ከመጀመሪያው 'የብላክ ሆል' ምስል ጀርባ ያለችው ሴት

ኬቲ ቦውማን

የህዋ ተመራማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ 'የብላክ ሆል' ምስልን በጣም ሩቅ ካለ የክዋክብት ስብስብ ውስጥ ማንሳት ችለዋል።

40 ቢሊየን ኪሎሜትር ይረዝማል የተባለው 'ብላክ ሆል' ምድርን በሶስት ሚሊየን እጥፍ ይበልጣታል ተብሏል። የዘርፉ ባለሙያዎች 'ትልቅ አውሬ' የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።

ይህንን አስገራሚ የብላክ ሆል ምስል ለማንሳት አገልግሎት ላይ የዋሉትን ስምንት ቴሌስኮፖች በማጣመር አንድ ወጥ ምስል እንዲገኝ ያደረገችው ደግሞ የ29 ዓመቷ ሳይንቲስቷ ኬቲ ቦውማን ነች።

ጨረቃን የሚረግጠው የመጀመሪያው ጎብኚ ታወቀ

በሳተላይቶች ዙሪያ ሰባት አስደናቂ እውነታዎች

በዚህ ስራዋም በመላው ዓለም የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ሰዎች አድናቆታቸውን እያጎረፉላት ይገኛሉ።

'ብላክ ሆል' ከምድር 500 ሚሊየን ትሪሊየን ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ 'ኢቨንት ሆራይዝን' የተባሉ ስምንት ቴሌስኮፖችን በመጠቀም ነው ምስሉን ማንሳት የተቻለው።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ጥቁሩ ቀዳዳ

ፕሮግራሙን ደግሞ በዋነኛነት ስትመራው የነበረችው ኬቲ ነበረች።

ሙሉውን ምስል ባገኘችበት ወቅትም '' እስካሁን ድረስ የመጀመሪያውን የብላክ ሆል ምስል ማግኘቴን አላመንኩም'' ስትል በፌስቡክ ገጿ ላይ አስፍራለች።

ኬቲ በመላው ዓለም ተበታትነው የሚገኙትን ቴሌስኮፖች እንደ አንድ አድርጎ ለመጠቀም የሚያስችል ዘዴ ለማበጀት የማሳቹሴትስ ቴክኖሎኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ ሶስት ዓመታት ፈጅቶባታል።

ይህንን የሙከራ ሃሳብ ያቀረቡትና ከኔዘርላንድስ ሬድባውንድ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ሄይኖ ፋልኬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት 'ብላክ ሆል' የተገኘው M87 በተባለ የክዋክብት ስብስብ ውስጥ ነው።

''ክብደቱ ከጸሐይ 6.5 ቢሊየን እጥፍ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ አሉ ብለን ከምንገምታቸው ሁሉ እጅግ የላቀ ሆነ አግኝተነዋል። የብላክ ሆሎች ሁሉ ታላቅ እንደሆነ አስባለሁ።'' ብለዋል።

የብላክ ሆልን ምስል ለማንሳት በተደረገው ጥረት ከአንታርክቲካ እስከ ቺሊ ድረስ ከ200 በላይ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።

''ማንም ሰው ብቻዬን አደርገዋለው ብሎ የሚያስበው ነገር አይደለም። ጥረታችን ወደ እውነታ የተቀየረው ሁሉም ተሳታፊ ባደረገው ትልቅ አስተዋጽኦ ነው። ለዚህም በስራው ላይ የተሳተፉትን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።'' ብላለች ኬቲ።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በታሪክ የመጀመሪያው የብላክ ሆል ምስል

ስለ ብላክ ሆል እስካሁን የታወቀው

  • ብላክ ሆል በአይን ለመመልከት እጅግ አስቸጋሪና እስከ 40 ቢሊየን ኪሎሜትሮች ድረስ ርዝማኔ ያለው ሲሆን ምድርን በሶስት ሚሊየን እጥፍ ይበልጣታል
  • M87 በተባለው የክዋክብት ስብስብ ውስጥ የተገኘው የብላክ ሆል ምስል ለአስር ቀናት ነው የተከናወነው
  • ከምድራችን ስርአተ ጸሐይ በእጅጉ የበለጠና ለማወዳደርም የሚከብድ ግዝፈት አለው

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

በሕይወት ከሌለች እናት የተወለደችው ሕፃን

በምድራችን ላይ የሚገኝ የትኛውም ቴሌስኮፕ ብቻውን የብላክ ሆልን ምስል መውሰድ አይችልም። ለዚህም ነው በመላው ዓለም የሚገኙ ስምንት ቴሌስኮፖችን በማጣመር አስር ቀናት የፈጀ ፎቶ ማንሳት ግድ ያለው።

ቴሌስኮፖቹ ያነሷቸውን ምስሎች ደግሞ በመቶዎች በሚቆጠሩ የመረጃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ በመሰብሰብ በየዕለቱ ወደ አሜሪካና ጀርመን በአውሮፕላን ይላኩ ነበር።

የዶክተር ኬቲ ቦውማን ስራም እዚህ ላይ ነበር እጅግ ጠቃሚ የነበረው። እሷ የፈጠረችው መረጃዎችን የማቀናጀት መንገድ ውጤታማ ሆኖ ዓለምን ያስደመመ ምስል ማግኘት ተችሏል።