"ለውጡን ለማደናቀፍ ከተቻለም ለመቀልበስ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ" ኢህአዴግ

ኢህአዴግ

የፎቶው ባለመብት, EPRDF

የኢህአዴግ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያደርግ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን ከድርጅቱ የወጣው መግለጫ አመለከተ።

መግለጫው እንዳመለከተው ምክር ቤቱ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ሰፊ ውይይት ማድረጉን አመልክቶ "ለውጡ ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዳይጓዝ፤ ከተቻለም እንዲቀለበስ የሚጥሩ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን" ጠቅሷል።

በተጨማሪም ከፅንፈኛ ብሔረተኝነት፣ ሥርዓት አልበኝነትና የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ፈተናዎች የሃገራዊ አንድነት ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሶ "ይህንን በተባበረ ክንድ በመፍታት ለውጡን ማስቀጠልና ማስፋት ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው" ብሏል።

ምክር ቤቱ ባለፉት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን የገመገመ ሲሆን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን ጠቅሶ በተለይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ በሃገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ጉልህ ቦታ ያለው እንደሆነ አመልክቷል።

መግለጫው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል ካላቸው ጉዳዮች መካከል በድርጅቱ ውስጥ ስላለው ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት፣በአባል ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል ይታያል ያለውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየቱንና "ሃገርንና ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጥሯል" ሲል ጠቅሷል።

ምክር ቤቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አንስቶ የተወያየ ሲሆን የተወሰዱ እርምጃዎች የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን በማስተካከል ረገድ በጎ ሚና እንደነበራቸውና በተለይም የውጪ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል የተከናወነውን ተግባር ገምግሟል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና ችግሮች ያልተቀረፉ መሆናቸውን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ወስኗል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል "ማንኛውም ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልፅ ተለይተው በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸውና መንግሥትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ሃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባው የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል" ሲል መግለጫው አመልክቷል።

በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ምክር ቤቱ የተወያየበት ሲሆን ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመስለ አስፈላጊውን ጥረት እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።

የውጪ ግንኙነቱንም በተመለከተ ከሁሉም ጎረቤት ሃገራት ጋር መልካም ግንኙነት መመስረቱና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እየተካሄደ መሆኑን የጠቆመው የኢህአዴግ ምክር ቤት መግለጫ "በተለይ ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል" ብሏል።

የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ለውጦች እንዳሉ ጠቅሶ ነገር ግን "የወደፊት ተልዕኳችንን ለማሳካት የሚያግዙ መልዕክቶችን ከመቅረፅ ይልቅ ባለፉት ጉድለቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ብሶትን ማራገብ የሚታይበት በመሆኑ በቀጣይ መታረም እንደሚገባው" አሳስቧል።

ማህበራዊ ሚዲያውን በተመለከተም አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሶ "ዴሞክራሲውን የማቀጨጭ ሚናው እየጎላ መምጣቱን" ምክር ቤቱ መገምገሙን አንስቶ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባና እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮችን በሕግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነ ምክር ቤቱ እንዳመነበት በመግለጫው አመላክቷል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ሰኞና ማክሰኞ ባደረገው ስብሰባ ላይ በቀረበው ሰነድና ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ ውሳኔውን በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁም ተመልክቷል።