ሱዳን የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር አዋለች

የተቃውሞ ሰልፈኞች Image copyright AFP/Getty

የሱዳን የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤት የቀድሞ የሃገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር በማዋል የተቃውሞ ሰልፈኞችን እንደማይበትን ቃል ገባ።

የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ጨምረው እንዳስታወቁት ተቃዋሚዎች ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር በፍጥነት እንዲመርጡ በማሳሰብ ፍላጎታቸውም እንደሚከበር ቃል ገብተዋል።

ለወራት የቆየው የሱዳን ተቃውሞ ለሰላሳ ዓመታት ሲመሩ የነበሩትን ኦማር አል በሽርን ባለፈው ሐሙስ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ያስገደደ ሲሆን ሰልፈኞቹ እስካሁንም ቢሆን ገለልተኛ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ከመንገዶች እንደማይንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

ኦማር አል-በሽር: ከየት ወደየት?

የሱዳን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ወታደሩ ያስቀመጠውን ሰዓት እላፊ ጣሱ

በዋና ከተዋማ ካርቱም በሚገኘው የመከላከያ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ውስጥ እየተደረገ ያለውም ውይይት እስካሁን እንደቀጠለ ነው።

ጊዜያዊው ወታደራዊ ምክር ቤት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት ማንኛውም አይነት የመንግስት አስተዳደር ሃሳብ እንደሚስማማና ተግባራዊ እንደሚያደርግ ቃል አቀባዩ ማጀር ጀነራል ሻምስ አድ ዲን ሻንቶ እሁድ ዕለት ገልጸዋል።

''እኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አንሾምም። ራሳቸው ናቸው የሚመርጡት'' ብለዋል ቃል አቀባዩ።

አክለውም ወታደሮች ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞችን ለመበተን ምንም አይነት እርምጃ እንደማይወስዱ ቃል በመግባት ሰልፈኞች ግን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱና መንገድ መዝጋት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ''የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም ሆነ መጠቀም ተቀባይነት የለውም'' ብለዋል።

በመግለጫው ላይም የወታደራዊ ምክር ቤቱ አዲስ የመከላከያና የፖሊስ ሃላፊዎች እንዲመረጡ፣ አዲስና ጠንካራ የደህንንት መስሪያ ቤት እንዲቋቋም፣ የሙስና ወንጀሎችን የሚመረምርና የሚከላከል ኮሚቴ ስራ እንዲጀምር፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳና አፈና እንዲነሳ፣ ተቃዋሚዎችን በመደገፋቸው በእስር ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት እንዲፈቱ ፣ ዲፕሎማሲያዊ ለውጥ እንዲደረግ እንዲሁም በአሜሪካና በስዊዘርላንድ የሱዳን አምባሳደር ከስራቸው እንዲነሱ ወስኗል።

ኦማር አል-በሽር ከስልጣን ተነስተው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ስለመደረጋቸው በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የተናገሩት የጦር አለቃ አዋድ ሞሐመድ አህመድ ኢብን ኡፍ ይሰኛሉ።

ሱዳን ውስጥ የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ንሮብናል ያሉ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

የኢትዮጵያና አሜሪካ የተለየ ግንኙነት እስከምን ድረስ?

ባለፈው ሐሙስም ለሰላሳ ዓመታት ያህል ሱዳንን ሲመሩ የቆዩት አል-በሽር ከስልጣን መነሳታቸውን የሃገሪቱ መከላከያ ሚንስትር አስታውቀዋል።

የኑሮ ውድነት ወደ አደባባይ ያወጣቸው ተቃዋሚዎች፤ የአል-በሽርን ከስልጣን መነሳት አደባባይ በመውጣት ሲጠይቁ መሰንበታቸው ይታወሳል።

ተቃዋሚዎች በአደባባይ ተሰቅለው የሚገኙ የፕሬዚዳንቱን ምስል ሲያነሱ ተስተውለዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በመናገሻ ከተማዋ ካርቱም በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቅጥር ግቢ ፊት ለፊት በመገኘት የይውረዱ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን ሰኞ ዕለት ከመከላከያ ኃይሉ ጋር የሽግግር መንግሥት መመስረት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚፈልግ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ተቃውሞ አካሂዷል።

ፕሬዝዳንት አል በሺር እ.ኤ.አ ከ 1989 ጀምሮ ሱዳንን ያስተዳደሩ ሲሆን 'ስልጣን ይብቃዎት፤ ይውረዱ' የሚል የሕዝብ ድምፅ በአደባባይ መሰማት ከጀመረ ወራት ተቆጥሯል።