የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን እሳት ለማጥፋት ሄሊኮፕተር ተጠየቀ

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ Image copyright Facebook

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እሳት ጠፋ ሲሉት እንደገና እየተነሳ ለሳምንታት ዘልቆ ከባድ ጉዳት እያስከተለ ያለውን እሳት ለማጥፋት የሚረዳ ሄሊኮፕተር ከኬኒያ መንግሥት መጠየቁን ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቢቢሲ አረጋገጠ።

ይህን በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በድጋሚ የተቀሰቀሰውን እሳት በሰው ኃይል ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቦታው የመልክዓ ምድር አቀማመጥ የተነሳ አዳጋች እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጾ ነበር።

በሰሜን ተራሮች በድጋሚ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር ጥረቱ ቀጥሏል

ትናንት ገደላማውን የፓርኩ ክፍል ማቃጠል የጀመረው እሳት መጠኑ መጨምሩን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የህብረተሰብ እና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሠ ይግዛው ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

እሳቱን ለመቆጣጠርም አደረጃጀቱን በማስተካከል የአካባቢው ማህበረሰብ 24 ሰዓት እንዲሠራ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።

"ዛሬም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው እሳቱን ለማጥፋት ወደ ቦታው አቅንቶ በመረባረብ ላይ ነው" የሚሉት ኃላፊው በክልል ደረጃ ልዩ ኃይል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን፣ በፌደራል ደረጃ ደግሞ የቁሳቁስ እና የፋይናንስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው "የንፋስ ፍጥነት ከፍተኛ መሆን፤ ተራራማ የመሬት አቀማመጥ እና የአካባቢው አፈር በእሳተ ገሞራ የተፈጠረ መሆኑ የመከላከሉን ሥራ አዳጋች አድርጎታል" ብለዋል።

እስካሁንም የመከላከልን ሥራን ለመደገፍ ሰባት ሺህ የሚሆን ሰው መሠማራቱንም አክለዋል።

የሰሜን ተራሮች ፓርክ እሳት ሙሉ በሙሉ አልጠፋም

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት እሳቱ ወደ ገደላማው የፓርኩ ክፍል በመስፋፋቱ እና ይህም በሰው ጉልበት ለማጥፋት አደጋች በመሆኑ እሳት የሚያጠፋ ሄሊኮፕተር ከኬንያ ለማምጣት እየተሞከረ መሆኑንና ሙከራውም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘውም ተመሳሳይ እሳት አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ከተነሳም በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥናት በሦስት ፓርኮች ላይ እየተሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሳምንት በፊት እሳት ተነስቶ 340 ሄክታር የሚሆን ቦታ መቃጠሉ ይታወሳል።