ኢትዮጵያ፡ ሲራክ ስዩም የዓለማችን ትልቁን ተራራ መውጣት ጀመረ

ሲራክ ስዩም በተራራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Sirak Seyoum

ነዋሪነቱን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገውና የኤሌክትሪካል ምህንድስና ባለሙያው ሲራክ ስዩም ከበርካታ ልምምድ በኋላ የዓለማችን ትልቁን ተራራ፤ ኤቨረስትን ዛሬ ሚያዚያ 15/2011 ዓ.ም መውጣት እንደጀመረ ለቢቢሲ ገለፀ።

ሲራክ እንደሚለው ተራራውን በመውጣት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነው።

"የኔፓል የቱሪዝም ኮሚሽን ማን ተራራ እንደወጣ፣ ማን እንደሞከረ፣ ማን ድጋሜ እንደወጣ የሚመዘግቡበት መዝገብ አላቸው፤ መዝገቡ ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1937 ጀምሮ የወጡ ሰዎች ስም ዝርዝር ሰፍሮበታል፤ በመሆኑም እስካሁን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ ነው የማውቀው" ሲል የመጀመሪያው ስለመሆኑ ያስረዳል።

በርካቶች ሲያዩትም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ፎቶ ለመነሳት ይሽቀዳደማሉ ብሎናል።

ተራራ መውጣት የረዥም ጊዜ ህልሙ የነበረ ሲሆን፤ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ይህንኑ ተራራ ለመውጣት እቅድ እንደያዘ አሳውቆ ነበር።

አንድም በቂ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት ልምድ ካላቸው ሰዎች ስለተነገረው፤ ሁለትም ያለው የገንዘብ አቅም ወጭውን የሚሸፍን ሆኖ ስላላገኘው፤ በሌላም በኩል በአባቱ ሕልፈት ምክንያት ከባድ ሃዘን ውስጥ ስለነበር ህልሙን ሳያሳካው ቆይቷል።

"በጣም ደስ የሚል መጽሐፍ አንብበን ስንጨርስ፤ ሌላ ማንበብ እንደሚያሰኘን ሁሉ፤ ተራራ መውጣትም እንደዚያው ነው" የሚለው ሲራክ፤ በኢኳዶር የሚገኘውን ቺምፖራዞን ተራራ ከወጣ በኋላ ተራራ የመውጣት ፍቅር እንዳደረበት ይናገራል።

እዚህ ላይ የእውቋን ፈረንሳዊት ተራራ ወጪ ኤልሳቤት ሮቨርን ተሞክሮ ያነሳል።

እሱ እንደሚለው ፈረንሳዊቷ ከዚህ ቀደም ከጓደኛዋ ጋር ሆና ይህንኑ ተራራ ሲወጡ የጓደኛዋ ሕይወት አልፏል። እሷ ደግሞ በበረዶው ምክንያት የአይን ጉዳት አጋጥሟታል። ይሁን እንጂ አሁንም ተመልሳ ለመውጣት ከእነሱ ጋር ተገኝታለች- ልክ እንዲህ ነው ሱስ የሚያሲዘው።

በአሁኑ ጉዞ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ዘጠኝ ሰዎች ተሳትፈዋል። ታዲያ አብዛኞቹ ተራራውን ከአንድም ሁለት ሶስቴ የወጡ ናቸው።

ሲራክም ልምድ ያላቸው ሰዎች ባሉበት ቡድን ውስጥ መሆኑ ተጨማሪ ልምድ የማግኘት ዕድልን ፈጥሮለታል።

ምን ስንቅ ቋጠረ?

ሲራክ ከተራራው ጫፍ ደርሶ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ተስፋ ሰንቋል። ተስፋ ብቻም ሳይሆን በቂ ልምምድ አድርጓል።

ከዚያ ባሻገር ግን ከቤት የወጣው ሁለት ትላልቅ ሻንጣዎች ይዞ ነው። ምን ያዝክ? አልነው።

መጀመሪያ የጠራልን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የታሰረበት ከአልሙኒየም የተሰራ የበረዶ መቆፈሪያን ነው። ጫማው ላይ በረዶውን ቆንጥጦ የሚይዝ አስር ሹል ነገሮች ያሉት ብረት መያዝም ግድ ነው።

ከፍተኛ የሆነ ሙቀት የሚሰጡ አልባሳት፣ ጓንት እንዲሁም የታሸጉ ሙቀት የሚሰጡ ኬሚካሎች እና ሌሎች መጠባባቂያ እቃዎችን አሰናድቷል።

የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ነውና ምግብን በተመለከተ ከተፈራረመው አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ የሚቀርብለት ሲሆን አሁን ባሉበት ደረጃ በጣም ኃይል የሚሰጡና ገንቢ የሆኑ ምግቦችን ያዘወትራሉ።

ተራራው አራት ካምፖች ያሉት ሲሆን ይህ አገልግሎት ከካምፕ አራት በኋላ ይቋረጣል። ከዚህ በኋላ ተራራው ጫፍ ለመድረስ የየራሳቸውን ምግብ ይዘው መጓዝ ግድ ይላቸዋል።

"እኔ ምግብ እምቢ ብሎኝ ባያውቅም፤ የተራራው ከፍታ በጨመረ ቁጥር ምግብ እንደማይበላ ነግረውኛል" ይላል።

እሱ እንደሚለው ተራራው ከፍ እያለ ሲሄድ የኦክስጅን እጥረት ስለሚኖር እሳት ለማያያዝ ስለሚያስቸግር አብስሎ ለመብላት ያስቸግራል።

ካምፕ አራት አብስሎ ለመብላት የሚቸገሩበትም ብቻ ሳይሆን ኦክስጅን የሚጠቀሙበት ከፍታ ነው፤ ብዙ የማይተኛበትም ቦታ ሲሆን ከተኙም ኦክስጅን መጠቀም ግድ ይላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Sirak Seyoum

ካምፕ አራት ከደረሱ በኋላ የአየር ሁኔታው ታይቶ ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ተነስተው ረፋድ ሶስት ሰዓት ላይ በተራራው አናት ላይ መድረስ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራል።

ቅድመ ዝግጅት

ይህን ተራራ ለመውጣት ሲሞክሩ በኦክስጅን እጥረት፣ ተንሸራተው በመውደቅና በሌሎች ምክንያቶች በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ የአካል ጉዳትም አጋጥሟቸዋል።

"ብዙዎቹ ለዚህ የሚዳረጉት ራሳቸውን በመኮፈስ በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅትና ልምምድ ሳያደርጉ ስለሚጀምሩ ነው" ይላል ሲራክ።

በዚህ በበረዶ ግግር በተሞላና ከኔጋቲቭ 25 ዲግሪ ሴልሺየስ የአየር ጠባይ ተራራ ለመውጣት እርሱስ ምን ዝግጅት አደረገ?

በተራራው ግርጌ ካለው ካምፕ ሆነው ልምምድ ያደርጋሉ፤ አየሩን ይለማማዳሉ። ሌሎች ተራራሮችን ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ።

ሲራክም ከባህር ጠለል በላይ 6090 ሜትር ከፍታ ያለውን ሎቦቼ ተራራን ወጥቷል። ይህም ከመጀመሪያው ካምፕ ወደ አንደኛው ለመሄድ የሚያስችላቸውን አቅም የሚፈታተኑበት ነው።

ወደ ዋናው ጉዟቸው ከመነሳታቸው ሁለት ቀን ቀድሞ በኔፓሎች ባህል 'ፑጃ' የተባለው ዝግጅት ይከናወናል። ይህ ዝግጅት የቡደሃ እምነት በሚከተሉት ኔፓሎች የፀሎትና የምርቃት ሥነ ሥርዓት ይደረግላቸዋል።

በእነሱ ባህል መሠረት አንድ ሰው ይህን ዝግጅት ሳይካፈል ከወጣ ለተራራውም ሆነ ለወጭው መጥፎ ዕድል ነው ብለው ያምናሉ። ተመራርቀው በጸሎት ነው የሚሸኛኙት።

በመሆኑም እሁድ ሚያዚያ 13/2011 ዓ.ም ሥነ ሥርዓቱን ተካፍሏል።

ሲራክ እንደነገረን በአንድ ጊዜ ተራራውን መውጣት አዳጋች ነው፤ በመሆኑም ከመነሻ ካምፕ ወደ አንደኛው ከሄዱ በኋላ ወደ መነሻው ካምፕ ይመለሳሉ። እንደገና ሁኔታቸው ታይቶ ከመነሻ ካምፕ ወደ ሁለተኛው ካምፕ ይጓዛሉ። እንደገና ተመልሰው ወደ መነሻ ካምፕ ይወርዳሉ። ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በቀጥታ ተራራውን መውጣት የሚጀምሩት።

ተራራውን በመውጣቱ ምን ያተርፋል?

ሲራክ ተራራውን ለመውጣት የተነሳው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያገለግል የነበረውንና መሃሉ ላይ የአንበሳ ምልክት ያለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ነው።

አንበሳ የኢትዮጵያ ምልክት ነው የሚለው ሲራክ፤ "ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ባደረጉት አስተዋጽኦ ምክንያት የአፍሪካ አንድነት ምልክት ሆኖ ይሰማኛል፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት እጅ አለመውደቋን ያስገነዝበናል፤ በመሆኑም ሁል ጊዜ በልቤ ተጽፎ ይኖራል" ይላል።

የኢትዮጵያን ስም ማስጠራትና ሰንደቅ ዓላማዋን ተራራው ጫፍ ላይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ አገሪቱ ያላትን የርሃብና የኋላቀርነት ታሪክ መለወጥ ዓላማው እንደሆነ ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, SIRAK SEYOUM

በአሁኑ ጉዞው የምዝገባ ክፍያውን ጨምሮ ለአልባሳትና አንዳንድ ለሚያስፈልጉት ወጪዎች በትንሹ እስከ ስልሳ ሺህ የአሜሪካ ዶላር (1 ሚሊየን 740 ሺህ ብር ገደማ) አውጥቷል።

ሲራክ በዚህ ብቻ አያቆምም ፓኪስታን ውስጥ እንደሚገኘው ኬቱ 8,611 ሜትር (28,251 ጫማ) ከፍታ ያላቸው ፈታኝ ተራራዎችን የመውጣትም እቅድ አለው።

አግራሞት

ሲራክን ካለበት ስናነጋግረው በተራራው ግርጌ ባለው ካምፕ ውስጥ ሆኖ ነበር። በእርግጥ በሥፍራው በቀጥታ የስልክ መስመር ማግኘት ባይቻልም ኢንተርኔት ግን ይሰራል። ይህ ለሁላችንም አግራሞትን የፈጠረ ነበር።

ሁለት ኔፓላውያን 'ኤቨረስት ሊንክ' የሚባል የኢንተርኔት ኮኔክሽን እንዳዘጋጁላቸው ይናገራል።

'ኤቨረስት ሊንክም' ኔፓላውያን ተራራውን ለሚወጡት ደንበኞቻቸው የፈጠሩት የኔትወርክ ስም ነው። ለሁለት ጊጋ ባይት የኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት 75 የአሜሪካ ዶላር በውድ እየገዙ እንደሚጠቀሙ ሰምተናል።