ሻሚማ ቤገም፡ ሴቶች የሽብር ምስጢራዊ መሳሪያ ለምን ሆኑ?

ሻሚማ ቤገም

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ,

ሻሚማ ቤገም እ.አ.አ 2015 እንግሊዝን ለቃ ስትወጣ የ15 ዓመት ታዳጊ ነበረች

ከሽብርተኝነት ጋር በተገናኘ ሴቶች የዜና አካል ሲሆኑ በአብዛኛው የዜናው ትኩረት የሚሆነው ሴቶች ተጎጂዎች አሊያም ተባባሪዎች እንደሆኑ ተደርጎ ነው። በአንፃሩ ሽብርተኝነትን የሚደግፉ አሊያም እጃቸው ያለበት ሴቶች ጎልተው አይወጡም።

ነገርግን በአስራዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኘው ሻሚማ ቤገም የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ምልክት ሆና መውጣት ከጀመረች አንስቶ ይህ እየተለወጠ መጥቷል።

ሻሚማ ከሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የእስላማዊ ቡድኑን ( አይ ኤስ) የተቀላቀለችው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር። እርሷ እንደምትለው በወቅቱ የቤት እመቤት ነበረች።

ቢሆንም ግን የእንግሊዝ ባለስልጣናት "ተመልሰሽ ከመጣሽ፤ አደጋ ሊገጥምሽ ይችላል" ሲሉ የእንግሊዝ ዜግነቷን እንደተነጠቀች ከተናገሩ በኋላ ውሳኔውን ለማስቀየር የህግ ድጋፍ ለማግኘት አቤቱታዋን አሰምታለች።

ሴቶችና ሽብርተኝነት

የሻሚማ ቤገም ጉዳይ ሴቶች በሽብርተኝነትና በእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ውስጥ በንቃት መሳተፋቸውን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የጥናት ተቋሙ ሩሲ ያካሄደው ጥናት እንደሚያመላክተው 17 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች የሚመለመሉት ከአፍሪካ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን በኢራቅና በሶሪያ በሚያካሂዳቸው የውጪ ምልመላወቹ 13 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው በሌላ ጥናት ተገልጿል።

ሌሎች የሚወጡ በርካታ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጉዳዩ የተወሳሰበና ቁጥሩም ከዚህም ሊልቅ ይችላል።

ከአራት ዓመታት በፊት ሻሚማ ቤገም (በቀኝ በኩል) ከሁለት ጓደኞቿ አሚራ አባሴ እና ካዲዛ ሱልታና በጋትዊክ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Met Police

የምስሉ መግለጫ,

ከአራት ዓመታት በፊት ሻሚማ ቤገም (በቀኝ በኩል) ከሁለት ጓደኞቿ አሚራ አባሴ እና ካዲዛ ሱልታና በጋትዊክ አየር መንገድ

የጥናት ማዕከሉ ሩሲ የቀደሙ ጥናቶች እና ሌሎች ምርምሮች በአፍሪካ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ በሆኑት በአል ሻባብ እና በእስላማዊው ቡድን (አይ ኤስ) ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ሚና መርምረዋል።

በአል ሻባብ እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፈችን አንዲት ሴት ቃለ መጠይቅ ያደረጉት አጥኝዎች፤ ሴቶቹ እንዴት እንደሚመለመሉና ጥቃቶች ላይ መሳተፋቸው በሴቶቹ በራሳቸው ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ መለየት ችለዋል።

ጥናቱ የተሰራው በኬንያ በሚገኝ የትምህርት ተቋም ሲሆን ድርጅቱ የእነርሱን ልምድና ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ትስስር በማየት ለእንደዚህ አይነት አደጋዎች የሚያጋልጡ ምክንያቶችን ለመለየትና ለመቀነስ ይሰራል።

አይ ኤስ እና አል ሻባብ

በሁለቱ የሽብር ቡድኖች የሴቶች ሚና የተለያየ ነው።

በአል ሻባብ ውስጥ ያሉ ሴቶች በአብዛኛው በተለመደና ባህላዊ በሆነ መንገድ ሚስት በመሆን፣ አጥፍቶ ጠፊ አሊያም በቤት ውስጥ ሥራ በመስራት የሚሳተፉ ሲሆን አንዳንዴም የወሲብ ባሪያ ይደረጋሉ።

እነዚህ ሴቶች ሌሎች አዳዲስ አባላትን ለመሳብ ይረዳሉ። በኬንያ የተሰራ አንድ የጥናት ግኝት እንዳመለከተው ሴቶች በሌሎች ይሳቡ የነበሩት የሥራ እድል እንደሚያገኙላቸው ቃል ስለሚገቡላቸው፣ በገንዘብ እርዳታና በሚሰጧቸው የምክር አገልግሎት ነበር።

ለምሳሌ ሂዳያ (እውነተኛ ስሟ አይደለም) ልብስ ሰፊ ስትሆን የንግድ ሥራዋን እንደሚያስፋፋላት ቃል በገባላት አንድ ጓደኛዋ አማካይነት ነበር የሽብር ቡድኑን የተቀላቀለችው። ከዚያም ከምትኖርበት ቦታ ወደ ሶማሊያ አመራች።

በኤይ ኤስ በኩል ግን ብዙ ጊዜ ሴቶች የሚመለመሉት በአብዛኛው በኢንተርኔት (ኦን ላይን) ሲሆን የቡድኑን እምነትና አቋም በማንፀባረቅ በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

እዚህ ላይ የሻሚማን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። የእርሷ መመልመል በአይ ኤስ በኩል የፕሮፓጋንዳቸው አንድ ድል ተደርጎ ይቆጠራል።

በአንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በአይ ኤስ ውስጥ ያሉ ሴቶች እንደ ዶክተርና የጤና ባለሙያዎች ሆነው ያገልግላሉ። ለቡድኑ በጠቅላላ የሞራል ድጋፍ የሚሰጡ ኃይል ሆነውም ይሰራሉ።

በቅርቡ ቡድኑ በኢራቅና በሶሪያ ያለውን ግዛት ሲያጣ ሴቶችን በግምባር ቀደምትነት አሰልፎ ነበር። ቡድኑ 'አል ናባ' በሚለው ጋዜጣውም ለሴቶቹ የጅሃድ ጥሪን አቅርቦላቸዋል። ባለፈው ዓመትም በሶሪያ ይህንኑ ሲያደርጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልም ተለቋል።

ምንም እንኳን በቡድኑ ውስጥ የሚታዩ ልዩነቶች የድርጅቱን ገፅታ ቢያጠለሹትም አንዳቸው ባንዳቸው እየተበረታቱ ቀጥለዋል።

አል ሻባብ በሸሪዓ የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት ለመመስረት በሚሞክርበት ሶማሊያ፤ ሴቶች ፊት አውራሪ ሆነው ሲታገሉና በአጥፍቶ መጥፋት ሲሳተፉ ታይተዋል።

በአል ሻባብ የተፈጸሙ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከአውሮፓውያኑ 2007 እስከ 2016 ድረስ ከተፈጸሙ ጥቃቶች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት የደረሱት በሴቶች ነው።

የቦኮ ሃራም እስላማዊ ቡድን ተንሰራፍቶ ባለባቸው እንደ ናይጀሪያ ያሉ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ለማድረስ ሴቶችን ይጠቀሙባቸዋል።

ሴቶች የጂሃዳዊ ቡድኖችን ለምን ይቀላቀላሉ?

ጥናቶች እንደሚያስረዱት ሴቶቹ ለእነዚህን ቡድኖች እንዲመለመሉ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።

ወንዶች የቡድኖቹ አባል ለመሆን የሚያነሳሳቸው ፅንፍ ያለው ርዕዮተ ዓለምና የገንዘብ ማግኛ ምንጭ የመሆኑ ምክንያት ለሴቶችም ይሰራል።

ይሁን እንጂ በተለየ መልኩ ሴቶች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል ሴቶች ፆታን መሰረት ባደረጉ ሚናዎች መታለላቸው ነው።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው አል ሻባብ ወጣት ሙስሊም ሴቶች በትምህርታቸው እየገፉ ሲሄዱ የጋብቻ ሁኔታቸውን እንደሚያጓትትባቸው በመንገር ያግባቧቸዋል።

"የሚያገባኝ፣ የሚጠብቀኝና የሚንከባከበኝ ባል ካገባሁ ለምን ራሴን በትምህርት አጨናንቃለሁ?" ስትል የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነች አንዲት ሴት አጥኝዎቹን ጠይቃቸው እንደነበር በምሳሌነት ቀርቧል።

ሌሎቹ ደግሞ ሥራ፣ ገንዘብና ሌሎች እድሎችን ለማግኘት ሲሉ ወደ ቡድኑ ይሳባሉ።

የአፍሪካ ቀንድ ካርታ

ምንም እንኳን ቡድኑን መቀላቀላቸው አደገኛ መሆኑን ቢያውቁም አንዳንዶቹ ካለፈቃዳቸው ይመለመላሉ።

ልክ እንደ ሻሚማ ቤገም ሁሉ በቡድኖቹ ውስጥ በንቃት እንደማይሳተፉ ቢናገሩም ያለፈቃዳቸው የሚያደርጓቸው ነገሮች ነበሩ፤ በመሆኑም አንዳንዶቹ ራሳቸውን እንደ ተጠቂ እንጂ እንደ ሽብርተኛ ቡድን አባል አድርገው አይቆጥሩም።

አንዳንዶቹ ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ፈቃደኛ እንዳልነበሩ በመግለፅና የነበራቸውን ኃላፊነት በመካድ ከማህበረሰቡ ጋር ዳግም ለመቀላቀል ምክንያት አድርገው ይጠቀሙበታል።

የተሃድሶ መንገዶች

ከዚህ ቀደም አባል የነበሩትም ሆኑ አሁን የተመለሱ ጥቃት አድራሾች ከድርጊታቸው ሊመለሱ የሚችሉባቸው የተሃድሶ ዘዴዎች አሉ። አብዛኞቹ በሴቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

የህግ እንዲሁም የፀጥታና ደህንነት አካላት ቀድሞ ለመከላከል፣ ለተሃድሶና፣ መልሶ ከህብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል የሚያስችሉ ህጎችን ሲያረቁ ሴቶች የሽብር ቡድኖችን ጥለው የወጡበትን ምክንያት በውል ሊረዱ ይገባል።

ለምሳሌ፣ አንዳንዶቹ የት እንዳሉ የማይታወቁ አሊያም የሞቱ ልጆች አሏቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ በደረሰባቸው የመደፈር ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ የአዕምሮ ጤና ችግር ስላጋጠማቸው የምክር አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል።

ሴቶች አፍራሽ በሆነው የሽብርተኛ ቡድን ያላቸውን ሚና አስመልክቶ መንግሥታት በትኩረት ሊከታተሉት ይገባል። ይህ የሚጀምረውም የሥርዓተ ፆታ ልዩነትን በመረዳትና በሽብር ቡድኖች ውስጥ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎና በራሳቸው ላይ ለሚመጣው ጉዳት ነዳጅ ሆኖ እያገለገለ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።

ይህ ደግሞ አደጋዎችን ለመከላከልና የሽብር ቡድኑን የሚቀላቀሉ ሴቶችን ቁጥር ለመቀነስ ይረዳል።