በጋምቤላ ክልል 89 ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ማምለጣቸው ተሰማ

የጋምቤላ ከተማ Image copyright Gambella Community Development of Canada

ትናንት ከረፋዱ 4፡30 አካባቢ 89 ታራሚዎች ከጋምቤላ ማረሚያ ቤት ማምለጣቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ አቶ ኡዶል ለጉዋ ለቢቢሲ ገለፁ።

እርሳቸው እንደሚሉት በማረሚያ ቤቱ በመጠጥ ውሃ ሽሚያ ምክንያት በሁለት ታራሚዎች መካከል ግጭት ይነሳል። በወቅቱ የነበሩት ስድስት ተረኛ ጠባቂዎች ግጭቱን ለማብረድ በመካከላቸው ይገባሉ። ይሁን እንጂ ታራሚዎቹ ፖሊሶቹን በመደብደብ በዋናው በር በኩል አምልጠዋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢህአዴግን ወዴት ይመራው ይሆን?

አቶ ኡዶል ለጊዜው የደረሳቸው መረጃ ይሄ ይሁን እንጂ ድርጊቱ ለመጥፋት ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት ሳይሆን እንደማይቀር መንግሥት ጥርጣሬ አለው ብለዋል።

"የውሃ እጥረት በሌለበት አካባቢ የመጠጥ ውሃ የግጭት መነሻ መሆኑ በራሱ ተቀባይነት" የለውም ሲሉ ያክላሉ።

316 ታራሚዎች በሚገኙበት በዚህ ማረሚያ ቤት 14 ተረኛ ጠባቂዎች የሚመደቡ ሲሆን ትናንት ግን ስድስት የጥበቃ ፖሊስ አባላት ብቻ እንደነበሩ ታውቋል። ቀሪዎቹ ስምንት ተረኛ ጠባቂዎች እስረኞች ወደ ፍርድ ቤቶች ለማድረስ ሄደው እንደነበር መስማታቸውን ኃላፊው ነግረውናል።

ትውስታ- የዛሬ 20 ዓመት ኢትዮጵያ ሞባይል ስልክን ስትተዋወቅ

አቶ ኡዶል በስፍራው ሄደው ያነጋገሯቸው ፖሊሶችም "በሁለቱ ታራሚዎች መካከል ያለውን ግጭት ለመፍታት በመካከል ስንገባ በድንጋይ ደብድበውን ጥለውን ወጡ" ሲሉ ገልፀውላቸዋል።

እስረኞቹ በግድያና በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው ሲሆኑ የፖለቲከኛ እስረኞች አለመሆናቸው ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ የከሸፈች ሀገር እየሆነች ነው" ሻለቃ ዳዊት

ከእስር ቤቱ አምልጠው የወጡት ታራሚዎች እስካሁን ያልተያዙ ሲሆን ምርመራና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል ኃላፊው።

በአካባቢው የሙቀት ወቅት በመሆኑ እስረኞች ከክፍላቸው ወጥተው በግቢው ውስጥ ባሉ ቦታዎች እየተዘዋወሩ መቆየት የተለመደ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ