ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ አቋሟን ትቀይር ይሆን?

የህዳሴ ግድብ Image copyright Getty Images

ሱዳን በህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ ከጅማሮ አንስቶ በነበራት አቋም የኢትዮጵያ አጋር ነች። በአጠቃላይ የተፋሰሱ ሃገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር ሱዳን የቆመችው ከኢትዮጵያ ጋር ነው።

በአንፃሩ ግብፅ የግድቡ ሃሳብን በመቃወም ገና ከጠዋቱ ይሆናል ያለችውን ዕድል ሁሉ ስትሞክር ነበር። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዛሬም ያን ጥረቷን አላቋረጠችም።

ከቀናት በፊት አንቀጥቅጠው የገዟትን ኦማር ሃሰን አል-ባሽርን በቃኝ ብላ ከሥልጣን ያስወገደችው ሱዳን ያልለየለት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነች። ይህን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የአቋም ለውጥ ልታደርግ ትችላለች ወይ?

በኢትዮጵያ በኩል የህዳሴው ግድብ ግንባር ቀደም ተደራዳሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ሱዳን የህዳሴው ግድብን በሚመለከት በአቋሟ ትቀጥላለች ብለው ያምናሉ። ግብፅ ግን ዳር ላይ ቆማ እንዲሁ ነገሮችን ልትመለከት አትችልም።

በቀዳሚነት የሚያነሱት ነጥብ የግድቡን ግንባታ መደገፍ ለሱዳን የፖለቲካ ውሳኔ ሳይሆን የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን ነው። "ትልቅ ጥቅም ነው የሚያገኙት ያለምንም ኢንቨስትመንት" ይላሉ።

ለአል-ባሽር ከሥልጣን መውረድ ምክንያት የሆነው ተቃውሞ በዳቦ ውድነት ፤ በኑሮ ውድነት የተቀሰቀሰ ነው። ግድቡ ደግሞ ለዚህ ጥያቄ በአጠቃላይ ለሃገሪቱ የልማት ጥያቄ መልስ እንደሚሆን አቶ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ።

አቶ ፈቅአህመድ እንደሚያስረዱት ግድቡ ለሱዳን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው፣ ያለ ምንም ወጪ እስከ ሶስት ሺህ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በርካሽ ሊገዙ ይችላሉ። በዚህ ደግሞ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ሊያነቃቁ፣ ግብርናና ዓሣ እርባታቸውን ሊያስፋፉ ይችላሉ።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?

ይህ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ትልቁን የነዳጅ ሃብቷን ይዛ በመገንጠሏ 'አግኝቶ ማጣት' እንደሚሉት ለሆነችው ሱዳን ከሰማይ እንደሚወርድ መና ሊቆጠር ይችላል።

ግድቡ ሱዳንን የማትወደው እንግዳ ከሆነባትና በየዓመቱ ከሚጎበኛት ጎርፍም ይታደጋታል። ጎርፉ የሚያመጣውን ደለል ከግድቦችና ቦዮች ለመጥረግ በየዓመቱ እስከ ሰባ ሚሊየን ዶላር ከመክሰርም ያድናታል።

ስለዚህም ምንም ዓይነት መንግሥት ቢመጣ ከዚህ ከፍተኛ ጥቅም የሚበልጥበትና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ይኖራል ብለው እንደማያምኑ አቶ ፈቅአህመድ ያስረግጣሉ።

በተመሳሳይ በአባይ ጉዳይ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖም ግድቡን መደገፍ የብሔራዊ ጥቅም እንጂ የፖለቲካ ውሳኔ ባለመሆኑ ሱዳን በአቋሟ ፀንታ ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፏን እንደምትቀጥል ያምናሉ።

ነገር ግን ለመጭው የሱዳን መንግሥት የህዳሴው ግድብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል አይሆንም የሚለው በሂደት የሚታይ እንደሆነ ይገልፃሉ ዶ/ር ያዕቆብ።

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አዲስ ሃሳብ አቀረበች

"ለዚህ ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ነው አቋማቸውን የማይቀይሩት" ሲሉም ያስረግጣሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ያለችው ሱዳን ገና መንግሥት እስክታቋቁም የሚወስደው ጊዜ በተለይም በሂደት ላይ ያለው የሦስትዮሽ ድርድር ላይ የተወሰነ የማዘግየት ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይናገራሉ።

እርሳቸው በጠቀሷቸው ምክንያቶች ሱዳን ለእራሷ ስትል የአቋም ለውጥ አታደርግም ተብሎ ቢታመንም ግብፅ የአሁኑን የሱዳን ፖለቲካዊ ለውጥ እንደሚያመቻት ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት ምን ድረስ ሊሄድ ይችላል? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።

ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ግብፅ ሱዳን ላይ በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ጫና ስታሳድር እንደነበር የሚናገሩት አቶ ፈቅአህመድ የግብፅ ጫና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይናገራሉ።

"ግብፆች አሁን ተጠናክረው ነው የሚንቀሳቀሱት። ጫናቸውም ሱዳን ላይ ይበረታል" ይላሉ።

Image copyright Getty Images

ነገር ግን እስከ ዛሬም ሱዳን ለህዳሴው ግድብ ድጋፏን ስትሰጥ የቆየችው የግብፅን ጫና ተቋቁማ ስለሆነ ከአሁን በኋላም በዚሁ ትቀጥላለች ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ግብፅ ከጅምሩ ሱዳንም ኢትዮጵያም ላይ ጫና ለመፍጠር ከመሞከር ወደ ኋላ ብላ እንደማታውቅ የሚያነሱት ዶ/ር ያዕቆብ በቀጣይ የግብፅ ተፅዕኖ ስኬት የሚወሰነው ከምንም በላይ በኢትዮጵያ ጥንካሬ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህ ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸውን ይጠቅሳሉ።

"ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሥራት ያላት አቅምና ቁርጠኝነት ነው" የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ ግብፅ በሱዳንም በኩል ሆነ በቀጥታ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ተፅዕኖ እንደ ከዚህ በፊቱ እንደሚቀጥል ያመለክታሉ።

ሌሎቹስ የተፋሰሱ ሃገራት በአቋማቸው እንደፀኑ ናቸው? ለአቶ ፈቅአህመድ ያነሳነው ጥያቄ ነበር። እርሳቸው በግልፅ የአቋም ለውጥ ያሳየ ሃገር እንደሌለ ይገልፃሉ። ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ኡጋንዳ ላይ የተፈረመውን የአባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ከአስራ አንዱ የተፋሰሱ ሃገራት የተወሰኑት በሦስት ወራት ውስጥ በፓርላማቸው ሲያፀድቁት ቀሪዎቹ እስከ አሁንም ሳያፀድቁት ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይህ መዘግየት ደግሞ እንዴት ነው ነገሩ የሚያስብል ነገር ነው። አቶ ፈቅአህመድ ደግሞ ይህን ስምምነት ብቻ በመመልከት የማፅደቁ ሂደት ዘግይቷል ሊባል ቢችልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ተመሳሳይ ስምምነቶች እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚወስዱ ይናገራሉ። የዚህ ዓይነቱ ድርድር እስከ 40 እና 50 ዓመት የፈጀባቸው ሃገራት መኖራቸውንም ይናገራሉ።

ኬንያ ስምምነቱን ለማፀደቅ ሶስት ጊዜ ፓርላማ አድርሳ መመለሷ በደቡብ ሱዳንም በሃገሪቱ የፖለቲካ በተመሳሳይ ሰነዱ ፓርላማ ደርሶ በተደጋጋሚ መመለሱ የሚታወስ ነው።

ስለአዲሱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ጥቂት እንንገርዎ

የተፋሰሱ ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች በየዓመቱ እየተገናኙ የሚወያዩ ሲሆን ያለፈው ስብሰባ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 አስረኛው ወር በቡጁምቡራ ነበር የተካሄደው።

የትብብር ማዕቀፉን ሱዳን ፣ ግብፅና ኮንጎ ጨርሶ አልፈረሙም። ከፈረሙት ሃገራት መካከል ደግሞ ሦስቱ ማለትም ኢትዮጵያ፣ታንዛኒያና ኡጋንዳ በፓርላማቸው ያፀደቁት ሲሆን ተጨማሪ ሦስት ሃገራት ቢያፀድቁት ለአፍሪካ ሕብረት በማቅረብ ከፍተኛ ትብብር ማድረግ የሚረዳቸውን ኮሚሽኑን ማቋቋም ይችላሉ። የትብብር ማዕቀፉን ፈርመው እስካሁን ያላፀደቁ ሃገራት ኬንያ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲና ሩዋንዳ ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች