ታሪካዊው የፈረንሳይ ካቴድራል ኖትረ ዳም በእሳት ጋየ

ኖተርዳም Image copyright Getty Images

በፓሪስ እምብርት የሚገኘው ጥንታዊው እና ታሪካዊው ኖትረ ዳም ካቴድራል ትናንት ነበር በእሳት የጋየው። በእሳት ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑኤል ማክሮ ኖትረ ዳምን መልሰን እንገነባዋለን ሲሉ ተደምጠዋል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች በወሰዱት እርምጃ የካቴድራሉን ግንብ እና ሁለት ማማዎች ከነበልባሉ መታደግ የቻሉ ሲሆን ጣሪያው እና አናቱ ግን ፈርሷል።

850 ዓመታትን ያስቆጠረው ኖትረ ዳም ካቴድራል ፓሪስ መሃል ከተማ ይገኛል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን መቆጣጠር የቻሉት እሳት መነሳቱ ሪፖርት ከተደረገ ከ9 ሰዓታት በኋላ ነበር። የእሳቱ መነሻ እስካሁን በግልፅ ባይነገርም የሃገሪቱ ባለስልጣናት ግን በካቴድራሉ እየተካሄደ ካለው እድሳት ጋር አገናኝተውታል።

በሰሜን ተራሮች ፓርክ በሄሊኮፕተር ውሃ እየተረጨ ነው

ሩሲያዊው ቄስ በባለቤታቸው "ሀጥያት" ለስደት ተዳረጉ

የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢህአዴግን ወዴት ይመራው ይሆን?

ፕሬዝደንት ማክሮ በአደጋው ስፍራ ተገኘተው በሁኔታው በጣም ማዘናቸውን ገልፀው የእሳት አደጋው እንዳይከስት ማድረግ እንደሚቻል በመጠቆም፤ ለኖትረ ዳም መልሶ ግንባታ ዓለም አቀፍ ጥሪ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ማክሮ ስሜታዊ ሆነው በሰጡት መግለጫ ''መልሰን እንገነባዋለን። ኖትረ ዳም የታሪካችን አካል ነው። የፈረንሳይ ሕዝብ የሚጠብቀውም ይህንኑ ነው'' ያሉ ሲሆን ከአሁኑ ኖትረ ዳምን መልሶ ለመገንባት በርካቶች ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል።

የጉቺና የሌሎች ፋሽን ምርቶች ባለቤት የሆነው ፈረንሳዊው ቢሊየነር ፍራንሷ-ኦንሪ ፒኖ፤ ለኖትረ ዳም ግንባታ 100 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ትናንት ሰኞ ምሽት 2፡30 ላይ የጀመረው እሳት በፍጥነት ወደ ጣሪያው በመዛመት ከመስተዋት የተሠሩ መስኮቶቹን፣ ከእንጨት የተሠሩ የውስጥ ንድፎቹን፣ ጣሪያውን እና ማማውን አውድሟል።

እሳቱን ለመቆጣጠር 500 የሚሆኑ የእሳት አደጋ ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆኑ አንዱ በእሳቱ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቧል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ በኖትረ ዳም ካቴድራል ውስጥ የነበሩ ውድ የጥበብ ሥራዎች እና ኃይማኖታዊ ቁሶችን ማዳን መቻላቸውም ተነግሯል። ከእሳት ከተረፉት ኃይማኖታዊ ቁሶች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት የተደረገለት የእሾህ አክሊል ይገኝበታል።

Image copyright Getty Images

ትረ ዳም ለፈረንሳዊያን ምናቸው ነው?

ኖትረ ዳም ካቴድራል ለ9 ሰዓታት ሲቃጠል የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ እየዘገቡት ነበር። ይህን ሲመለከቱ የነበሩት የታሪክ ምሁር ካሚይ ፓስካል ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ '' ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዓለም ደስታ እና ሃዘን በኖትረ ዳም ደውል ታውጇል። እያየን ባለነው ነገር እጅግ በጣም ተደናግጠናል'' ብለዋል።

ኖትረ ዳም ለፈረንሳውያን ሃገራዊ አርማቸው ተደርጎ ይወሰዳል። ኖትረ ዳም ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መሃል ፓሪስ ላይ ቆሟል። በርካቶች የፈረንሳይ መለያ አድርገው የሚወስዱት የኤይፈል ማማ እንኳ ዕድሜው ከ100 ዓመት ፈቅ ቢል ነው።

ኖትረ ዳም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጉዳት ሳያስተናግድ አልፏል። በፈረንሳይ ሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥም ስሙ ሳይጠቀስ አያልፍም።

ኖትረ ዳም ለ9 ሰዓታት ያክል በእሳት ሲነድ በርካታ ፈረንሳውያን አደጋው ስፍራ በመገኘት ቆመው በዝምታ ይመለከቱ ነበር። ሌሎች ይዘምራሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ፀሎት ያደርሳሉ። በፓሪስ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ደውል ሲያሰሙ አመሹ።

ኖትረ ዳም በዓመት 13 ሚሊዮን ሕዝብ ይጎበኛዋል።

ዶናልድ ትራምፕ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬዛ ሜይ፣ ዩኔስኮ፣ የጃፓን መንግሥት፣ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚንስትር እና የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሃዘናቸውን ከገለፁ ግለሰቦች እና ተቋማት መካከል ይገኙበታል።

ተያያዥ ርዕሶች