"ሕግ ማጥናት ከተለየ መብት ወይም ገንዘብ ጋር አይገናኝም" ኪም ካርዲሽያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊቷ ሞዴል፣ የሚዲያ ባለሙያ እና ቱጃር ነጋዴ ኪም ካርዳሺያን ሕግ መማር መጀመሯን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች እየዘነቡባት ነው። ከአስተያየቶቹ መካከል አንዳንዶቹም ሕግ የምታጠናው ሃብታምና ዝነኛ ስለሆነች እንጂ ብቁ ስለሆነች አይደለም የሚለው ይገኝበታል።
ኪም የሕግ ባለሙያ ለመሆን ትምህርት የጀመረችው ባለፈው ሳምንት ነበር። የማጠናቀቂያ ፈተናዋን ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደምትወስድም ተነግሯታል።
እርሷ እንደምትለው ሕግ የማጥናቷ ጉዳይ ከዝነኝነት አሊያም ከቱጃርነት ጋር ፈፅሞ ሊገናኝ እንደማይችል ተናግራለች።
"ደስ ከሚያሰኘን ህልማችን ምንም ነገር ሊወስነን አሊያም ሊገታን አይገባም" ስትል ሕግ ማጥናት መፈለጓ ህልሟ እንጂ ዝነኝነት አለመሆኑን ተናግራለች።
ኪም ከሁለት የሕግ አስተማሪዎቿ፣ ጀሲካ ጃክሰን እና ኤሪክ ሀኒ ጋር የተነሳቻቸውን ፎቶዎች በግል ኢንስታግራሟ ገጿ ላይ ለጥፋ ነበር።
በዚህም ምክንያት በርካታ አስተያየቶችን ተመልክቻለሁ የምትለው ኪም "ወደ ሕግ ያመራኝ የተለየ መብት አሊያም ሃብታም ስለሆንኩ አድርገው የተሰጡ አስተያየት ተመልክቻለሁ፤ እውነታው ግን ይህ አይደለም" ብላለች።
ከእነዚህ መካከል አንድ ሰው በያዘችው ሙያ ብቻ እንድትቆይ አስተያየቱን ሰጥቷታል። እኔ ግን ትላለች ኪም፤ ማንም ሰው ህልሙንና ራዕዩን ከማሳካት የሚያግደው አንዳች ነገር እንደሌለ መረዳት አለበት ብላለች። እሷ እንዳደረገችው ሁሉ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ህልም ሊፈጥር ይችላል።
"ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሳምንት 18 ሰዓታት ትማራለች፤ በየወሩ የፅሁፍና የምርጫ ጥያቄዎችን መስራት ይጠበቅብኛል" ስትል የትምህርቱን ሂደት ገልፃለች።
ልምምዱ በዚህ መልክ ካጠናቀቀች የታዋቂው ተዋናይ ፣ የማስታወቂያና የሚዲያ ባለሙያ ኦጀ ሲምፕሰን ጓደኛና የእርሳቸውን የግድያ ሙከራ በተመለከተ ጠበቃ የነበሩትን የአባቷን ሮበርት ካርዳሺያን ፈለግ ትከተላለች።
ዝነኛዋ ካርዳሺያን ለብዙዎች ብዥታን የፈጠረውንና የኮሌጅ ትምህርቷን ሳታጠናቅቅ ህግ የምታጠናበትን ምክንያት አስረድታለች።
ብዥታው ትክክል መሆኑን ያረጋገጠች ሲሆን የኮሌጅ ትምህርቷን አለማጠናቀቋንም አረጋግጣለች። ነገር ግን" ህግ ለማጥናት 60 የትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚያስፈልግ ሲሆን ፤ እኔ ግን 75 ነበረኝ " ስትልም ትሟገታለች።
ኪም እንደምትለው ሕግ ለማጥናት የእረፍት ቀናቶቿን፣ ከልጆቿ ሰዓት በመሸራረፍ እየተጠቀመች እንደሆነ ተናግራለች።
በእርግጥ ብዙ ጊዜ እንደማልችል ተሰምቶኝ ነበር፤ ነገር ግን በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ድጋፍ አድርገውልኛል ስትልም አክላለች።