በአዲስ አበባ ሊፈጸም የነበረ የሽብር ጥቃት መክሸፉ ተነገረ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ጸጋዬ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ሊፈጸም ታስቦ ሳይሳካ ስለቀረ የሽብር ጥቃት፣ በሃገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች ስለተከሰቱት ግጭቶች፣ ትናንት እና ዛሬ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ስለዋሉት ግለሰቦች በመግለጫው የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

ከአልሸባብ ጋር ግነኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ ጨምረውም ከፍተኛ የሽብር ጥቃት በሀገሪቱ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውንና ተጠርጣሪዎቹ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር የሚፈፅሙበትን ስልት በመቀየስ እና ቦታ በመለየት ላይ እንደነበሩ ጠቁመዋል።

የሽብር ጥቃቱን ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የነበሩትን ተጠርጣሪዎች ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባባር አደጋ ከማድረሳቸው በፊት በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።

አቃቤ ሕጉ እንዳሉት የሽብር ጥቃቱን ሊፈጽሙ ነበር ከተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ተገኙ በተባሉት ሰነዶች መሰረት የሽብር ጥቃቱን ቢፈፀሙ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችል እንደነበር አመልክተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጥቃቶቹ ህዝብ በስፋት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሊፈጸሙ ታቅደው እንደነበረ ተናግረዋል። ታስበው ስለነበሩት የሽብር ጥቃቶች ዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚሆንም አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ተናግረዋል።

መግለጫውን የሰጡት ዋና አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ ከግንቦት 2010 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም ድረስ 21 መትረየሶች፣ 270 በላይ ኤኬ47 ክላሽንኮቮች፣ 33ሺህ ሽጉጦች እና ወደ 300ሺህ የሚጠጉ ጥይቶች መያዛቸውንም ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል መስቃን፣ በወሎ እና በቅማንት አካባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ዙሪያ ምርመራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅላይ ቃቤ ሕጉ ጨምረው ተናግረዋል።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስለዋሉት ግለሰቦች ተጨማሪ መረጃ የሰጡት ዋና አቃቤ ሕጉ የመንግሥት ንብረት ግዢና ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በሰጡት መግለጫ እንደጠቆሙት፤ በሦስት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች የተጠረጠሩ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ጨምሮ 59 ሰዎች በፖሊስ መያዛቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት የተደረገን ምርመራን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ብርሃኑ ምርመራው የወንጀል ድርጊቶቹና ያስከተሉት ጉዳት ከእያንዳንዱ ተጠርጣሪ አንጻር መረጃ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ተቋም ላይ በተካሄደው የምርመራ ከ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ ጋር በተያያዘ 24 ሚሊዮን ዶላር ከመመዝበሩ በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ የዳቦ እጥረት እንዲከሰት በማድረግ በህዝብና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ማድረሳቸው ተጠቁሟል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በተጨማሪም በውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ውስጥ በመመሳጠር ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ከሕግ ውጪ በተፈፀመ ግዢ የሙስና ወንጀል መፈጸሙን ጠቅሰዋል። እንዲሁም የመድሃኒት ፈንድ ኤጀንሲም ከሕግ ውጪ የ79 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን አመልክተዋል።

አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ሊፈጸም ስለነበረው ጥቃትና ሌሎቹም ጉዳዮች በምርመራ ሂደት ላይ በመሆናቸው ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቀደም ሲል በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር፣ በምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ እና ከኢትዮጵያ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ውስጥ የሚገኙ ስድሳ አንድ ሰዎች በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ መያዛቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ከተያዙት ሰዎች መካከል እስካሁን ማንነታቸው የተጠቀሰው የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይገዙ ዳባ እና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በኅላፊነት የሚሰሩ ሌሎች 59 ሰዎች ናቸው።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በመንግሥት ሃብት ምዝበራ፣ በሙስናና በኢኮኖሚያዊ ሻጥር ተጠርጥረው መሆኑንም የተለያዩ ምንጮች ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ጠቅላይ አቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በጋራ በመሩት ዘመቻ ትናንት ሲሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል ላይ አስፈላጊው መረጃ መሰብሰቡም ተጠቅሷል።