ስለ እንቅልፍ የተሳሳቱ አመለካከቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስለ እንቅልፍ በስፋት የሚነገሩ የተሳሳቱ ነገሮች የሰወችን ጤናና ስሜት እየጎዱ እድሜንም እያሳጠሩ እንደሆነ አጥኚዎች አስታወቁ።
የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ቡድን የሰራው ጥናት ግኝቶች ጠንካራ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ያላቸው እንደሆኑ የተገለፀ ሲሆን ስለ እንቅልፍ የሚነገሩ የተሳሳቱ ነገሮችን ማረም እጅግ አስፈላጊ ነው ተብሏል።
ጥናቱ ስለ እንቅልፍ በስፋት የሚነገሩ ያላቸውን የተሳሳቱ ነገሮችን አንድ በአንድ ይዘረዝራሉ።
አምስት ወይም ከዚያ ያነሰ እንቅልፍም ጤናማ ነው
የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር የእንቅልፍ ሰዓታቸው በጣም አጭር እንደነበር ይነገራል። የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክልም እንቅልፍ ላይ እንደ ታቸር እንደሆኑ ይነገራል። ብዙ የንግድ ሰዎችና ስራ ፈጣሪዎችም እንዲሁ መኖናቸው እንደሆኑ ይነገራል።
ነገር ግን ተመራማሪዎቹ በተከታታይ አምስት ወይም ከዚያ ያነሰ ሰዓት እንቅልፍ ጤናማ ነው የሚለው እምነት የተሳሳተና ለጤናም አደገኛ ነው ይላሉ።
ከተመራማሪዎቹ አንዷ የሆኑት ዶ/ር ሬቤካ ሮቢንስ በዚህ ምክንያት ሊያጋጥሙ ይችላሉ ካሏቸው ነገሮች ድንገተኛ የልብ ህመም፣ስትሮክና በህይወት የመቆየት እድሜ ማጠር ይገኙበታል።
ይልቁንም ዶክተሯ ሁሉም ሰው ያልተቋረጠ የሰባት ወይም የስምንት ሰአት እንቅልፍ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
አልኮል ለእንቅልፍ ይረዳል
ወደ አልጋ ከመሄድ በፊት አልኮል አንድ ሁለት ማለት ጥሩ እንቅልፍ ያስተኛል የሚባል ቢሆንም ይህ ፍፁም ትክክል አይደለም ይላሉ ተመራማሪዎቹ።
ወይን፣ ውስኪም ሆነ ቢራ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት አያግዙም እንደ ተመራማሪዎቹ
"ወዲያው እንቅልፍ ለመተኛት ይረዳ ይሆናል ።ነገር ግን የሙሉ ምሽት እንቅልፍን ይረብሻል" ይላሉ ዶ/ር ሮቢንስ።
በተለይም ለትምህርትና ትውስታ የሚጠቅመውን የእንቅልፍ ሂደት REM (rapid eye movement) ያውካል ይላሉ።
አልኮል የሚፈጥረው የፊኛ መወጠርም ሌላ ለእንቅልፍ መረበሽ ምክንያት ነው። በጥቅሉ ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ አልኮል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ይደመድማሉ ተመራማሪዎቹ።
ቴሌቪዥን ማየት ዘና ያደርጋል
ብዙዎች ቲቪ ተመልክተው ዘና ቢሉ ጥሩ እንቅልፍ ሊተኙ እንደሚችሉ ያምናሉ። ዶ/ር ሮቢንስ ግን ቲቪ ለውጥትና እንቅልፍ ለማጣት ምክንያት ነው ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ዜና ይባል ፊልም ላይ የሚታዩት ነገሮች ዘና ከማድረግ ይልቅ የማስጨነቅ ነገራቸው የበዛ ነው ይላሉ።
እንደ ስማርት ስልኮችና ታብሌቶች ሁሉ ቲቪዎች የሚለቁት ሰማያዊ ብርሃን የሰውነትን የእንቅልፍ ሆርሞን የሆነው ሜላቶኒንን የማምረት ሂደት ያዘገያል የሚለው ደግሞ ተመራማሪዎቹ የሚያነሱት ሌላ ነጥብ ነው።
እንዲሁ አልጋ ላይ መተኛት ለእንቅልፍ ይረዳል
ምንም እንኳ እንቅልፍ ባይመጣ መተኛት አለብኝ ባሉት ሰዓት ወደ አልጋ ሄደው እንቅልፋቸውን በመጠባበቅ ለመተኛት የሚጠባበቁ ብዙዎች ናቸው።
ዶ/ር ሮቢንስ ግን ይህ ትክክል አይደለም አእምሯችን አልጋን እንቅልፍ ከማጣት ጋር ያገናኘዋል ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ጤናማ እንቅልፍ ያላቸው ሰዎች በእንቅልፍ ለመውደቅ አስራ አምስት ደቂቃ ብቻ ይበቃቸዋል።
ሰዎች ወደ አልጋቸው ሄደው ለመተኛት ከአስራ አምስት ደቂቃ በላይ ከወሰደባቸው አልጋቸው ውስጥ መቆየት ሳይሆን ያለባቸው ተስተው የመኝታቸውን ሁኔታ መቀየር ወይም ማሰብ የማይጠይቅ ሌላ ነገር እንዲያደርጉ ዶክተሯ ይመክራሉ።
ማንኮራፋት ምንም ችግር የለውም
ማንኮራፋት ጉዳት ባይኖረውም አንድ የእንቅልፍ ማጣት ምልክት ነው።
በማንኮራፋት ሰዎች ድንገት መተንፈስ እንዳይችሉ ሊያደርግ ይችላል።
በተለይም በከፍተኛ ድምፅ ማንኮራፋት አደገኛ ነው ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

• የስዊዘርላንድ መንግሥት ቡና ለህይወት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገለፀ
በነፍስ ወከፍ 9 ኪሎ ግራም ቡና የጠጣሉ። የስዊዘርላንድ መንግስት ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት የሚያከማቸውን ቡና ሊያቆም ነው።