የዩክሬን ምርጫ፡ 'ኮመዲያኑ' ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቀልደኛ ወይም 'ስታንድ አፕ ኮመዲያን' ናቸው፤ አዲሱ የዩክሬን መሪ ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ።
በሁለት ዙር በተካሄደው የዩክሬን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ብልጫ በማምጣት መንበረ-ሥልጣኑን ተቆናጠዋል።
የ41 ዓመቱ ኮመዲያን፤ ተቀማጩን ፕሬዝደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮን 70 በመቶ በሆነ ድምፅ በመዘረር ነው ማሸነፍ የቻሉት።
«በኔ ይሁንባችሁ ጥዬ አልጥላችሁም» ሲሉም ለደጋፊዎቻቸው በድል ዜማ የቃኘ ንግግር አሰምተዋል።
ከድሉ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት ዜሌንስኪ፤ በሩስያ ከሚደገፈው የዩክሬን ታጣቂ ቡድን ጋር የሰላም ሰምምነት ለማምጣትም ቃል ገብተዋል።
ዜሌንስኪ፤ በቴሌቪዥን በሚሰሠራጭ አንድ አስቂኝ ተከታታይ ድራማ ላይ የዩክሬን ፕሬዝደንት ሆነው በመተወን ይታወቃሉ።
ኪዬቭ የሚገኘው የቢቢሲው ተንታኝ ጆናህ ፊሸር ዜሌንስኪ፤ «ቀልዱን ወደጎን ትተው ሀገሪቱን ሰጥ ለጥ ብለው የሚመሩበት ጊዜ ቀርቧል» ብሏል።
የዩክሬን ጎረቤት ሀገር ሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር መሥሪያ ቤት «ዩክሬናውያን ለፖለቲካዊ ለውጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል» የሚል መግለጫ አውጥቷል።
በተጨማሪም ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ለአዲሱ ፕሬዝደንት ያላቸውን ድጋፍ የገለጡ ሀገራት ናቸው።
ከአንድ ወር በኋላ በይፋ የፕሬዝደንትነት ቃለ-መሃላ ፈፅመው መንበሩን የሚረከቡት ዜሌንስኪ፤ በርካታ ፈተናዎች እንደሚጠብቋቸው እሙን ነው። ምክንያቱም የያዙት ሥልጣን እንደ ቴሌቪዥኑ በ 'ስክሪፕት' የተደገፈ አይደለምና።