ኢትዮጵያዊው የኡጋንዳ አየር ኃይል ፊታውራሪ

ኮሎኔል ጌታሁን ካሳ

የፎቶው ባለመብት, Yonathan Menkir Kassa

ለዓመታት የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በጦር አውሮፕላን አብራሪነት አገልግለዋል። ሌተናንት ኮሎኔል ጌታሁን ካሳ በፈፀሟቸው ጀብዶች እና በወታደራዊ ስነምግባራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ የጀግንነት ሽልማት አግኝተዋል።

ከእናት አገራቸው ብቻም ሳይሆን ሌተናንት ኮሎኔል ጌታሁን ከጎረቤት አገር ኡጋንዳ መንግሥትም ትልቅ ወታደራዊ ሽልማት የተበረከተላቸው የሁለት አገር ጀግና ናቸው።

የአየር ኃይሏ ፊታውራሪ በመሆን ለዓመታት ያገለገሏትና ከጥቂት ቀናት በፊት ህይወታቸው ያለፈው፤ ሌ/ኮ ጌታሁን ሽኝትን በከፍተኛ ወታደራዊ ስነ ስርዓት በማድረግም ነው ኡጋንዳ ለባለውለታዋ ምስጋናዋን የገለፀችው።

ሌ/ኮ ጌታሁን ለዓመታት የሙሴቬኒ አውሮፕላን አብራሪም ሆነው አገልግለዋል።

"የሙሴቪኒ ታናሽ ወንድም ወደ ኡጋንዳ ወሰዷቸው..."

በደርግ ስርዓት ውድቀት ዋዜማ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው እንደ ኬንያ ወዳሉ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል። ሄሊኮፕተር ይዘው እንደ የመን እና ሳዑዲ አረብያ ወዳሉ አገራት የሄዱ የአየር ኃይል አብራሪዎችም ነበሩ። ሌ/ኮ ጌታሁን ግን እስከ መጨረሻዎቹ ማለትም ኢህአዴግ አዲስ አበባን እስከተቆጣጠረበት ዕለት ድረስ በአየር ኃይል ቅጥር ቆይተው ነው በመጨረሻ ራሳቸውን ቀይረው በስውር በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ያቀኑት።

ለተወሰነ ጊዜ በኬንያ የስደተኞች ካምፕ ከቆዩ በኋላ በካምፑ መቆየታቸው ለደህንነታቸው እንደሚያሰጋ ስለታመነ ወደ መዲናዋ ናይሮቢ እንዲዘዋወሩ ተደረገ።

በወቅቱ ስልጣኑን በማደራጀት ላይ የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት እሳቸውና ሌሎችም የአየር ሃይል ሰዎች ተላልፈው እንዲሰጡት እየጠየቀ እንደነበርና በመጨረሻም በልዩ ድርድር እሳቸውና ጓደኞቻቸው አስር ሆነው ወደ ኡጋንዳ እንዲሄዱ ተደረገ።

እነ ሌ/ኮ ጌታሁንን ናይሮቢ ድረስ መጥቶ ወደ ኡጋንዳ የወሰዷቸውም የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዎሪ ሙሴቬኒ ታናሽ ወንድም ጀነራል ሳሊም ሳለህ እንደነበሩ ወንድማቸው አቶ ተሾመ ካሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌ/ኮ ጌታሁን መጀመሪያ ሶሮቲ በተሰኘ አካባቢ ቆይተው ኋላ ቋሚ ኑሯቸውን በኢንቴቤ አደረጉ።

የፎቶው ባለመብት, Yonathan Menkir Kassa

ከዚያም የኡጋንዳ አየር ኃይልን በማደራጀት፣ በርካታ ፓይለቶችን በማሰልጠንና የስልጠና መመሪያዎችን በመቅረፅ ለኡጋንዳ አየር ኃይል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

በጆሴፍ ኮኔ የሚመራው የሎርድ ሬዚስታንስ እንቅስቃሴ ኤል አር ኤ ሰሜናዊ ኡጋንዳ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ለአገሪቱ ራስ ምታት በሆነበት ወቅት ትልልቅ ወታደራዊ ተልእኮዎችን እንደፈፀሙ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

ዜግነት እንደ ሽልማት

የኤል አር ኤ መፈንጫ የነበረውን ሰሜናዊ ኡጋንዳ ወደ ሰላም ለመመለስ ላበረከቱት ተሳትፎ ኡጋንዳዊ ዜግነት ሲሰጣቸው የአገሪቱን ከፍተኛ የጀብድ ኒሻን ከፕሬዝዳንት ዩዎሪ ሙሴቬኒ እጅ መቀበልም ችለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1996 እስከ 2005 የኡጋንዳ መከላከያ ሰራዊት ባካሄዳቸው እና አየር ኃይሉ በተሳተፈባቸው ተልእኮዎች ሁሉ ሌ/ኮ ጌታሁን እንደነበሩም በሕይወት ታሪካቸው ላይ ሰፍሯል።

ከስልጠና፣ ከበረራ፣ የአደረጃጀት መመሪያዎችን ማዘጋጀትና የሄሊኮፕተር ግዥዎችን ማማከርን ጨምሮ እሳቸው ያልተሳተፉበት የኡጋንዳ አየር ኃይል እርምጃ አልነበረም ማለት ይቻላል።

ሌ/ኮ ጌታሁን ከልብ ጋር በተያያዘ ችግር ለአንድ ሳምንት ያህል ታምመው መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም በህክምና ሲረዱ በነበሩበት የካምፓላው ናካሴሮ ሆስፒታል ሕይወታቸው አልፏል።

ህልፈታቸው እንደተሰማ ቤተሰባቸው ወደ ኡጋንዳ ያቀናው፤ አስክሬናቸውን ወስዶ በኢትዮጵያ ለመቅበር የነበረ ቢሆንም ኡጋንዳ ባለውለታዋ ሌ/ኮ ጌታሁንን ለመሸኘት እያደረገች ያለውን የሽኝት ዝግጅት ሲመለከቱ አስከሬናቸው ማረፍ ያለበት እዚያው በኡጋንዳ ምድር እንደሆነ ማመናቸውን የታላቅ ወንድማቸው ልጅ ዮናታን መንክር ካሳ ገልፆልናል።

አጎቱን 'የሁለት አገር ጀግና' ብሎ የሚገልፀው ዮናታን አጎቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪ በነበሩበት ወቅት ከባድ የሚባሉ የጦር ጀብዱዎችን መፈፀማቸውን፤ በአንድ አጋጣሚም ጓደኛቸው ያበር የነበረው ሄሊኮፕተር በጠላት ቀጠና ውስጥ ተመትቶ በወደቀ ወቅት ምንም እንኳ እሳቸው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ቢተላለፍላቸውም በተኩስ ልውውጥ ውስጥ ሄሊኮፕተር አሳርፈው የቆሰለ ጓደኛቸውን ይዘው እንደተነሱ ብዙ ጓደኞቻቸው እንደሚመሰክሩም ይናገራል።

እሱ እንደገለፀልን ራሳቸው ያስተማሯቸውና የአሁኑ የኡጋንዳ አየር ኃይል አዛዥ ተገኝተው የሕይወት ታሪካቸውን ባነበቡበት በከፍተኛ ወታደራዊ ሽኝት በኡጋንዳ ወታደራዊ መቃብር ስፍራ ስርዓተ ቀብራቸው ሰኞ ሚያዝያ ሰባት ቀን ተፈፅሟል።

ፍታታቸው የተፈፀመውም ከምስረታው ጀምሮ ትልቅ ተሳትፎ ባደረጉበት በካምፓላው የኢትዮጵያ መካነ ሰላም መድሃኒዓለም ቤተ ክርስትያን ነው።

ፕሬዘዳንት ሙሴቪኒ የሌ/ኮ ጌታሁንን ሕልፈተ ዜና እንደሰሙ በርግጥም ህልፈታቸው ተፈጥሯዊ መሆኑ እንዲረጋገጥ ማድረጋቸውንና የቀብር ስነስርዓቱን በሚመለከትም ነገሮችን እየጠየቁ መከታተላቸውንም ወንድማቸው አቶ ተሾመ ነግረውናል።

ሌ/ኮ ጌታሁን ከጥቂት አመታት በፊት በረራ ቢያቆሙም ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የኡጋንዳ አየር ኃይል ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሲሰሩ ነበር።

ከእሳቸው ጋር የኡጋንዳ አየር ኃይልን የተቀላቀሉ ኢትዮጵያዊ ጓደኞቻቸው ጥቂት ከሰሩ በኋላ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሲሄዱ እሳቸው ግን እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ኡጋንዳን አገራቸው ማድረጋቸው በኡጋንዳዊያን ዘንድ ክብርን እንዳተረፈላቸው ይነገራል።

ከቤተሰቦቻቸው እንደተረዳነው የ69 ዓመቱ ሌ/ኮ ጌታሁን ትዳር አልመሰረቱም፤ ልጅም የላቸውም። ብዙ ጓደኛም የሌላቸውና ብቸኛ የሚባሉ ዓይነት ሰው ነበሩ።

ኡጋንዳን መኖሪያ ቤታቸው ቢያደርጉም በየዓመቱ በቋሚነት ኢትዮጵያ ለሚገኙ 23 የቤተሰባቸው አባላትና ልጅ ሳሉ ላገለገሉባቸው የገጠር አብያተ ክርስትያናት በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ይልኩ እንደነበርም ያነጋገርናቸው ቤተሶቦቻቸው ገልፀውልናል።