ባህሬን የ138 ሰዎችን ዜግነት ነጠቀች

ባህሬን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በባህሬን የሚገኝ ፍርድ ቤት በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 139 ሰዎችን ወደ ማረሚያቤት እንዲገቡ በመወሰን 138ቱ ደግሞ የባህሬን ዜግነታቸውን ነጥቋል።

69 ሰዎች የሞት ፍርድ ሲበየንባቸው ቀሪዎቹ ደግሞ ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ተፈርዶባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

የሱኒ እስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነችው ባህሬን፣ የሺያ ተከታይ የሆነችው ኢራንን ከመሰሎቿ ጋር በመሆን በባህሬን መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖር እየሠራች ነው የሚል ውንጀላ አቅርባ ነበር።

58 ተጠርጣሪዎች በሌሉበት የፍርድ ሂደቱ የተከናወነ ሲሆን የባህሬን ዜግነታቸውን የተነጠቁት ሰዎች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

ባሳላፍነው መስከረም ነበር የባህሬን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ''የባህሬን ሂዝቦላህ'' ከተባለው አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 169 ሰዎች የክስ ሂደት እየተከታተለ እንደሆነ ያስታወቀው።

ተጠርጣሪዎቹም ፈንጂዎችን በመቅበር፣ የግድያ ሙከራ በማድረግ፣ ንብረት በማውደምና ህገወጥ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር ክሶች ቀርበውባቸዋል።

ማክሰኞ ዕለትም ፍርድ ቤቱ ለመጨረሻ ክስ የቀረቡት 139 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ፍርድ የበየነ ሲሆን 96 ተጠርጣሪዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው ከ700 ሺ ብር በላይ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።

ለፍርድ ከቀረቡት 138ቱ ያለምንም ይግባኝ የባህሬን ዜግነታቸው ሙሉ በሙሉ የተገፈፈ ሲሆን አንድ ግለሰብ ግን የእስር ፍርድ ብቻ ተበይኖበታል።

የዓለማቀፉ ሰብአዊ መብት አዋጅ መሰረት ግን ማንኛውም ግለሰብ ዜግነት የማግኘት ሙሉ መብት ያለው ሲሆን በማንኛውም ሁኔታ ዜግነቱን መነጠቅም ሆነ ወደ ሃገሩ መግባት እንደሚችል ተደንግጓል።

በአውሮፓውያኑ 2018 የባህሬን መንግስት በተመሳሳይ መልኩ ስምንት ዜጎቹን ዜግነታቸውን በመንጠቅ ወደ ኢራን አባሯቸው ነበር።