሆኑ የተሻለ ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ፊልም ይመርጣሉ፣ የቀደሙትን ቲያትሮች በብስለትም በሃሳብም የሚስተካከላቸው ስለሌለ ተደጋግመው ቢታዩም ይወደዳሉ፤ የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶችን የሚሰጡ በርካቶች ናቸው።

ትንሳኤን "አድማቂ" ገጣሚያን

በእነዚህ ሃሳቦች መካከል ባቢሎን በሳሎን፣ የጠለቀች ጀምበር የሚሉና ሌሎች ተውኔቶችም በድጋሚ ለተመልካች ቀርበዋል። 'አሉ' የተሰኘ ትርጉም ተውኔትም ከ20 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሊወጣ መሆኑን ሰምተናል። በቅርቡ በሀገር ፍቅር ቲያትር የተከፈተው 'ነቃሽ' ተውኔትም አንዱ ሆኗል።

"ነቃሽ በወቅቱ እንደ ሼክስፔር ሥራዎች ያህል ተወዳጅ ስለነበር ከወቅቱ ጋር አስማምተን በድጋሚ ለዕይታ እንዲበቃ ሆኗል" የሚለው አዘጋጁ፣ በተውኔቱ ላይ ከዛሬ 28 ዓመታት በፊት ከተወኑት ተዋናዮች ሁለቱ አሁንም የቀደመውን ገፀ ባህሪያቸውን ወክለው ተጫውተዋል- አልአዛር ሳሙዔልና ፋንቱ ማንዶዬ።

በድጋሜ በተውኔቱ ላይ የመተወን ዕድሉን ያገኘው አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ ቲያትሩን በድጋሚ ለመጫወት ጥያቄ ሲቀርብለት ደስታው ወደር አልነበረውም። "በዚያን ጊዜም ሲሰራ ወቅቱን የጠበቀ ቲያትር ነበር፤ አሁንም ተሻሽሎ በመቅረቡ ተመልካች ይወደዋል" ይላል የቀደመውን በማስታወስ።

እርሱ እንደሚለው የድርሰቱ ሃሳብ ዘመን የሚሽረው አይደለም፤ በተለይ የተነሳው የህክምናው ዘርፍ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተየያዘ የሚሰሩ ደባዎችን የሚያጋልጥና ለመንግስት አቅጣጫ የሚያሲዝ ነው።

በተውኔቱ ላይ የሆስፒታሉ የጥበቃ ክፍል ሆኖ የሚተውነው አርቲስት ፋንቱ አሁንም ተመሳሳይ ገፀ ባህሪይ ይዞ ይጫወታል።

Image copyright Solomon Hagos

28 ዓመታት ወደ ኋላ ተጉዘው ቃለ ተውኔቱን ሙሉ በሙሉ ባያስታውስም ዋናውን ገፀ ባህሪ ውድነህን በተመለከተ "ውድነህ ለድሃ ገንዘቡን የሚሰጥ እንጂ እሱ ከድሃ አይዘርፍም" የሚለውን ንግግር አይረሳውም።

ዳንስን በሁለተኛ ዲግሪ

“ከወጡት ስራዎቼ ይልቅ ገና የሚወጡት ናቸው ትልቅ ቦታ ያላቸው” አለማየሁ ገላጋይ

አርቲስት ፋንቱ ተውኔቶች በድጋሜ ወደ መድረክ መምጣታቸው መልካም ቢሆንም ደራሲያን ወደ ፊልሙ ማዘንበላቸው ግን አዳዲስ ተውኔቶች እንዳይቀርቡ እንደ አንድ ምክንያት ያነሳል። የቀደሙት አንጋፋና ዘመን አይሽሬ ድርሰቶችን የሚያበረክቱት አንጋፋ ደራሲያን ዛሬ በሕይወት አለመኖራቸውም ሌላኛው ተያያዥ ምክንያቱ ነው።

"እኛ በፊት የምንሰራውም፣ የምንተውነውም ፤ በአብዛኛው ህዝቡ እንዲያይልን ፣ እንዲወድልን ፣ እንዲያጨበጭብልን ነው" የሚለው አርቲስቱ ትምህርት ለኑሮ፤ ሙዚቃ ለአዕምሮ በሚል በነፃ ሜዳው ላይ የሚያቀርቡት ዝግጅት እንደነበር ያስታውሳሉ። ዘመኑ ያለ ገንዘብ ለመኖር አዳጋች ቢሆንም፣ ሁሉ ነገር ወደ ገንዘብ መቀየር አለበት ማለቱ ተገቢ እንዳልሆነ ያሰመረበት ጉዳይ ነው።

አርቲስት አልአዛር ሳሙዔልም ከዚህ የተለየ ሃሳብ የለውም። "ተውኔቱ በድጋሚ እንዲመጣ ፍላጎቱ ነበረኝ" የሚለው አልዓዛር አሁንም አዳዲስ ተውኔቶች እየተፃፉ ነው የሚል አቋም አለው። ነቃሽ በዛን ጊዜ የነበረውን የተውኔት ተመልካችን ፍላጎት ያሟላ ስለነበር አሁንም ያንን በድጋሚ ማሳየቱ ጥሩ ነው" ይላል።

የቆዩ ተውኔቶች ለምን በድጋሜ ይመጣሉ?

የተውኔቱ አዘጋጅ አርቲስት ተፈራ ወርቁ በተለያየ ጊዜ በአዘጋጃቸው ተውኔቶች በመጠይቅ ከተሰበሰቡ የተመልካች ምርጫ ውስጥ አንዱ ነቃሽ ሆኖ በማግኘታቸው በድጋሚ እንደተዘጋጀ ይናገራል።

አዘጋጁ እንደሚለው እነዚህ ተመልካቾች ተውኔትን በቋሚነት የሚያዩ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ28 እስከ 45 የሚገመቱ ናቸው ብሏል።

"አሁንም አዳዲስ ተውኔቶች ይወጣሉ፤ ነገር ግን የድሮዎቹም በድጋሚ መሰራታቸው ያላየው ትውልድ እንዲመለከተው ዕድል የሚሰጥ ነው" የሚለው አዘጋጁ አዳዲስ ተውኔቶች ቢፃፉና ለዕይታ ቢበቁ ምርጫው እንደሆነ ይናገራል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ተውኔቶች ለዓመታት መድረክ ተፈናጠው የሚቆዩበትን ምክንያቶች የተውኔት ፅሁፍ አለማግኘት፣ ደራሲዎች ከሚያገኙት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከተውኔት ይልቅ ፊልምን መምረጣቸውና ከተውኔት መሸሻቸውን ከብዙ በጥቂቱ ይዘረዝራል።

የተውኔት ዘርፉ ከድርሰት ጋር በተያያዘ ካለበት ፈተና በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶችን እንደሚያስተናግድም ተደጋግሞ ይነሳል። "አበረታች አይደለም፤ ለባለሙያዎች ጥሩ ክፍያ መክፈል አልተቻለም፤ ቢሮክራሲው፣ የትኬት ቀረጥ፣ የመግቢያ ዋጋ አነስተኛ (30 /40ብር) መሆኑ ኢንዱስትሪውን ቁልቁል እንዲሄድ አድርጎታል" ሲል ያስረዳል። በተለይ በግል ተውኔትን ለሚያቀርቡት ፈተናው ያይላል።

"ፊልሞች በተውኔት ላይ ተፅእኖ አሳድረው ነበር፤ አሁን ግን እየተመለሰ ነው" የሚለው አርቲስት አልአዛር፤ ለዚህም የቀደመው ትውልድ የሚያስታውሰውን መድገሙ አስተዋፅኦ ሳይኖረው አይቀርም ይላል። በመሆኑም የቀደሙት ተውኔቶች ድጋሚ መቅረባቸው ሊበረታታ እንደሚገባ ይናገራል።

ነቃሽ ተውኔት ዘወትር ማክሰኞ ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ከትናንት ሚያዚያ 1/2011 ዓ.ም መታየት ጀምሯል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ