በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል በኩፍኝ ወረርሽኝ 39 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሶስት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው የኩፍኝ ወረርሽኝ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሰዎች ሕይወት አልፏል። በርካቶችም በወረርሽኙ መያዛቸውንና አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች መቀስቀሱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር በየነ ሞገስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት በሶማሌ ክልል ላይ በዋናነት በሸበሌ፣ ሊበንና ጃረር የሚባሉ ዞኖች ላይ ወረርሽኑ የተከሰተ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ባሌ ላይ ተዛምቶ ነበር።
ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በኦሮሚያ ክልል 3611፤ በሶማሌ ክልል 1248 ሰዎች መጠቃታቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ከተያዙት ሰዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል 23 እንዲሁም በሶማሌ ክልል 16 ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ፕሮግራም ወጥቶለት ህፃናትን ለመከተብ የተቀመጠ መድሃኒት ስለነበር ከዚያ ላይ በማንሳት የተወሰኑ ሰዎችን መክተብ እንደተቻለና በከፋ ሁኔታ ሳይስፋፋ ማስታገስ እንደተቻለ አስረድተዋል።
"ሁሉንም ለመከተብ የክትባት እጥረት ነበር " የሚሉት ዳይሬክተሩ በተለይ በሶማሌ ክልል አዳዲስ ቦታዎች ወረርሽኙ እየተስፋፋ ነው ብለዋል።
አገሮች እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲያጋጥማቸው መድሃኒት ከሚያገኙበትና ኤም አር አይ የተባለ ዓለም አቀፍ የመድሃኒት ማከማቻ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በኩል 1.3 ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) ክትባት ትናንት ኢትዮጵያ መድረሱን ዶ/ር በየነ ተናግረዋል።
ክትባቱም በሚቀጥሉት ሳምንታት በወረርሽኙ ለተጠቁ ሰዎች በዘመቻ ይሰጣል፤ ክትባቱን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት በመደረጉም የከፋ ስጋት እንደሌላቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወር ብቻ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር ወረርሽኙ በሶስት እጥፍ መጨመሩን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።
የኩፍኝ በሽታ አፍሪካ ውስጥ በ700 እጥፍ የጨመረ ሲሆን አሁን ያለው መረጃ እንደሚያሳየው መላው ዓለም ለወረርሽኙ ተጋላጭ መሆኑን ነው። በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ አገሮች መካከል ዩክሬን፣ ማዳጋስካርና ህንድ ይገኙበታል።
ወረርሽኙን በክትባት መከላከል ቢቻልም የክትባት እጥረት መኖሩን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አስታውቋል።