ግሪክ ውስጥ አንድ ህጻን ከሶስት ሰዎች ተወልዷል

File image of IVF Image copyright SPL

በግሪክና ስፔን የሚገኙ የስነተዋልዶ ህክምና ባለሙያዎች የአንዲት ልጅ መውለድ የማትችል እናት ችግር ለመፍታት በማሰብ ከሶስት ሰዎች የተወጣጣ ወንድ ልጅ እንድትገላገል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ልጁ ባለፈው ማክሰኞ የተወለደ ሲሆን 2.9 ኪሎ እንደሚመዝንም ታውቋል። እናትና ልጅም በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የህክምና ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ልጅ መውለድ ለማይችሉ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥንዶች ትልቅ ዜና እንዲሁም ታሪካዊ የህክምና ግኝት ነው።

በርካቶች ከምጥ ይልቅ በቀዶ ህክምና መውለድን እየመረጡ ነው

ኢትዮጵያዊያን ቶሎ አያረጁም?

እንግሊዛዊው ከኤችአይቪ 'ነጻ' ሆነ

ነገር ግን የህክምና ሂደቱን የሚቃወሙ ሰዎች አልጠፉም። ምክንያቱም ዶክተሮቹ የተከተሉት የህክምና ስርአት የሙያ ስነምግባር ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል በእንግሊዝ የሚገኙ ዶክተሮች።

የሙከራ ህክምናው የእናቲቱን እንቁላል፣ የአባትየውን ዘር ፍሬና ፈቃደኛ የሆነች አንዲት ሴት እንቁላል በመጠቀም ሲሆን የተሞከረው በስኬት መጠናቀቁ ደግሞ መውለድ ለማይችሉ አስደሳች ዜና ያደርገዋል።

በሙከራ ህክምናው ተሳትፋ ወንድ ልጅ ለመሳም የበቃችው የ32 ዓመቷ ግሪካዊት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ አራት ያልተሳኩ የእርግዝና ሙከራዎችን አድርጋ ነበር።

እንደ ዶክተሮቹ ከሆነ የእናትየው 'ማይቶኮንድሪያ' የተባለውና በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ ያሉ ምግቦችን ወደ ሃይልነት የሚቀይረው አካል ችግር ስለላበት የግድ እንቁላል ከእሷ ተወስዶ 'ማይቶኮንድሪያ' ደግሞ ከፈቃደኛዋ ሴት እንዲቀላቀል ተደርጓል።

አሁን የተወለደው ህጻን በአማካይ ህጻናት ከሚኖራቸው ክብደት ትንሽ አነስ ያለ ቢሆንም በጤናው ላይ ምንም አይነት ችግር እንደማይገጥመው ተገልጿል።

የስነተዋልዶ ችግር ያለባቸው ሴቶች የእራሳቸው ዘረመል ያለበት ልጅ መውለድ የመቻል መብታቸው በሙከራ ህክምናው እውን ሆኗል ብለዋል በህክምናው የተሳተፉት ዶክተር ፓናጎዪስት ፕሳታስ።

በግሪክ እየተከናወነ ባለው የሙራ ህክምና እስካሁን 24 ሴቶች እየተሳተፉ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ስምንቱ ሊያረግዙ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።