በጦላይ የኦነግ ሠራዊት አባላት ላይ የተከሰተው ምንድን ነው ?

ድንገት የወደቁ የኦነግ ሰራዊት አባላት

ከባለፈው እሁድ ጀምሮ የጤና እክል ገጥሟቸው ሆስፒታል እየገቡ ያሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወታደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው።

ወታደሮቹ ቁርስ ተመግበው ሲነሱ ብዙ እራሳቸውን እየሳቱ መውደቅ መጀመራቸው መነገሩ ይታወሳል። ወታደሮቹ ጨምረውም የቀረበላቸው ሻይ ውስጥ ነጭ ባዕድ ነገር መመልከታቸው እና የተለየ ጠረን እንዳለው ጨምረው ተናግረዋል።

"ሻይ በምንጠጣበት ብርጭቆ ስር ነጭ ዱቄት የሚመስል ነገር አግኝተናል፤ ይህንንም ለማሰልጠኛው አስተዳደሮች አሳይተናል" ሲል አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የኦነግ ሠራዊት አባል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ትጥቅ የፈቱ የኦነግ ወታደሮች የረሃብ አድማ ላይ ናቸው

የጤና እክል በገጠማቸው የሠራዊቱ አባላት ላይ የሚታዩበት ምልክት ምን እንደሆነ ሲናገር "የአፍ ድርቀት፣ የሆድ ቁርጠት፣ ሆድ የማቃጠል ስሜት፣ ከደም ጋር የተቀላቀለ ትውከትና የፊት መገርጣት ናቸው" ብሏል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ረታ በላቸው፤ በጦላይ በሚገኙ የኦነግ ወታደሮች ላይ ያጋጠመው የጤና ችግር መንስዔ እየተጣራ ነው ያሉ ሲሆን የደረሰባቸው የጤና እክል ግን ለህይወት አስጊ አይደለም ብለዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ከሆነ 134 የኦነግ ወታደሮች በወሊሶ ቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ የጦላይ ማሰልጠኛ አስተዳደሮች ጉዳት አስከተለ የተባለውን ሻይ ቀምሰው ምን የደረሰባቸው ነገር የለም ብለዋል። ''እኛ የቀረበላቸው ሻይ ውስጥ መርዝ ተጨምሯል ብለን አናምንም፤ ምርመራ እየተካሄደ ነው። እንደተባለው መርዝ ተጨምሮ ከተገኘ ግን ጠፋተኛው ላይ እርምጃ ይወሰዳል።''

በዚሁ ሆስፒታል እየታከመ የሚገኘው ሌላኛው የሠራዊቱ አባል ኢብሳ በበኩሉ የተሰጣቸውን ሁሉ ተመግበው ቢሆን ኖሮ ጉዳቱ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ገልፆ "ሁላችንም እናልቅ ነበር" በማለት ተናግሯል።

«ኦነግ ሀገር ለመገንጠል ነው የምሠራው ብሎ አያውቅም» ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)

"ይሄ ነገር የመርዝ ሽታ አለው ብዬ ስላስቆምኩዋቸው ሻዩን አልጨረሱትም ነበር። ገሚሱ ቀምሰው ብቻ ስለሆነ የተዉት በዚያ መንገድ ነው የተረፍነው" ይላል።

"እከሌ ብለን ማንም ላይ ጣታችንን ባንቀስርም ህብረታችንን የማይወዱ ሰዎች እንዳሉ እንጠረጥራለን። ነገር ግን ግቢው ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ምንም አይነት ግጭት የለንም" ብሏል።

የህክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

ወሊሶ በሚገኘው የቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታል ሃኪም የሆኑት ዶ/ር አብዱላቲፍ ይሲያቅ እስከ ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት ድረስ 154 የኦነግ ሠራዊት አባላት ህክምና እየተደረጋለቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"በእኛ ምርመራ መሰረት የምግብ መበከል (መመረዝ) ሳይሆን ራሱን የቻለ መርዝ ተጨምሮበት እንደሆነ ነው የሚያሳየው። የሠራዊቱ አባላትም መርዝ እንደሸተታቸው ተናግረዋል" ብለዋል።

ዶ/ሩ ጨምረውም ታካሚዎች ራስ ምታት፣ የሆድ ቁርጠት፣ ሆድ የማቃጠል ስሜት፣ ከደም ጋር የተቀላቀለ ትዉከትና የፊት መገርጣት ምልክቶች እንደታየባቸው በመናገር እነዚህም የመርዝ ምልክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ አዲስ የጥላቻ ንግግር ህግ አያስፈልጋትም” አቶ አብዱ አሊ ሂጂራ

የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው 136 የኦነግ ሠራዊት አባላት በጤና እክል ምክንያት በወሊሶ ሉቃስ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንና የከፋ የጤና ችግርም እንደሌለ ለመንግሥት ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በመግለጫቸው ጨምረው በሠራዊቱ አባላት ላይ የምግብ መመረዝ ደርሶባቸዋል፤ ሠራዊቱ ላይም ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው እየተባለ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው ብለዋል።

ያጋጠመውን የጤና እክል መንስኤም ለማጣራት ፖሊስና የሚመለከታቸው አካላት ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀው መንስኤውም ሲታወቅ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ነው።