የአድዋ ማዕከል የአዲስ አበባ እምብርት ላይ ሊሰራ ነው

የምኒልክ ኃውልት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በጭቆና ስር ለነበሩ አፍሪካውያንም ሆነ ለጥቁር ህዝቦች የሰውነት ክብር መለኪያ የተረጋገጠባት የአድዋ ድል በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ይህንንም ለማጉላት ከሰሞኑ የአዲስ አበባ መስተዳድር የአድዋን ድል የሚዘክር ማዕከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የማዕከሉ አስፈላጊነት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቷ ካጠላባት መቃቃርና መከፋፈል ለማውጣት ህዝቡን የሚያስተሳስር ታሪክን ወደ ኋላ መቃኘት አስፈላጊ መሆኑ አንዱ ምክንያት መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ይናገራሉ።

በተለይም ዕድሜ፣ ብሔር፣ ፆታ፣ ሀይማኖት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው የተሰባሰቡባት አድዋ በታሪክም ሆነ የህዝቡን አንድነት ለመመለስ ከፍተኛ ሚና እንዳላት ኃላፊው ይናገራሉ።

"አድዋ የድል ትርክት ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የሰብአዊነትና ሌሎች ገዢ ሀሳቦችን ተምሳሌት ናት" የሚሉት ኃላፊው አድዋን ለመዘከር ምን አይነት ማዕከል ያስፈልጋል በሚለው ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያውን ምክረ ኃሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።

በምክረ ኃሳቡ መሰረት ማዕከሉ ሊያካትታቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል በወቅቱ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች፣ ስንቆች፣ ትጥቆች በአጠቃላይ የጦርነቱን ሁኔታ የሚያሳይ የጦርነቱ መዘክር ሙዚየም፤ በአድዋ ድል ላይ የተፃፉ መፃህፍት፣ የኪነ ጥበብ ውጤቶች፣ ሙዚቃዎች፣ ፊልሞች፣ ተውኔቶች ተከማችተው ለህዝብ የሚቀርብበት ቦታ፤ በተለያዩ ሰዓሊያንና ቀራፂያን የሚቀርቡ በአድዋም ሆነ በሌሎችም ሀሳቦችም የሚሰሩ ስራዎችን የሚታዩበት ቋሚ የሆነ ጋለሪ፣ ትልቅ ቤተ መፃህፍት፤ ለሲኒማ፣ ለትያትር እንዲሁም ለማንኛውም ክዋኔ ጥበባት የሚያገለግል ሁለገብ የሆነ አዳራሽ፤ ምግብ ቤቶች ናቸው።

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሌሎች ሃገራት ላይ እንዳለው የርቀቶች መነሻ ወይም የአገሪቷ እምብርት ተብሎ የሚወሰደው ቦታ ላይ ህንፃውን ለመስራት ታስቧል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የከተሞች ርቀት የሚለካው አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ሲሆን ይህ ዜሮ ኪሎ ሜትር (እምብርት ) ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ላይ ማዕከሉ ይሰራል።

በዚህም ቦታ ላይ"ሁሉ ከዚህ ይጀምራል" የሚል ፅሁፍ የሚኖረው ሲሆን ሁሉንም የሚያሰባስብ ቦታ ሊሆን እንደታቀደም ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ገልፀዋል።

"በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅ፣ በምዕራብ ያለነው ኢትዮጵያውያን አንድ የሚያደርገን የሚያስተሳስረን ነገሮች ቢኖሩም በዚህ ጥበባዊ መንገድ የምንተሳሰርበት ሁኔታ ሲፈጠር አብረን ቆመን ሁላችንም ከዚች ቦታ ነው የምንነሳው፤ ስለዚህ ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ አድዋ ደግሞ ሁላችንም የተሳተፍንበት ነው" ይላሉ።

የማዕከሉ ዲዛይን ጋሻ እንዲመስል ተደርጎ የታሰበ ሲሆን ከዚህም ጀርባ ያለው ፅንሰ ሃሳብ አለኝታነትን፣ መከታነትን እንዲወክል ቢሆንም የመጨረሻው ዲዛይን እንዳልሆነ ግን ኃላፊው ገልፀዋል።

ዲዛይኑም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ማህበረሰቡን እንዲያሳትፉ በሚል እሳቤ ውይይቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለትም ከሀይማኖት አባቶች፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራን፣ ከኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አርበኞችና ከተውጣጡ የማህበረሰቡ አባላት ግብአት መሰብሰቡን ኃላፊው ነግረውናል።

ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ እንደሚሉት ምን ያህል ወጭ እንደሚያስፈልግ አሁን ባለው ሁኔታ ባይታወቅም "የአድዋን ታሪክ አስፈላጊነት፣ ለትውልድ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ጥቅምና ለአገራችን የሚኖረውን ታላቅ እሴት በማሰብ ማንኛውንም ወጪ ለመሸፈን ከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኝነት አለው" ብለዋል።