በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በድጋሚ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር ጥረቱ ቀጥሏል

ሳር በእሳት ሲቃጠል Image copyright Amhara Mass Media agency

እ.ኤ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሳምንት በፊት እሳት ተነስቶ መቆጣጠር መቻሉ ይታወሳል።

በዚህም ሳንቃ በር እና መስገጎ በሚባሉ ቦታዎች 330 ሄክታር የሚሆን ቦታ ተቃጥሎ ነበር። ከሳምንት በኋላም በፓርኩ ውስጥ በድጋሚ እሳት ተነስቷል።

በድጋሚም በትናንትናው ዕለት በፓርኩ ውስጥ እሳት ተነስቷል።

እሳቱ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ትላንት ከሰዓት በኋላ መጀመሩን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የህብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሠ ይግዛው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠርም የአካባቢው ህብረተብ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

"በሙጭላ በኩል ወደ ገደሉ በመውረዱ እሳቱን መከላከል አልተቻለም። ገደል በመሆኑም ለመከላከል አዳጋች አድርጎታል። ሜዳማውን ክፍል ተቆጣጥረነዋል። ንፋስ እና ጸሐይ ሲኖር ካልተነሳ በአሁኑ ሰዓት ጋብ ያለ ይመስላል" ሲሉ ገልጸዋል።

የሰሜን ተራሮች ፓርክ እሳት ሙሉ በሙሉ አልጠፋም

እሳቱ የተነሳበት ምክንያት አለመታወቁን የሚናገሩት ኃላፊው ከሳምንት በፊት የተነሳውንም ሆነ አሁን የተቀሰቀሰውን እሳት መንስዔ ለማወቅ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

በአማራ ክልል አካባቢ ደንና የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አልዬ በበኩላቸው ፓርኩ "በሰው ኃይል የተቃጠለ መሆኑ ይታወቃል። ምክንያቱም ቦታው በተፈጥሮ (ቡሽ ፋየር) የሚቃጠል አይደለም። ማነው የሚለውን ግን የምርመራ ቡድኑ እያጠና ነው።" ብለዋል።

ይኽ ዓይነቱ የእሳት አነሳስ አልተለመደም የሚሉት አቶ አብርሃም በፊት በእርሻ እና በንብ ማነብ ምክንያት እሳት ይነሳ እንደነበር ያስታውሳሉ። "የአሁኑ ፓርኩ መሐል መነሳቱ፤ ርቀት ያለው ቦታ ላይ መሆኑ እና የበጋ ጊዜው መራዘሙ ያልተለመደ አድርጎታል።"

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ እሳቱ የተነሳበት አካባቢ ሰዎች ይኖሩበት የነበረ ቢሆንም ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሌላ ቦታ ሄደው እንዲኖሩ ተደርጓል።

አቶ አብርሃም በእሳቱ ጉዳት የደረሰበት የፓርኩ ሣር ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ፓርኩን ከዓለም ቅርስ መዝገብ ውጭ የሚያደርግ ስጋት አለመኖሩን አስታውቀዋል።

አቶ ታደሰ በበኩላቸው "አሁን ከተቃጠለው አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ሳር ነው። ዛፎች ካሉበት እሳቱ የገባው ትንሽ ቦታ ነው። ሣር ደግሞ ዝናብ ሲጀምር ስለሚመለስ በዓለም ቅርስነቱ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም" ሲሉ ሃሳቡን አጠናክረው በዱር እንስሳትም በኩል አንድም ጉዳት እንዳልደረሰም ጨምረው ተናግረዋል።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ አብርሃም እሳት በአካባቢው በተደጋጋሚ ተነስቶ እንስሳቶቹን እና ስነ ምህዳሩን በጊዜ ሂደት የሚጎዳ ሲሆን ብቻ የዓለም ቅርስነቱ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል ይላሉ።

እሳቱን በአውሮፕላን በመታገዝ ለማጥፋት ቀደም ሲል ተጠይቆ እንደነበር የገለፁት ኃላፊው ያሉት አውሮፕላኖች እሳት ከማጥፋት ሥራ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ስላልሆኑ እና የአካባቢው ከፍታም አስቸጋሪ ስላደረገው የሰው ጉልበት መጠቀም መመረጡን አስታውቀዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከዚህ ቀደምም እሳት የተነሳ ሲሆን እንዳሁኑ ግን ስፋት `ያለው አልነበረም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ