ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ጠቅላለ ባለስልጣናት ስልጣን ለቀቁ

የመዲናዋ ከተማ ነዋሪዎች መንግሥት ሰላም እና መረጋጋት ለሃገሪቱ ማምጣት ተስኖታል በሚል አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የመዲናዋ ከተማ ነዋሪዎች መንግሥት ሰላም እና መረጋጋት ለሃገሪቱ ማምጣት ተስኖታል በሚል አደባባይ ወጥተው ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ኃላፊዎች በማሊ እየጨመረ የመጣውን ሥርዓት አልበኝነትን ተከትሎ እራሳቸውን ከኃላፊነት አገለሉ።

ከሁለት ቀናት በፊት የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚንስትር ሶሜይሉ ቡብሄ ማኢጋ በሃገሪቱ ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ሥርዓት አልበኝነት መቆጣጠር አልቻሉም በማለት የመተማመኛ ድምጽ ነፍገዋቸዋል።

ባለፈው ወር በርካታ አርብቶ አደሮች በተደራጁ የተቀናቃኝ ጎሳ አባላት ተገድለዋል።

ፕሬዝደንት ኢብራሂም ቦባካር ኬይታ በሰጡት መግለጫ የጠቅላይ ሚንስትሩን ከኃላፊነቴ ልነሳ ጥያቄ ተቀብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ መግለጫ ''በሃገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር እና መንግሥት ይሰየማል'' ይላል።

የማሊ መንግሥት እአአ በ2012 ላይ ከአልቃይዳ ጋር ግነኙነት እንዳላቸው የሚታመን ጸንፈኛ ቡድኖች የሃገሪቱን ሰሜናዊ በረሃማ ከፍል መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አካባቢውን ከጸንፈኛ ቡድኖቹ ማጽዳት ተስኖታል።

160 አርብቶ አደሮች በግፍ መጨፍጨፋቸውን ተከትሎ የማሊ መንግሥት በሃገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ተስኖታል በሚል ከፍተኛ ጫና ሥር ወድቋል።

በአርብቶ አደሮቹ ግድያ ማሊያዊያን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ ይህን በመቃወም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመዲናዋ ባማኮ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።

የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎም ፕሬዝደንቱ በቴሌቪዥን ለህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ''ንዴቱን ስምቻለሁ'' ሲሉ ተደምጠዋል።