መሞነጫጨርን አንድ የሥዕል ስልት ያደረገው ሙያተኛ

አፄ ሚኒሊክ

የፎቶው ባለመብት, MERHATSION GETACHEW

መርሃፅዮን ጌታቸው ይባላል፤ በሙያው የኪነ ሕንፃ ባለሙያ ሲሆን በዓይነቱ የተለየ የሥዕል ተሰጥዖውን በእራሱ ጥረት በልምምድ አዳብሯል።

ልጆች ሥዕል በሚስሉበት ወቅት ከመስመር ትንሽ ወጣ ሲሉ እንዲያስተካክሉ ማድረግ የተለመደ ቢሆንም ለመርሃፅዮን ግን ይሄ ከመስመር የመውጣትም ሆነ የመሞነጫጨር ስልት እንደ አንድ የጥበብ መገለጫ ዘዴ ሆኖ ታይቶታል።

የኪነ ሕንፃ ትምህርት መማሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገለት የሚናገረው መርሃፅዮን ምንም እንኳን የሥዕል ትምህርትን ባይማረውም ሁለቱ ዘርፎች አብረው መሄዳቸው ተሰጥዖውን ለማዳበር ረድቶታል።

ሥዕል ለመሳል ያነሳሳው አጋጣሚ አስረኛ ክፍል በነበረበት ወቅት በፎቶግራፎች ተማርኮ እንደሆነ ይናገራል። "ጥቁርና ነጭ ፎቶግራፎች ቀልቤን ይስቡታል፤ እነሱን እያስመሰሉ በመሳል ነው የጀመርኩት" ይላል።

በፎቶዎች የብርሃንና ጨለማ መስተጋብር ልዩ ስሜት የተማረከው መርሃፅዮን ሰዎችን የሥዕሎቹ ዋና ገፀባህርይ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም።

ዓይን የነፍስ መስኮት ነው እንደሚባለው መርሃፅዮንም "በሰዎች ፊት ላይ ምሉዕነት አያለሁ፤ በተለይ ደግሞ የሰዎች ዓይን በቃላት መግለፅ የማልችለው ስሜት ይፈጥርብኛል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, MERHATSION GETACHEW

ብዙ ንግግር እንደማይችል የሚናገረው መርሃፅዮን ቃላትን ለማውጣት በሚቸገርበት ወቅትና ስሜቱን ለመግለፅ በሚከብደው ጊዜ ሥዕል ሃሳቡን መተንፈሻ መንገድ ብቻ ሳይሆን የሥዕል ኃያልነት መገለጫም እንደሆነ ያስባል።

"የዚህ ዓይነት የአሳሳል ዘዴ ደግሞ ለጣቶቼ ነፃነት ይሰጠኛል" ይላል መርሃፅዮን።

"እየሞነጫጨሩ መሳል ምስቅልቅል ባለ መልክ ላይ ሥርዓትን ማሳየት ይችላል፤ ይህ ተቃርኖ የእራሱ የሆነ ውበት ይፈጥራል። መስመሮቹ አቅጣጫ ስለሌላቸው በፈለጉት መንገድ ይወረወራሉ።"

የሚከተለው የሥዕል አሳሳል ስልት 'ስክሪብል' የሚባል ሲሆን "ስክሪብል የተባለው የሥዕል ስልት ሐቀኛ ነው፤ መስመሮቹ የሥዓሊው ጣቶች ሙሉ ጉዞ ሕትመት ናቸው" በማለት ስለ አሳሳል ዘዬው ያስረዳል።

"በተለይ ደግሞ ሲመለከቱት የቆመ ሥዕል አይደለም፤ ጉልበት አለው፣ ይንቀሳቀሳል።"

ከሥዕሎቹ ውስጥ ልዩ ስሜት የሚፈጥርበት የአዳም ረታ ሥዕል ሲሆን ሥራው የአዳምን ሥነ-ጽሑፍ ጥልቀት፣ ውስብስብነትና እውነታን እንደገለፀለት ያስረዳል።

በፌስቡክና በኢንስታግራም ገፆቹ ቃላትን ከሥዕሎቹ ጋር አዛምዶ የሚጠቀም ቢሆንም አንዳንዴ ግን ሥዕሎቹ የሚገልፁትን ሃሳብ በቃላት ለመግለፅ እንደሚቸገርና ስለዚህም በእራሳቸው ለብቻቸው እንደሚያስቀምጣቸው ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, MERHATSION GETACHEW

የምስሉ መግለጫ,

ከስዕሎቹ መካከል ልዩ ስሜት የሚፈጥርበት ስዕል

በዋናነት የታዋቂ ሰዎችን የፊት ገፅ የሚስል ሲሆን ይህንንም የመረጠበት ምክንያት ግለሰቦቹ የሚወክሉት ሃሳብ እንደሆነ ይናገራል።

"ሰዎች ከሚያውቁት ነገር ጋር እራሳቸውን አዛምደው መረዳት ይችላሉ፤ ሃሳብ ለብቻ ከሚቀርብ ይልቅ ሰዎች ከሚያውቁት ነገር ጋር ሲቀርብ ለመረዳት አይቸገሩም" ይላል።

ወደ መጀመሪያ አካባቢ ሥዕሎቹን ለመሳል እርሳስ በብዛት የሚጠቀም ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ግን ቀለሞችን መጠቀም ጀምሯል። ሥዕሎቹን ወረቀትና እንጨት ላይ የሚስል ቢሆንም አሁን የተለያዩ ቁሶች ላይ ለመሳል ሙከራን እያደረገ ነው።

የጥበብ ሥራ ሂደት እንደሆነ የሚናገረው መርሃፅዮን መማር እንደማያቆም ያስረዳል "አሁንም እየተማርኩ ነው፤ የእራሴ የሆነ የሥዕል ስልት አግኝቻለው ብዬ አላስብም። ሥነ-ሥዕል ውስጥ ገና ብዙ የምማራቸው ነገሮች አሉ" ይላል።

መርሃፅዮን ለወደፊቱ ግን ከኪነ ሕንፃው ይልቅ ወደ ሥነ-ሥዕል ለማዘንበል አስቧል።