ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያገናኙት የድንበር በሮች ተዘጉ

ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስኑ ድንበሮች

የፎቶው ባለመብት, Google

ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙት ሁሉም የድንበር በሮች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋገጡ።

የሁመራ-ኦማሃጀር ድንበር ባሳለፍነው ሳምንት የተዘጋ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ የቡሬ-አሰብ ድንበር መዘጋቱን የአፋር ክልል የሕዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኦስማን እድሪስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተቀሩት ሁለቱ ድንበሮች ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ዝግ መደረጋቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ ድንበሮቹ ለመዘጋታቸው ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም፤ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የቪዛ እና የቀረጥ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ በሚል ምክንያት በእግር እና በመኪና ድንበር ማቋረጥ ለማስቆም በማሳብ የድንበር በሮቹ ዝግ መደረጋቸውን ይጠቁማሉ።

ቢቢሲ ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት ለማጣራት የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ጥረት አድርጓል።

በአሥመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት የሚችለው የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ነው ብሏል። የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ በድንበር ጉዳዮች ላይ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ አነጋግሩ ብሎናል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የፕሬስ ሴክተሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቆይተን እንድንደውል ነግረውናል። ተጨማሪ መረጃ እንዳገኘን እናቀርባለን።

የትግራይ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊያ ካሳ፤ "ድንበሮቹ የተዘጉበትን ምክንያት የፌደራል መንግሥት ለሕዝብ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ከወራት በፊት ድንበሮቹ መከፈታቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ዜጎች መካከል ንግድ ተጧጡፎ እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል።

ለምሳሌ ለሱዳን ቅርብ የሆነው ሁመራ-ኦመሃጀር ድንበር ሳይዘጋ በፊት ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ነበረው። በሑመራ ገንዘብ መንዛሪዎች ንግድ ደርቶላቸው ዶላር ወደ ናቅፋ እንዲሁም ናቅፋ ወደ ዶላር ይመነዝሩ ነበር። ዛላምበሳ-ሰርሃ ደንበር እንዲሁም ንግድ ተጧጡፎ ነበር።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ 1ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ድንበር ይጋራሉ። ለመሆኑ በዚህ ረጅም ድንበር ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ አራቱ መግቢያና መውጫ በሮች የትኖቹ ናቸው?

1. ዛላምበሳ-ሰርሃ

ቀድመው ከተከፈቱት ሁለት በሮች የዛላምበሳ-ሰርሃ ድንበር አንዱ ነበር። በቅድሚያ የተዘጋውም ድንበር ዛላምበሳ-ሰርሃ ነው።

አንድ ሰው ከመቐለ ከተማ ተነስቶ፣ አዲግራትን አልፎ፣ ዛላምበሳን ቢሻገር የኤርትራዋን ሰርሃ መንደር ያገኛል። ጉዞውን ገፋ ቢያደርግ ደግሞ ከፊቱ ሰንዓፈ አለች። መንገዱ፤ ዓዲ ቀይሕን እና ደቀምሃረን የተሰኙ አነስተኛ ከተሞችን አልፎ አሥመራ ድረስ ይዘልቃል።

የዛላምበሳ-ሰርሃ መስመር መስከረም 01፣2011 ዓ. ም. ከተከፈተ በኋላ፤ ፈጣን የንግድ ልውውጥ የተጀመረው ወድያውኑ ነበር። እህልና ሸቀጦች የጫኑ ግዙፍ መኪኖች መስመሩን ማጨናነቅ የጀመሩትም ድንበሩ መከፈቱን ተከትሎ ነበር።

ባለፈው ህዳር ወር ላይ ግን ይህ መስመር መልሶ ተዘግቷል። በአሁኑ ወቅት፤ ለተለመዱት ማህበራዊ መስተጋብሮች በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱም ሃገራት ዜጎች በእግር ከሚያደርጉት ግንኙነት ውጪ፤ መንገዱ ለመኪኖች ዝግ ሆኗል።

2. ራማ-ክሳድ ዒቃ

ኢትዮጵያና ኤርትራ በዚህ መስመር የሚገናኙት በመረብ ወንዝ ላይ በተዘረጋው ድልድይ አማካይነት ነው። በድልድዩ ሁለቱ ጫፎች፤ በኢትዮጵያ በኩል ራማ በኤርትራ በኩል ደግሞ ክሳድ ዒቃ አለች።

በአድዋ በኩል ወደ አሥመራ መግባት የሚፈልግ ሰው፤ በዚሁ መስመር ዓዲ ኳላን እና መንደፈራን አልፎ አሥመራ ድረስ መዝለቅ ይችላል።

ይህ መሰመርም መስከረም ወር ላይ ተከፍቶ ህዳር ወር ላይ ዳግም ተዘግቷል።

3. ሁመራ-ኦምሃጀር

ሁመራ-ኦማሃጀር ሌላኛው በትግራይ በኩል ኢትዮጵያን ከኤርትራ የሚያዋስነው ድንበር ሲሆን፤ ለሱዳን ቅርብ የሆነው በር ነው። ድንበሩ የተከፈተ ሰሞን በድንበሩ አቅራቢያ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት ተስተውሎ ነበር።

ይህ መስመር ዘግየት ብሎ በዕለተ ገና የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት ታህሳስ 29፣2011 ዓ. ም. ነበር የተከፈተው።

ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በተጨማሪ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልና የአማራ ክልል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በዚሁ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ነበር።

ይህ የድንበር በር ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለአማራ ክልልም ቅርብ ነው። ስለዚህም፤ ከጎንደር ወደ ኤርትራ መዝለቅ የፈለገ ሰው ይህን መስመር መምረጡ አይቀሬ ነው።

በሁመራ በኩል ተሰነይንና ባረንቱን አልፎ፤ አቁርደት እና ከረንን ረግጦ አሥመራ የሚያደርሰው ይህ መስመርም ከቀናት በፊት ተዘግቷል።

4. ቡሬ-ደባይ ሲማ

ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ የድንበር በሮች በትግራይ በኩል የሚያዋስኑ ሲሆን ቡሬ-ደባይ ሲማ ደግሞ በአፋር በኩል የሚያገናኘው ነው።

በአፋር ክልል አድርጎ ኢትዮጵያን ከአሰብ ወደብ ጋር የሚያገናኛት ይሄው መስመር ነው።

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቄ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በቡሬ ድንበር

ቡሬ- ደባይ ሲማ መስመር የተከፈተው የሰርሃ ዛላምበሳው መስመር በተከፈተበት የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ላይ ነበር። ይህም የድንበር በር ዛሬ መዘጋቱ ተረጋግጧል።