በፖርቹጋል ባጋጠመ የመኪና አደጋ ቢያንስ የ29 ሰዎች ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በፓርቹጋሏ ደሴት ማዴራ፤ ጀርመናዊ ጎብኝዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ መንገድ ስቶ በመገልበጡ ቢያንስ የ29 ሰዎች ሕይወት አለፈ። ሌሎች 27 ሰዎችም ጉዳት እንዳጋጠማቸው ታውቋል።
የፖርቹጋል የዜና ወኪል በመጓዝ ላይ የነበረው የጎብኝዎች መኪና መስቀለኛ መንገድ ላይ ሲደርስ አሽከርካሪው መኪናውን መቆጣጠር እንዳልቻለና መንገድ ስቶ በመውጣት ከአንድ ቤት ጣሪያ ላይ እንደወደቀ ዘግቧል።
ተሽከርካሪው ሹፌሩንና አስጎብኝውን ጨምሮ 55 ተሳፋሪዎችን ሲያጓጉዝ የነበረ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል አስራ አንዱ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 17 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል። አንዲት ሴትም ለህክምና እርዳታ ሆስፒታል ከገባች በኋላ ነው ሕይወቷ ያለፈው።
የከተማዋ ከንቲባ ፊሊፔ ሶሳ "ያጋጠመውን አደጋ ለመግለፅ በጣም ይከብደኛል፤ የእነዚህን ሰዎች ስቃይ ማየት አልችልም" ሲሉ ተናግረዋል።
ከንቲባው አክለውም በአውቶብሱ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ጀርመናዊ ሲሆኑ የአገሬው ዜጋ የሆኑ ሌሎች ሰዎችም እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው በደሴቷ ዋና ከተማ ፉንቻል ሆስፒታል ተልከው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።
የማዴራ አስተዳዳሪ ፔድሮ ቻላዶ በበኩላቸው ተሽከርካሪው የደህንነት ብቃት መስፈርቶችን ያሟላ ሲሆን "የአደጋውን ምክንያት በማጣራት ላይ ነን፤ ምክንያቱን ለመናገር ጊዜው ገና ነው" ብለዋል።
የፖርቱጋል ፕሬዚዳንት ማርሴሎ ሬቤሎ ዲ ሶሳ አደጋውን ለማየት ወደ ከተማዋ እያመሩ መሆናቸውን መገናኛ ብዙኀን የዘገቡ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር አንቶኒዎ ኮስታ ለጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል በአደጋው ማዘናቸውን የሚገልፅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጀርመን መንግስት ቃል አቀባይ ስቴፈን ሴበርት በበኩላቸው "በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት የተሰማንን መራር ሃዘን እንገልፃለን፤ ከተጎዱት ወገኖችም ከጎናቸው ነን" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

መስከረም ኃይሌ፡ ከአንታርክቲካ በስተቀር ስድስቱን አህጉሮች ያዳረሰችው ኢትዮጵያዊት
በአካባቢዋ ያሉትን ቦታዎች በመጎብኘት ጉዞዋን የጀመረች መስከረም ከአንታርክቲካ በስተቀር ወደ ሁሉም የዓለማችን አህጉሮች ተጉዛለች፡፡ በዚህም ከመቶ በላይ የዓለማችን አገራት እንግዳ ሆናለች፤ እንደ አፍሪካዊት ሴት ጎብኝም በርካታ ፈተናዎችን አስተናግዳለች።