የመን፡ በስለላ ወንጀል የተጠረጠረው ጥንብ አንሳ

ኔልሰን

የፎቶው ባለመብት, Hisham al-Hoot

ኔልሰን የተባለው ጥንብ አንሳ የመን ውስጥ በመብረር ላይ ሳለ ነበር ባላሰበው መልኩ በወታደሮች ተይዞ በቁጥጥር ስር የዋለው። ከተያዘ በኋላም ጠባብና ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል። የተጠረጠረበት ወንጀል ደግሞ ወታደራዊ ስለላ ነበር።

ቲያዝ በተባለችው ትንሽ ከተማ ወታደሮቹ ሲያገኙት እንቅስቃሴውን የሚቆጣጠር መሳሪያ እግሩ ላይ ተገጥሞለት ነበር። መሳሪያውም ወታደሮቹ አይተውት የማያውቁትና እጅግ የተራቀቀ ሲሆንባቸው ጊዜ ወታደራዊ መረጃዎችን ማስተላለፊያ ሊሆን እንደሚችል በመገመት በቁጥጥር ስር አዋሉት።

በየትኛውም አይነት ጦርነት ውስጥ በስለላ ወንጀል መከሰስ በጣም ከባድ ነው። እንደ ቲያዝ ባለች ትንሽ የየመን ከተማ ውስጥ ደግሞ ማንኛው ሰውም ሆነ እንሰሳት ሰላይ ተብሎ ሊጠረጠር ይችላል- ጥንብ አንሳም ቢሆን።

በሳኡዲ የሚደገፉት እነዚህ ሚሊሺያዎች የኔልሰን እግር ላይ ያለውን ዘመነኛ መሳሪያ እንደተመለከቱ ወዲያው ያሰቡት ሁቲ የተባሉት አማጺያን ቡድኖች ለስለላ የላኩት እንደሆነ ነው።

ነገር ግን የኔልሰን እግር ላይ የተገጠመው መሳሪያ ለጥበቃ ስራ ሲባል የበራሪ እንስሳውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ታስቦ ነበር። በተጨማሪም በሕይወት መኖር አለመኖሩንም ባለሙያዎች የሚቆጣጠሩት በዚሁ መሳሪያ ነው።

ኔልሰን በአውሮፓዊቷ ሃገር ቡልጋሪያ ውስጥ ለምርምር ስራ በማሰብ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ከተገጠመላቸው 14 ጥንብ አንሳዎች መካከል አንዱ ነው። ጉዞውንም አንድ ብሎ የጀመረው ከቡልጋሪያ ነበር። የህይወት አጋጣሚ ሆነ እራሱን በጦርነት በምትታመሰው የመን ውስጥ አግኝቶታል።

ሊያውም በስለላ ወንጀል ተጠርጥሮ እስር ቤት ውስጥ።

የኔልሰንን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሲቆጣጠሩ የነበሩት በቡልጋሪያ የሚገኙት ባለሙያዎች ደብዛው የጠፋውን ግዙፍ በራሪ ማፈላለጋቸውን ቀጥለው ነበር። እነሱ እንደሚሉት ሳኡዲ አረቢያን ካለፈ በኋላ ወደ የመን ሲጠጋ ኔልሰን እግር ላይ ተገጥሞ የነበረው መቆጣጠሪያ መሳሪያ መልዕክት ማስተላለፍ አቆመ።

የፎቶው ባለመብት, Hisham al-Hoot

በሚያስገርም ሁኔታ ቡልጋሪያውያን ተመራማሪዎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ መልዕክቶች ይደርሷቸው ጀመር። ለማንኛውም ብለው በኔልሰን እግር ላይ ባስቀመጡት የስልክና የኢሜይል አድራሻ በኩል ብዙ የቲያዝ ከተማ ነዋሪ የመናውያን የድረሱለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አንዳንዶቹ እንደውም የኔልሰንን ምስል በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በማንሳት ለተመራማሪዎቹ ልከውላቸዋል።

ከተመራማሪዎቹ አንዷ የሆነችው ናድያ ቫንግሎቫ እንደተናገረችው የከተማዋ ነዋሪዎች በጣም ሩህሩህና አስገራሚ ሰዎች ናቸው ብላለች።

''የራሳቸውን የጦርነት መከራና ጭንቀት ወደ ጎን ብለው የኔልሰንን ደህንነት ለማረጋገጥ ይህን ያክል መሰዋዕትነት መክፈላቸው እጅግ አስገራሚ ነገር ነው።'' በማለት አድናቆቷን ለቢቢሲ ገልጻለች።

በመጨረሻም ተመራማሪዎቹ የመን በሚገኘው ኤምባሲ በኩል መልዕክታቸውን ማስተላለፍ ጀመሩ። ሙከራቸውም ፍሬ አፍርቶ ኔልሰንን የያዙት ወታደሮች እግሩ ላይ ያለው መሳሪያ ለስለላ ሳይሆን ለምርምር እንደሆነ መረዳት ቻሉ።

በአሁኑ ሰአት ኔልሰን እግሩ ላይ፣ አንገቱ ላይ እንዲሁም ክንፉ አካባቢ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ክብደቱም ቀንሶ ወደ 4.8 ኪሎ ግራም ወርዷል። እራሱን ችሎ ለመብረርም ቢያንስ ከአምስት ኪሎ በላይ መመዘን አለበት።

በአካባቢው ያሉ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎችና ነዋሪዎቹ ኔልሰን ወደ ሙሉ ጤንነቱ እስኪመለስ ድረስ ስጋ እየመገቡት ነው።

በጦርነት እየታመሰች በምትገኝውና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ባለባት የመን ዜጎቿ እንዲህ አይነት ደግነት በማሳየት ለዓለም ምን አይነት ህዝቦች እንደሆኑ መልዕክት እያስተላለፉ ይመስላል።