ባንግላዲሽ፡ ፆታዊ ትንኮሳ ደርሶብኛል በማለቷ ተቃጥላ እንድትሞት የተደረገችው ወጣት

ኑስራት

የፎቶው ባለመብት, family handout

ኑስራት ጃሃን ራፊ በትምህርት ቤቷ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነዳጅ ተርከፍክፎባት፤ በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት ተደርጋለች። ከሁለት ሳምንታት በፊት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ፆታዊ ትንኮሳ አድርሶብኛል ስትል ለፖሊስ አሳውቃ ነበር።

ኑስራት ጃሃን የ19 ዓመት ወጣት ነበረች። ባንግላዴሽ ውስጥ ፌኒ በምትሰኝ አነስተኛ ከተማ ውስጥ የእስልምና ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታለች።

መጋቢት 18 2011 ዓ.ም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ኑስራትን ወደ ቢሮው ያስጠራታል። ከዚያም ኑስራት እንደምትለው ርዕሰ መምህሩ ባልተገባ ሁኔታ ይነካካት ጀመረ። ከዚያም ከቢሮው ሮጣ አመለጠች።

የባንግላዴሽ ሴቶች ከማህብረሰቡ እና ከቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸውን መገለል እና ሃፍረት በመፍራት የሚፈፀምባቸውን ፆታዊ ትንኮሳዎች አይናገሩም። ኑስራት ግን ርዕሰ መምህሩ የፈፀመባትን መናገር ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቿ እርዳታ ጉዳዩን ፖሊስ ጋር ወሰደችው።

ፖሊስ ግን ቃሏን ተቀብሎ ጉዳዩን እያጣራ ከለላ ማድረግ ሲገባው ኑስራትን ማብጠልጠል ጀመረ። በዕለቱ ተረኛ የነበረው ፖሊስ ኑስራት ቃሏን ስትሰጥ ቪዲዮ እየቀረፃት ነበር። ኑስራት ቃሏን እየሰጠች በፖሊሱ መቀረፅ አላስደሰታትም። በተቀረፀው ቪዲዮ በግልፅ እንደሚታየው ኑስራት በእጇ ፊቷን ለመሸፈን ጥረት ታደርግ ነበር።

በተንቀሳቃሽ ምስሉም ፖሊሱ የኑስራትን ቅሬታ ''ይህ ትልቅ ጉዳይ'' አይደለም እያለ ሲያጣጥል ይሰማል። ይህ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto/Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኑስራት ላይ የተፈፀመው አስከፊ ተግባር በርካቶችን አስቆጥቷል።

ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄዳ ቃሏን ከሰጠች በኋላ፤ ርዕሰ መምህሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደረገ። ይህ ግን ለኑስራት ችግርት ፈጠረ። በቡድን የተደራጁ ወንዶች ርዕሰ መምህሩ ከእስር እንዲለቀቁ ሰልፍ ማድረግ ጀመሩ። ተቃውሞ ሰልፉን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል ኑስራት የምትማርበት ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑ ሁለት ወንዶች ይገኙበታል። የአከባቢው ፖለቲከኞችም የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ሆነዋል።

በርካቶች ለርዕሰ መምህሩ መታሰር ኑስራትን ተጠያቂ ማድረግ ጀመሩ። ወላጆቿም የልጃቸው ደህንነት ያሰጋቸው ጀመር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ለፖሊስ ቃሏን ከሰጠች ከ11 ቀናት በኋላ ኑስራት ማጠቃለያ ፈተና ለመፈተን ወደ ትምህርት ቤቷ ሄደች።

''ደህንነቷ ስላሰጋን ትምህርት ቤት ድረስ ይዣት ሄድኩ። ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዳልገባ ግን ተከለከልኩ።'' ይላል የኑስራት ወንድም መሃሙዱል ሃሰን ኖማን። "እንዳልገባ ባይከለክሉኝ ኖሮ፤ ይህን መሰል ተግባር በእህቴ ላይ አይፈፅሙም ነበር'' ሲል ጨምሮ ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Shahadat Hossain

የምስሉ መግለጫ,

የኑስራት ወንድም መሃሙዱል ሃሰን ኖማን በኑስራት የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ ሃዘኑን ሲገልጽ።

ኑስራት በሰጠችው ቃል መሠረት አንድ የክፍል ጓደኛዋ፣ ጓደኛቸው እየተደበደበች እንደሆነ በመንገር ኑስራትን የትምህርት ቤቱ ሕንፃ ጣሪያ ላይ ይዛት ትወጣለች። ጣሪያው ላይ የጠበቃት ግን ሴት ለመምሰል ዓይነ እርግብ የለበሱ (ዓይናቸው ብቻ የሚያሳይ ሂጃብ) አምስት የሚሆኑ ወንዶች ነበሩ።

ከዚያም ኑስራትን በመክበብ በርዕሰ መምህሩ ላይ ያቀረበችውን ክስ እንድታነሳ ያስፈራሯታል። ኑስራት ግን እንደማታደርገው ትናገራለች። ከዚያም ነዳጅ አርከፍክፈውባት እሳት ለኩሰው አቃጠሏት።

የመርማሪ ፖሊሶች ኃላፊ ባንድ ኩማር ማጁመደር እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ ''ኑስራት እራሷን ያጠፋች ለማስመሰል አስበው ነበር'' ሃሳባቸው ሳይሳካ የቀረው ተጠርጣሪዎቹ ኑስራት ሕይወቷ ያለፈ መስሏቸው አካባቢውን ጥለው ከሄዱ በኋላ ኑስራት እስተንፋሷ ሳይወጣ ቃሏን በመስጠቷ ነው።

''አንደኛው ተጠርጣሪ የኑስራትን ጭንቅላት በእጆቹ ወጥሮ ከመሬት አጣብቆ ይዞ ስለነበረና ጭነቅላቷ ላይ ነዳጅ ስላላፈሰሱ ከአንገቷ በላይ አልተቃጠለችም። በዚህም ሕይወቷ ሊቆይ ችሏል'' ሲሉ የፖሊስ አዛዡ ለቢቢሲ ቤንጋሊ ቋንቋ አገልግሎት ተናግረዋል።

ኑስራት አካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ስትወሰድ 80 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍሏ ተቃጥሏል። ጉዳቷ ከሆስፒታሉ የማከም አቅም በላይ በመሆኑም ዋና ከተማ ወደሚገኝ ዳካ የሕክምና ኮሌጅ ሆስፒታል ተልካለች።

አምቡላንስ ውስጥ ሳለች ሕይወቷ ሊተርፍ እንደማይችል የተረዳችው ኑስራት በወንድሟ ስልክ የቪዲዮ መልዕክት ቀርፃ አሰቀመጠች። በቪዲዮ ላይም ''አስተማሪው ነካክቶኛል። እስትንፋሴ እስኪቋረጥ ድረስ ይህን ወንጀል እፋለማለሁ'' ስትል ትታያለች። ጉዳት ካደረሱባት መካከልም የተወሰኑትን ማንነትም ይፋ አድርጋለች።

ሚያዝያ 1 ላይ ሕይወቷ አለፈ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በትውልድ ከተማዋ የቀብር ሥነ-ሥርዓቷ ላይ ተገኙ።

ፖሊስ እስካሁን 15 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ከእነዚህም መካከል ሰባቱ ከግድያው ጋር በቀጥታ ግንኙነት አላቸው ተብሏል። ተቃውሞ ሰልፍ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሁለቱ ወንድ ተማሪዎችም ከታሳሪዎቹ መካከል ይገኙበታል። ለፖሊስ ቃሏን ስትሰጥ ቪዲዮ የቀረፃት ፖሊስ ወደ ሌላ ክፍል ተዛውሯል።

የባንግላዴሸ ጠቅላይ ሚንስትር ሼክህ ሃሲና የኑስራትን ቤተሰቦች አግኝተው ያነጋገሩ ሲሆን በወንጀሉ የተሳተፉ ሰዎች በሙሉ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተውላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Shahadat Hossain

የምስሉ መግለጫ,

የኑስራታ ቀብር ሥነ-ሥርዓት

የኑስራታ ሞት በርካቶችን አበሳጭቷል። በባንግላዴሸም መነጋገሪያ ሆኗል። አንዲት ሴት ''ሴት ልጅ እንዲኖረኝ ሁሌም እመኛለሁ። እዚህ ሃገር ውስጥ ሴት ልጅ መውለድ ማለት ለሕይወቷ ሁሌም መስጋት ማለት ነው'' ስትል በፌስቡክ ገፇ ላይ አስፈራለች።

በባንግላዴሽ የሴቶች መብት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ የመብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት እ.አ.አ 2018 ላይ ብቻ 940 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ተመዝግበዋል።