ታዋቂው ኩባንያ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችን ''ይበድላል'' ተባለ

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በአሠሪዎቻቸው በደል ይደርስባቸዋል ተባለ።
የፋሽን ምርቶች አምራቹ ፒቪኤች (PVH) በስሩ የሚገኙና በኢትዮጵያ እየሠሩ ያሉ ተቋሞቹ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ይዘልፋሉ፣ አድልዎ ይፈፀምባቸዋል እንዲሁም በሰዓት እስከ 12 የአሜሪካ ሳንቲም (3 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ) ብቻ የሚከፈላቸው ሠራተኞች አሉ መባሉን ተከትሎ ፒቪኤች (PVH) ምርመራ እንደሚያደርግ ሮይተርስ ያነጋገራቸው የኩባንያው የሥራ ኃላፊ አስታወቁ።
ፒቪኤች (PVH) ኩባንያ ቶሚ ሂልፊገር እና ካልቪን ክሌን የመሳሰሉ ታዋቂ ኩባንያዎች ባለቤት ነው።
በኢትዮጵያ ለፒቪኤች (PVH) ኩባንያ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለሚያመርቱ ድርጅቶች እየሠሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ በደል እንደሚፈፀምባቸው መቀመጫውን አሜሪካን ሃገር ያደረገ ዎርከር ራይትስ ኮንሶርቲየም (Worker Rights Consortium) የተባለ ድርጅት ባደረገው ጥናት አጋልጧል።
ዎርከር ራይትስ ኮንሶርቲየም ገለልተኛ የሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ የሠራተኞችን መብት የሚቃኝ እና የሥራ ቦታ ሁኔታን የሚመረምር ድርጅት ነው።
ድርጅቱ እንደሚለው ለፒቪኤች (PVH) ኩባንያ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለሚያመርቱ ኩባንያዎች እየሠሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ያለ ክፍያ ትርፍ ስዓት እንዲሠሩ ይገደዳሉ እንዲሁም በሥራ ቦታቸው ላይ ውሃ በመጠጣታቸው ብቻ ከደሞዛቸው ተቆራጭ ይደረጋል ይላል።
የዎርከር ራይትስ ኮንሰርቲየም ምረመራ ውጤት እንዳመላከተው ሥራ ቀጣሪ ኃላፊዎች በሥራ ቅጥር ወቅት ሴት ሠራተኞችን ሲቀጥሩ ነብሰጡር መሆን አለመሆናቸውን እጃቸውን ሆዳቸው ላይ በማድረግ ለማረጋጋጥ ይጥራሉ።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ በሠራተኞች ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት ለማረጋጋጥ ቢቢሲ ሁለት በፓርኩ የሚሠሩ ሠራተኞችን አነጋግሯል። ስሟ እንዲጠቀስ ያለፈለገች ወጣት ሠራተኛ፤ በፓርኩ ውስጥ ለሚገኘው አንድ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ እንደምትሠራ ትናገራለች።
ተማሪ ሳለች በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ድረስ በመምጣት የሥራ ቃለ መጠይቅ አድርጋ ከምርቃት በኋላ ሥራ እንደ ጀመረች ታስረዳለች።
''እርጉዝ ብቻ ሳይሆን እናቶችንም አይፈለጉም። ለፈተና ሲቀርቡ ልጅ እያላቸው ልጅ የለኝም ብለው የሚቀጠሩ አሉ'' በማለት ነብሰጡር እና የልጆች እናት የሆኑ ሴቶች በሥራው ላይ አድልዖ እንደሚፈፀምባቸው ታስረዳለች።
የቅርብ ኃላፊዎቿም ''የሥራው ባህሪ ለእርጉዞች እና ለእናቶች አይመችም'' የሚል ምክንያት እንደሚያቀርቡ ይህችው ወጣት ትናገራለች።
ያነጋገርነው ሌላው በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሚሠራ ወጣት፤ የሚከፈላቸው ክፍያ በሐዋሳ ከተማ ላይ ቤት ተከራይተው እና ወጪያቸውን ሸፍኖ ስለማያኖራቸው በቡድን ሆነው ቤት ተከራይተው ለመኖር መገደዳቸውን ይናገራል።
በሥራ ቦታው ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ፤ በ8 ሰዓት ልዩነት ሦስት ፈረቃ መኖሩን ተራ በደረሰ ቁጥር የምሽት ፈረቃን በ10 ብር ጭማሪ ብቻ እንዲሠሩ እንደሚገደዱ ይናገራል።
የዎርከር ራይትስ ኮንሰርቲየም ምርመራ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የፒቪኤች (PVH) ኩባንያ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ''ማናቸውም ዓይነት የመብት ጥሰቶች ተደርገው ስለመሆኑ ለማረጋገጥ አስቸኳይ እና ዝርዝር ምረመራ እናደርጋለን። የመብት ጥሰቶች ከደረሱም አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን'' ሲሉ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሌሊሴ ነሜ ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርክ እና መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በመጥቀስ ጉዳዩ የእርሳቸውን መሥሪያ ቤት እንደማይመለከት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሸን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መኮንን ኃይሌ በበኩላቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚሠሩ ሠራተኞች ላይ በደል ይፈፀማል የተባለው ከእውነተ የራቀ ነው ይላሉ።
አቶ መኮንን የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መከፈት ለአከባቢው ነዋሪዎች በተለይም ለወጣቶች ዕድል መክፈቱን በመናገር፤ በፓርኩ ውስጥ ብዙዎቹ ተቀጣሪዎች ሴቶችና ናቸው። ነብሰጡር እና እናቶች ላይ ይፈፀማል የተባለው ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ።
ሠራተኞች ከደምወዛቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እና የምግብ አገልግሎት ስለሚቀርብላቸው የተሻለ ተጠቃሚዎች ናቸው በማለት የዎርከር ራይትስ ኮንሶርቲየም የጥናት ውጤት እውነታውን እንደማያሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፌደራል እና የደቡብ ክልል የሠራተኛ እና ማህብራዊ መሥሪያ ቤቶች በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያደረግነው ጥረት ሊገኙ ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቷል። የሠራተኞች ፌዴሬሽንም ስለ ሠራተኞቹ ቅሬታ የሚያውቀው ካለ ለመጠየቅ ብንጥርም እነርሱም ሊገኙ አልቻሉም።
ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየት ለማካታት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ እና የሠራተኛ እና ማህበረዊ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ አመላክቷል።
በእሲያ የጉልበት፣ የጥሬ ግብዓት እና የግብር ወጪ መጨመርን ተከትሎ ግዙፍ ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ አፍሪካ አዙረዋል። ኢትዮጵያም የተመቻቸ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማቅረብ የግዙፍ ኩባንያዎችን ትኩረት ለመግኘት ትጥራለች።
ኢትዮጵያ የተተመነ ዝቅተኛ ክፍያ መጠን ባይኖራትም፤ ማንኛውንም ዓይነት ጥሰቶችን መፈፀም የሚከለክል የአሠራር ሥርዓት አላት።
ፒቪኤች (PVH) በዓለማችን ከሚገኙ ግዙፍ የአልባሳት አምራች ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ከሚጠጉ ሠራተኞቹ ባሳለፈነው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ 9.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰብ ችሏል።