ደስታና እንቅልፍ- የፀሃይ ብርሃን ለህይወት አስፈላጊ የሆነባቸው ምክንያቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደምትገኙበት የዓለም ክፍል ቀን ሊረዝምና ሊጨልም ቢችልም የሚያገኙት ብርሃን አስፈላጊነት ግን ጥያቄ የሌለው ነገር ነው። በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ ሌሊቶች በደቂቃዎች አጠር እያሉ ቀናት ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ረዘም ይላሉ።
በአንፃሩ ደግሞ በደቡባዊው ክፍል ለሚኖሩ በተቃራኒው ይሆናል።
በደመናማና ጨለምለም ባሉት ወራትም ቤት ሞቅ ሞቅ አድርጎና ደረብረብ አድርጎ ሞቅ የሚያደርግ ምግብ መብላትም ደስ የሚል ነገር አለው። ነገር ግን የፀሃይ ብርሃን ለጤና ወሳኝ ነው።
ብዙዎች ፀሃይ የምትፈነጥቅበትን ጊዜ በፍንጥዝያ ነው የሚቀበሉት። ይህ ጊዜ ሰዎች በደስታ ተሞልተው የሚጠብቁት የሚናፍቁትም ነው። ሰዎች በደስታና በልዩ ስሜት ሆነው ለምን ይጠብቃሉ? ለሚለው ሳይንስ መልስ ያለው ይመስላል።
1. ብርሃን ሰዓት ቆጣሪ ነው
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀናችን በ24 ሰዓት ዑደት የተወሰነ ነው። ይህ ዑደት መሬት በራሷ ዛቢያ ለመዞር የሚወስደው 24 ሰዓትን የተከተለ ሲሆን ሰርካዲያን ሰዓት ይባላል።
ይህ የሰዎች የሰዓት ዑደት ያለምንም ሌላ ተፅእኖ ሁሌም የሚቀጥል ቢሆንም ሰውነት ግን ከምንም በላይ ብርሃንን ይከተላል።
ይህ የሰውነት የውስጥ ክፍል ስርዓቶች ብርሃንን ይከተላሉ ማለት ነው።
2. ብርሃንን ተከትሎ መተኛትና መንቃት
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብርሃን የመኝታና የመንቃትን ጊዜ ጠቋሚ ነው። ይህ የሚሆነው ብርሃን አእምሯችን የመተኛትና የመንቃት ጊዜን እንዲያውቅ በማድረግ ነው።
በዚህ መልኩ መሸት ሲል አእምሯችን ለመተኛት የሚረዳንን ሜላቶኒን የተሰኘው ሆርሞን እንዲመረት መልእክት ያስተላልፋል።
የተወሰኑ አየር መንገዶች ይህን የተፈጥሮ ዑደት ለመከተል መንገደኞች ሲሳፈሩ እራት ላይ ዘና የሚያደርግ ብርሃን ከዚያም ፀሃይ መጥለቂያ በሚመስል መልኩ ብርሃን በመልቀቅ መንገደኞቻቸው እንዲያሸልቡ ለማድረግ ይሞክራሉ።
3. ብርሃን እንቅልፍ ማጣትን ይከላከላል
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮምፒውተር፣ ታብሌትና ስልክ ስክሪኖች የሚለቁት ሰማያዊ ብርሃን ለመተኛች የሚረዳው ሆርሞን እንዳይለቀቅ ያደርጋል። በቅርቡ እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከእንቅልፍ በፊት እነዚህ ነገሮችን ማስወገድን ይመክራሉ። እንዲያውም እነዚ ነገሮች በእንቅልፍ ሰዓት መኝታ ክፍል ሁሉ እንዳይገኙ ሁሉ ይመከራል።
እንቅልፍ የመተኛት ችግር ካለብዎት የጠዋት ፀሃይን ማግኘት እንደሚረዳ ጥናቶች ያመለክታሉ።
4. ብርሃን ስሜታችን ላይ ተፅእኖ ያደርጋል
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀን የተወሰነ ብርሃን ማግኘት ለእንቅልፍ ብቻም ሳይሆን ለስሜታችንም ወሳኝ ነው። ከሰዎች ደስተኝነት ጋር በቀጥታ ይገናኛልና።
ብርሃን ላይ ስንሆን አእምሯችን መልእክት ስለሚደርሰው ጥሩ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርገው ሴሮቶኒን የተባለው ሆርሞን በደንብ እንዲመረት ያደርጋል። በተቃራኒው አነስተኛ የብርሃን የሚያገኙ ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ይታመናል።
ቀናት በሚያጥሩበት ወቅት የብርሃን እጥረት በሚያሳድረው ተፅእኖ ብዙዎች በተመሳሳይ የስሜት ችግር ይጠቃሉ።
5. የፀሃይ ብርሃን አጥንትን ያጠነክራል
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰውነት ከምግብ የሚገኘውን ካልሲየምና ፎስፈረስ መጠቀም እንዲችል የፀሃይ ብርሃን ወሳኝ ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ ለአጥንት፣ ለጥርስና ጡንቻ መጠንከር እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
በተቃራኒው ከፀሃይ ብርሃን የሚገኘው ቫይታሚን ዲ (የፀሃይ ቫይታሚን) እጥረት የአጥንት ደካማነትንና የአጥንት መጣመምን ያስከትላል። በርግጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለፀሃይ መጋለጥም ችግር እንደሚያስከትል አይዘነጋም።