ስሪላንካ ውስጥ በተፈፀመ ተከታታይ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 290 ደርሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዕለተ ሰንበት፤ የስሪላንካ ሰዎች ሃገር ሰላም ብለው ፋሲካን እያከበሩ ሳለ ነበር ተከታታይ ጥቃቶች ቤተክርስትያናት እና ታዋቂ ሆቴሎች ላይ የተፈፀሙት።
ጥቃቱ የተጀመረው በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 2፡45 ገደማ ነበር፤ ስድስት ተከታታይ ፍንዳታዎች ተከታትለውም ተሰሙ።
የመጀመሪያዎቹ ዒላማዎች የነበሩት ሦስት ቤተክርስትያናት ሲሆኑ፤ ፋሲካን ሊያከብሩ የሄዱ ምዕመናንን ታሳቢ ያደረጉ ጥቃቶች ናቸው ተብለዋል። ለጥቆም በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ሆቴሎች ሦስቱ ተመሳሳይ ጥቃት ተሰነዘረባቸው።
ፖሊስ እነዚህን ጥቃቶች በጀ እያለ በነበረት ወቅት ደግሞ ሌሎች ሁለት ጥቃቶች ተከታትለው ተፈፀሙ።
የሀገሪቱ አየር ኃይል ዘግየት ብሎ እንዳስታወቀው አንድ ፈንጂ ቁስ በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተገኝተል።
እስካሁን 500 ያክል ሰዎች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ስሪላንካ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የሌላ ሀገራት ዜጎችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል።
ስሪላንካ ድንጋጤ ውስጥ ናት። ከእርስ በርስ ጦርነት ከወጡ አስር ዓመት እንኳን ያልሞላቸው የሃገሪቱ ዜጎች በዕለተ ፋሲካ ማለዳ በሰሙት ፍንዳታ ሰቀቀን ውስጥ መሆናቸውን በርካታ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ።
የስሪላንካው ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል የደህንነት ኃይላቸው ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል መረጃ ቢደርሰውም ፈጣን ምላሽ አልሰጠም ሲሉ ወቅሰዋል። «እኔም ሆንኩ ሚኒስትሮቼ ስለጥቃቱ ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። ለምን ቅድመ ጥቆማ እንዳልደረሰን ማጣራት ይኖርብናል» ብለዋል።
መንግሥት ዜፎቹን ለማረጋጋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲሉም ተደምጠዋል ጠቅላዩ። ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ለጊዜው ሊዘጉ እንደሚችሉም ወሬ እየተሰማ ነው።
የሃገሪቱ ፖሊስ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ እስካሁን 24 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ቢልም፤ ጥቃቱን ማን እንደፈፀመው በውል የተለየ ነገር የለም።
ኮሎምቦ የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ ባለሥልጣናት ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ጥቃቱ የተፈፀመው በአንድ "ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን" ሳይሆን አልቀረም።
ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ የክርስትና እምነት ተከታይ ስሪላንካውያን እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ የሕንድ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ፖርቱጋል፣ ቱርክና ኔዘርላንድስ ዜጎችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተሰምቷል።

• ሴቶች ስለምን የአሸባሪ ቡድኖች አባል ይሆናሉ?
በአብዛኛው ሴቶች ሰላማዊ ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ይሁን እንጂ ሴቶች በሽብር ቡድን ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንደሚጫወቱ ጥናቶች ያመለክታሉ።