የሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዜና አቅራቢ ሮቦት ይፋ አደረገ

ዜና አቅራቢው ሮቦት በሮሲያ 24 ቴሌቪዥን ዜና ሲያቀርብ

የፎቶው ባለመብት, Rossiya 24

የሩሲያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜና የሚያቀርብ ሮቦት ይፋ አደረገ።

'አሌክስ' የተሰኘው ዜና አቅራቢ ሮቦት ገና ከአሁኑ በቴሌቪዥኑ ተመልካቾች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፤ በርካቶች መልኩን አለመውደዳቸው እና ፕሮፖጋንዳ ይነዛል እያሉ እየወቀሱት ይገኛሉ።

ሮቦቱ ፐርም በተባለች የሩሲያ ከተማ ውስጥ የተሰራ ሲሆን የፊቱ ቅርጽ ከቴሌቪዥን ጣቢያው መስራቾች መካከል አንዱ የሆነዉን አሌክሲ ዩዘሀኮቨን እንዲመስል ተደርጎ ተቀርጿል።

የሮቦቱ ግንባታ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረ ሲሆን አሁን ባለበት ደረጃ ሮቦቱ ፊቱን እና አንገቱን ብቻ ነው ማነቃነቅ የሚችለው።

የፎቶው ባለመብት, Prombot

የምስሉ መግለጫ,

አሌክሲ ዩዘሀኮቨ (ግራ) እና አሌክስ ሮቦቱ (ቀኝ)

ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳለው የአሌክስ ውጫዊ አካል እና ውስጣዊ ስሪቱ (ሶፍትዌሩ) ሙሉ በሙሉ የተሰራው ሩሲያ ውስጥ ነው።

በርካታ የዜና ሰዓቶችን የተቆጣጠረው አሌክስ በርካታ ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል። የፊቱ ገጽታዎች ያልተለመደ እና በርካቶች አስቂኝ ሆኖ ያገኙታል። ተመልካቾች "አሌክስ ሁሉንም ዜናዎች በተመሳሳይ ፍጥነት እና ስሜት ነው የሚያነበው" በማለት ከሰው ልጆች የሚለይበትን መንገድ ይዘረዝራሉ።

ሮሲያ 24 የተሰኘው የቴሌቪዝን ጣቢያ ''ለመጀመሪያ ጊዜ ሮቦት የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢ ሆነ ''ሲል በድረ-ገጹ አስፍሯል።

ቴሌቪዥን ጣቢያው ጨምሮም ''ውሳኔው የተመልካቾች ነው፤ ሮቦቶች ጋዜጠኞችን መተካት ይችላሉ?'' በማለት ጠይቋል።