የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢህአዴግን ወዴት ይመራው ይሆን?

ኢህአዴግ Image copyright EPRDF

የገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከጠቅላላው ጉባኤ ቀጥሎ ወሳኝ የሆነውን መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን ከዛሬ ጀምሮ በማካሄድ ባለፉት ወራት ስለተከናወኑ ተግባራትና በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ግምገማ በማድረግ ውሳኔዎችን እንደሚሰጥ ተነግሯል።

ይህ የምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን መጥተው በድርጅቱ የተወሰኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ድፍን አንድ አመት ከሞላቸው በኋላ የሚደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ ሃገሪቱ ውስጥ የተለያዩ አሳሳቢ ችግሮች እየተከሰቱ ባሉበት ወቅት ነው።

በተጨማሪም ቀደም ሲል የገዢው ግንባር መስራችና ዋነኛ አካል የነበረው ህወሓት በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረው ወሳኝነትና ተሳትፎ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጡ በኋላ እየቀነሰና ከግንባሩ ጋር ያለው ትስስር ላልቶ ባለበት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ምናልባትም የጥምረቱን የወደፊት አቅጣጫ የሚወስን ሊሆን ይችላል።

ኢህአዴግ እዋሃዳለሁ ሲል የምሩን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆን የሃገሪቱን የመሪነት መንበር ከያዙ በኋላ የህወሓት ተሳትፎ በእጅጉ የቀነሰ ሲመስል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ኦህዴድ (የአሁኑ ኦዲፒ) ከብአዴን (ከአሁኑ አዴፓ) ጋር የጠነከራ ጉድኝት አጠናክረዋል። የደቡቡ ደኢህዴንም የሁለቱን ያህል ባይሆንም ከጥምረቱ ጋር ያለው ዝምድና በነበረበት የዘለቀ ነበር።

ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከህወሓት እንደ ድርጅት የሚወጡ መግለጫዎችና አመራሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚናገሯቸው ነገሮች በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከዚህ በፊት የነበረው ጥብቅ ትስስርና ማዕከላዊነት እየላላ አንዳንድ ጊዜም የሚቃረኑ ተጻራሪ ነገሮች ሲቀርቡ ተስተውሏል።

በተለይ ዛሬ ከሚጀመረው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ቀደም ብሎ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ካደረገው ስብሰባ ተከትሎ የወጣው የድርጅቱ መግለጫ ማዕከላዊው መንግሥት የሚጠበቅበትን እንዳልተወጣና የድርጅቱ የተሃድሶ ውሳኔ ከታሰበለት አቅጣጫ መውጣቱን በመጥቀስ ጠንካራ ትችትን ሰንዝሯል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ በሃገሪቱ እየተከሰተ ያለው ችግር እየተባባሰ መሆኑንና ወደማያባራ አደጋ የሚያስገቡ ችግሮች በመጠንም በስፋትም እየጨመሩ መሆናቸውን አመልክቶ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ለውጦችን ስጋት ላይ መውደቃቸውን አመልክቷል።

የኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ እርምጃ "ተኮላሸቷል" ብሎ የሚያምነው ህወሓት በሃገሪቱ "የሰላም እጦት መስፋፋቱን፣ መረጋጋት እየጠፋ ሁከትና ግርግሮች በስፋት እየጨመረ መምጣቱ፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር እንዳልተቻለ. . ." በመጥቀስ ግምገማ ማድረጉን ገልጿል።

"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጨምሮም ለዚህ እንደዋና ምክንያት ያስቀመጠው አመራሩ ከኢህአዴግ መሰረታዊ እምነቶች ማፈንገጡና "ቅጥ ባጣ ደባል አመለካከት" ተበርዟል በማለት የሕገ መንግሥት ጥሰት እየፈፀመ እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አስተሳሰብና ድርጊት መንሰራፋቱን በመጥቀስ ያለውን የድርጅቱን አመራር ከሷል።

ይህ ከኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በፊት የወጣው የህወሓት መረር ያለ መግለጫ የድርጅቱን ስብሰባ ጠንከር ያሉ ጉዳዮች የሚነሱበትና የአባል ድርጅቶቹ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚወስን ውጤትን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ነገር ግን ከድርጅቱ የቆየ ባሕል አንጻር በውስጥ የሚደረጉ ንግግሮች ከውጪ እንደሚታዩት የጎላ ለውጥ በሚያመጣ ሁኔታ ሳይሆን የእርስ በርስ ግምገማ በሚመስል ሁኔታ ውይይት ተደርጎባቸው በእዚያው ተዳፍነው ይቀራሉ የሚሉ በርካታ ሰዎች አሉ።

የቀድሞው የአዴፓ አባል አቶ ቹቹ አለባቸው እንደሚሉት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባቸው ላይ ብዙ ነገሮች አንስተው "እስከ ጥጋቸው" ድረስ እንደሚገማገሙ ነገር ግን አንዳችም ነገር ወደ ውጪ አይወጣም።

የህወሓትና ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለድምጺ ወያኔ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ግን ድርጅቱን የገጠሙት ፈተናዎች ከበድ ያሉ በመሆናቸው ፊት ለፊት ያሉ ችግሮችን ከመነጋገር ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ የድርጅታቸው እምነት መሆኑን አመልክተዋል።

አምስት ጉዳዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ

በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲነሱ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች ቀደም ብሎ በመግለጫው ላይ ይፋ ያደረገው ህወሓት ብቻ ሲሆን በዋናነት የእርሱ አጀንዳ የውይይት መድረኩን ይይዘዋል ተብሎ ይታመናል። ጉዳዮቹም ያለውን አመራርና የድርጅቱን ቀጣይነት የሚመለከቱ በመሆናቸው ውይይቱ ከዚህ በፊት ከነበሩት አንጻር ጠንከር ያለ ሊሆን ይችላል።

የድርጅቱን የወደፊት ዕጣን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የተነሳው አባል ድርጅቶችን በማዋሃድ ኢህአዴግን አንድ ወጥ ፓርቲ የማድረጉ ፍላጎት ክፉኛ በህወሓት ከተብጠለጠሉት ጉዳዮች አንዱ ነው። መግለጫው ጉዳዩ የተነሳው "ኢህአዴግ ጤናማ በነበረበት ወቅት" እንደሆነ በመግለጽ ችግሮች እንዳሉ አመልክቷል።

"ጉባኤው ከፍተኛ ፍትጊያ ይኖረዋል" የሚሉት አቶ ቹቹ፤ በተለይ ወደ ውህደት የመሄዱ ጉዳይ ከፍተኛ የሃሳብ ፍጭት እንደሚያስተናግድ ይህም ከህወሓት በኩል እንደሚሆን ያምናሉ።

ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ "ህወሓት እያለ ያለው ከአንድነት በፊት አንድ ሊያደርጉን የሚገቡት የመርህ ጉዳዮች ላይ እንስማማ ነው። ከዚህ አንጻር የፓርቲዎቹ ጉልበት እያበጠ የኢህአዴግ አቅም እየተዳከመ ስለመጣ ውህደቱ እውን ይሆናል ብዬ አላምንም፤ ከሆነም ለይስሙላ እንጂ ትርጉም አይኖረውም" ይላሉ።

ይህንን ሃሳብ የሚያራምዱት ኦዲፒ፣ አዴፓ እና ደኢህዴንም ቢሆኑ በየክልሎቻቸው የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ድርጅቱን በማዋሃድ ሊወጡት ያሰቡ እንደሚመስላቸው የሚናገሩት አቶ ቹቹ ሦስቱ ከደገፉት ወደፊት የመሄድ ዕድል እንዳለው ይገምታሉ።

"ኦዴፓ በክልሉ በኦነግ ና በሌሎች ፖለቲከኞች የበላይነት እየተወሰደበት ስለሆነ በመጣበት ለመሄድ ስለሚቸገር ውህደቱን ተጠቅሞ በመድረኩ ላይ አስፈላጊ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋል፤ ደኢህዴን በክልሉ በሚነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች የተነሳ እየተፍረከረከ ከማንም በላይ ውህደቱን ይፈልገዋል። አዴፓ መንታ መንገድ ላይ ይቆማል፤ ምክንያቱም ውህደቱን ይፈልገዋል ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ብሄርተኛ ድርጅት ስለመጣበት ለመምረጥ ይቸገራል። እንደዚያም ሆኖ መምረጥ ካለበት ውህደቱን ይመርጣል" ሲሉ አቶ ቹቹ ይተነትናሉ።

አቶ ጌታቸው አሰፋ የሀዋሳውን ጉባኤ ይታደማሉ?

አሁን አሁን ፓርቲዎቹ ባሉበት ሁኔታ ውህደት ይፈጸማል የሚል ግምት የለኝም የሚሉት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ገረሱ ቱፋ ናቸው። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ "መጀመሪያ በውስጣቸው ያለው አብሮ የመቀጠልን ችግር መፍታት አለባቸው። አብረው ከቀጠሉ ምን አሻሽለው ነው የሚቀጥሉት? አጋር ተብለው ሲጠሩ የነበሩት ድርጅቶችስ እንዴት ነው የሚሆኑት?" የሚለውን ወስነው ለህዝብ ግልጽ ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ።

የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ህወሓት እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ያለውን አመራር ተጠያቂ ነው ማለቱ እንደ ክርክር ሊቀርብ የሚችል ቢሆንም አሁን ያለው አመራር ሲመረጥ ህወሓቶችም እንደነበሩ ይጠቅሳሉ። ስለዚህ የኢህአዴግ ውድቀት የህወሓትም ውድቀት ነው ይላሉ።

እንደ አቶ ሙሉጌታ "ፓርቲዎቹ አሁን የያዙት አንዱ አንዱን መክሰስና መወንጀል ነው። እንደ ኢህአዴግ አንድ ሆነን በአንድ መመሪያ ለመገዛት በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ቃል የምንገባበት ውሳኔ ማስተላለፍ አለብን የሚሉ አይደሉም። ሌላው ቀርቶ በርዕዮተ ዓለም እንኳን ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው።"

አክለውም ያላቸውን ልዩነቶች በአንድ ስብሰባ አስታርቀው አንድ የሚያደርጋቸው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው እንደማይጠብቁና "እንደዚያ ብሎ ማሰብ ተአምር እንደመጠበቅ ነው" ይላሉ።

አቶ ቹቹ አለባቸውም ከስብሰባው ብዙ አዲስ ነገር ይመጣል ብለው አይጠብቁም። "በውህደቱ በኩል ግን ምናልባት አገሪቱ አስፈሪ ደረጃ ላይ እየደረሰች ስለሆነ፤ ቢስማሙም ባይስማሙም ወደ አንድነት የመምጣቱን ጉዳይ ሊያጣጥሙት ይችላሉ። ይህ የሆነው ደግሞ የብሄር ፖለቲካው ጫፍ ላይ በመድረሱ ነው የሚል ድምዳሜ ስላለ በዚህ ላይ ጠንከር ያለ አቋም ይወስዳሉ" በማለት በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በርካታ አወንታዊ ለውጦች እንደመጡ የሚናገሩት አቶ ቹቹ "ኢህአዴግ ግን ተዳክሟል" ይላሉ።

በለውጡ ሂደት የማዕከላዊ መንግሥት ሕግ የማስከበር አቅም መዳከም አመራሩ ወደሚፈለገው አቅጣጫ እንዳይሄድ እንዳገደው ጠቅሰው መፈናቀሎች፣ በአዲስ አበባ ላይ የተወሰደው አቋም፣ ሹመት አስጣጦች ተደማምረው "ከህወሓት የባሰ እንጅ የተሻለ አልመጣም ወደሚል ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ ህዝቡን ወሰዶታል" ይላሉ አቶ ቹቹ።

በአዲስ አበባ ሊፈጸም የነበረ የሽብር ጥቃት መክሸፉ ተነገረ

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከሚያካሂደው ስብሰባ ሃገርን ወደ ጤነኛና ወደ ተረጋጋ መንገድ ሊወስድ የሚችል የመፍትሄ ሀሳብ አልጠብቅም ብለዋል አቶ ቹቹ አለባቸው።

ምክንያታቸውንም "አራት ድርጅቶች እንደ ድርጅት እና እንደ ግለሰብ በመሃከላቸው ያለው ግንኙነት ጤነኛ አይደለም። እየተወያዩ ሳይሆን አንዱ አንዱን ሲያወግዝና ሲከስ ነው የቆዩት። በዚህም ሳቢያ የድርጅቶቹ መሪዎች ተገናኝተው ሲወያዩ በተቻለ መጠን አንዱ ሌላኛውን እየወቀሰ የራሱን የፖለቲካና የበላይነት ለማረጋገጥ የሚጥሩ ነው የሚመስለኝ።" ሲሉ ያስቀምጣሉ።

ፖለቲከኞች ዋና አላማቸው ስልጣን ነው የሚሉት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ "ከዚህ ቀውስ ምን አተርፋለሁ? የሚለው ይመስለኛል የመጀመሪያው እሳቤያቸው" ይላሉ።

በዚህ ምክንያት አሁን ያለው ከባድ አገራዊ ችግር ከባድ ፈተና የደቀነ ቢሆንም ለፖለቲከኞች ግን ችግሩ አልታያቸውም ይላሉ። "በአንድ ስብሰባ ተገናኝተው መሰረታዊውን የአገራችን ችግር ፈትሸው፤ የራሳቸውን የስልጣን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው የአገር ፍላጎት አስቀድመው ሊያረጋጋ የሚችል ውሳኔ ያሳልፋሉ ብዬ አላስብም" ይላሉ አቶ ሙሉጌታ።

ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ አዎንታዊ እርምጃዎች ቢታዩም ፈታኝ ሁኔታዎችም እንዳሉ የሚያስታውሱት አቶ ገረሱ ቱፋ አሁን በሚያደርጉት የምክር ቤት ጉባኤም "ድርጅቶቹ በውስጣቸው ያለውን ችግር ፈትተው፤ ለወደፊቱም ግልፅ የሆነ ራዕይ በማስቀመጥ አገሪቷ አሁን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ወዴት እንደሚወስዱ፣ እየተነሱ ያሉ ግጭቶች እንዴት እንደሚፈቱ ወስነው ይወጣሉ" ብለው እንደማያስቡ አቶ ገረሱ ይናገራሉ።

በርካቶች ከገዢው ኢህአዴግ ውስጥ ተለይቶ ለመውጣት ፍላጎት እንደማይኖር ቢያምኑም፤ ምናልባት የመለያየት ነገር ቢከሰት አሳሳቢ ሁኔታ እንደሚፈጠር አቶ ገረሱ ይናገራሉ።

መለያየቱ ከመጣ "አገሩን በማስተዳደር ላይ ችግር ይገጥማቸዋል። ግጭቶች በየቦታው ይከፈታሉ። ይህ ሁኔታ ለተቃዋሚዎች አማራጭ ሆነው ሊመጡ የሚያስችላቸው ቢሆንም ዝግጅት እያደረጉ አይደሉም። እስካሁንም ምን አይነት አማራጭ እንደሚያመጡ ያሳዩበት ሁኔታ የለም። በዚህ ምክንያት በቂ ሚና ይጫወታሉ የሚል እምነት የለኝም" ሲሉ አስረድተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ