የፔሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ራሳቸውን አጠፉ

ጋርሺያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አሜሪካዊቷ ሃገር ፔሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አለን ጋርሺያ ስልጣን ላይ ሳሉ ፈጽመዋል ተብለው ለተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ፖሊስ መኖሪያ ቤታቸው ደርሶ በቁጥጥር ስር ሊያውላቸው ሲል ጭንቅላታቸውን በጥይት በመምታት ራሳቸውን አጠፉ።

የመሞታቸው ዜና ስልጣን ላይ ባሉት ፕሬዝዳንት ማርቲን ቪዝካር ተረጋግጧል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጋርሺያ የሚቀርብባቸውን የሙስና ክስ ቢክዱም፤ ፖሊስ ከብራዚል የግንባታ ኩባንያ ጉቦ ተቀብለዋል ብሎ ጠርጥሯቸዋል።

ጋርሺያ እ.ኤ.አ 1985-1990 እንዲሁም በድጋሚ ከ2006-2011 ድረስ ፔሩን ለ10 ዓመታት አስተዳድረዋል።

በቀድሞ ፕሬዝንት ቤት ምን ተፈጠረ?

ፖሊስ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጋርሺያን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የባለጸጎች መኖሪያ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ያቀናል። ፖሊስ መኖሪያ ቤታቸው ደርሶ በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ሲል ጋርሺያ የስልክ ጥሪ ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረው ወደ አንድ ክፍል ውስጥ ገብተው በሩን ቆለፉ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የተኩስ ድምጽ ተሰማ። የሃገር ውስጥ ሚንስትሩ ካርሎስ ሞራን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ የተኩስ ድምጽ እንደተሰማ ፖሊሶች በሩን በኃይል ከፍተው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ፤ የቀድሞ ፕሬዝድንት ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ጭንቅላታቸው በጥይት ተመትቶ ተመለከቱ።

በፔሩ መዲና ሊማ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ቢደረግላቸውም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም።

ጋርሺያ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው በሊማ ከተማ የባቡር መስመር ሲገነባ ኦዱሬችት ከተሰኘ የብራዚል ኩባንያ ጉቦ ተቀብለዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ኩባንያው በፔሩ እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ 30 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ መክፈሉን አምኗል።

ጋርሺያ ከሁለት ቀናት በፊት በትዊተር ገጻቸው ላይ ስለቀረበባቸው ክስ ''ምንም አይነት ፍንጭም ይሁን ማስረጃ የለም'' በማለት ጉቦ አለመቀበላቸውን አሳውቀው ነበር።