ማክሮን፡ ኖትረ ዳም በተሻለ ሁኔታ ውብ ተደርጎ ይገነባል

ካቴደራሉ ከመቃጠሉ በፊት፣ በቃጠሎ ወቅት እና ከቃጠሎ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ካቴደራሉ ከመቃጠሉ በፊት፣ በቃጠሎ ወቅት እና ከቃጠሎ በኋላ

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ኖትረ ዳም ካቴድራል ''በተሻለ ሁኔታ ውብ'' እድርግን እንገነባዋለን አሉ። ማክሮን ጨምረውም ግንባታው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በፓሪስ እምብርት በሚገኘው ጥንታዊው እና ታሪካዊው ካቴድራል ሰኞ ምሽት እሳት ተነስቶ መስኮቶቹ፣ ጣሪያው እና ማማው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

850 አመት ያስቆጠረው ካቴድራሉ በእሳቱ ሙሉ በሙሉ ለመውደም ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ነበር እሳቱ የጠፋው።

ማክሮን ኖተረ ዳም በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ማየት ቢሹም፤ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን መልሶ ግንባታው ከ10-15 ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል ይላሉ።

50 ሰዎች የእሳቱን መነሾ ያጣራሉ። አቃቤ ህግ እሳቱ ሆነ ተብሎ የተቀስቀሰ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ የለም፤ ጉዳዩም እንደ አደጋ ተደርጎ ነው እየተወሰደ ያለው ብለዋል።

ካቴድራሉን መልሶ ለመገንባት ግለሰቦች እና ኩባንያዎች እስካሁን በጠቅላላው 800 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን መቆጣጠር የቻሉት እሳት መነሳቱ ከተነገራቸው ከ9 ሰዓታት በኋላ ነበር።

ትናንት ሰኞ ምሽት 2፡30 ላይ የጀመረው እሳት በፍጥነት ወደ ጣሪያው በመዛመት ከመስተዋት የተሠሩ መስኮቶቹን፣ ከእንጨት የተሠሩ የውስጥ ንድፎቹን፣ ጣሪያውን እና ማማውን አውድሟል።

እሳቱን ያደረሰውን ጥፋት በትክክል ለመመዘን ባለሙያዎች እስካሁን ወደ ውስጥ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። የእሳት አደጋ ሰራተኞች ድሮን (በራሪ ካሜራ) ወደ ውስጥ በመላክ የደረሰውን ጉዳት መቃኘት ችለዋል።

በአሁኑ ሰአት ቃጠሎው ያደረሰውን ጉዳት በገንዘብ መተመን እንደማይቻልም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ማክሮን በትናንትናው ምሽት ንግግራቸው የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር የወሰዱትን እርምጃ አድንቀዋል።

ኖትረ ዳም ለፈረንሳዊያን ምናቸው ነው?

ኖትረ ዳም ካቴድራል ለ9 ሰዓታት ሲቃጠል የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ እየዘገቡት ነበር። ይህን ሲመለከቱ የነበሩት የታሪክ ምሁር ካሚይ ፓስካል ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ '' ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዓለም ደስታ እና ሃዘን በኖትረ ዳም ደውል ታውጇል። እያየን ባለነው ነገር እጅግ በጣም ተደናግጠናል'' ብለዋል።

ኖትረ ዳም ለፈረንሳውያን ሃገራዊ አርማቸው ተደርጎ ይወሰዳል። ኖትረ ዳም ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መሃል ፓሪስ ላይ ቆሟል። በርካቶች የፈረንሳይ መለያ አድርገው የሚወስዱት የኤይፈል ማማ እንኳ ዕድሜው ከ100 ዓመት ፈቅ ቢል ነው።

ኖትረ ዳም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጉዳት ሳያስተናግድ አልፏል። በፈረንሳይ ሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥም ስሙ ሳይጠቀስ አያልፍም።

ኖትረ ዳም ለ9 ሰዓታት ያክል በእሳት ሲነድ በርካታ ፈረንሳውያን አደጋው ስፍራ በመገኘት ቆመው በዝምታ ይመለከቱ ነበር። ሌሎች ይዘምራሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ፀሎት ያደርሳሉ። በፓሪስ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ደውል ሲያሰሙ ነበር።

ኖትረ ዳም በዓመት 13 ሚሊዮን ሕዝብ ይጎበኛዋል።

ካቴድራሉ ውስጥ የነበሩት እና ከእሳት የተረፉት የጥበብ ስራዎች እና ሃይማኖታዊ ቁሶች ሉቭ ወደተሰኘው ሙዚየም በጊዜያዊነት እንሚሸጋገሩ ተነግሯል። ከእሳቱ ከተረፉ ሃይማኖታዊ ቁሶች መካከል ኢየሱስ ክርስቶች ከመሰቀሉ በፊት ተደርጎለት የነበረው የእሾህ አክሊል ይገኝበታል።